ወጣት ዲ/ን ሳሙኤል ብርሃኑ እና ከንቲባ ሮቤን ዌልስ በመድረክ ላይበታምሩ ገዳ

የፊታችን አርብ ለንደን ውስጥ በሚከፈተው እና በብዙ ቢልዮኖች የሚቆጠር የአለም ህዝብን ትኩረት እና ቀልብ ለመጪዎቹ አራት ሳምንታት ይስባል ተብሎ በሚገመተው የለንደን 2012 እኤአ የኦሎምፒክ እና ፓራ ኦሎምፒክ ውድድርን ምክንያት በማደርግ ላለፉት ሶስት ወራት ከጥንታዊቷ የኦሎምፒክ አገር ግሪክ ተነስቶ በመላው የእንግሊዝ ከተሞች ሲበራ የነበራው የኦሎምፒክ ችቦ ለንደን ከተማ ውስጥ አርብ ዕለት ገብቷል። በበነጋታው (ቅዳሜ ዕለት) በመዲናይቱ ጎዳናዎች ላይ በተደረገው የችቦ ማብራት ስነስርአት ላይ የተሳተፈው ወጣት ኢትዮጵያዊ ችቦ አብሪ ከማህበረሰቡ ከፍተኛ አድናቆት እና ድጋፍ ተቸሮታል።

 

በለንደን ከተማ በሚገኘው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክን የቅዱስ ሥላሴ ቤ/ን አገልጋይ የሆነው የአስራ ዘጠኝ አመቱ ወጣት ዲያቆን ሳሙኤል ብርሃኑ ቅዳሜ ዕለት (ሃምሌ 21 ቀን 2012 እኤአ) ከቀትር በፊት በምስራቅ ለንደን ኔውሃም በተባለው ክፍለ ከተማ ጎዳና ላይ በተደረገው የኦሎምፒክ ችቦ የማብራት ሩጫ ላይ በመሳተፍ በተለይ የችቦው ማብራቱ ስነስርአት በተጠናቀበት በክፍለ ከተማው የህዝብ ዋና የመዝናኛ ስፍራ ፓርክ ሲደርስ ቁጥሩ ከአምስት ሺህ እስከ አስር ሺህ የሚገመት የአካባቢው ነዋሪ እና የኦሎምፒክ ውድድር አፍቃሪዎች በጭብጨባ እና በእልልታ ለኢትዮጵያዊው ወጣት ችቦ አብሪ ለዲ/ን ሳሙኤል አድናቆታቸውን ሰጥተውታል።

 

በአሉን በማስመልከት በስፍራው ቀደም ብለው የተገኙት የኒው ሃም ክፍለ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ሰር ሮቤን ዌልስ ዕለቱን በማስመልከት ባሰሙት ንግግር “ይህንን ለአመታት በጉጉት ስንጠብቀው የነበረው እና የአለም ህዝብን ትኩረት በሳበው ለለንደኑ ኦሎምፒክ ውድድር የጎዳና ላይ ችቦ የማብራት ስነ ስርአት በተለይ ደግሞ በመዝጊያው ፕሮግራም ላይ ተመርጠህ እዚህ መድረክ ላይ በመገኘትህ ላንተ ታላቅ አክብሮት አልን። በሰራሃቸውም ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችህ ኮርተንብሃል።” በማለት ለወጣቱ ኢትዮጵያዊ ሳሙኤል አድናቆታቸውን አሰምተዋል። በአካባቢው የነበረው ህዝብም በበኩሉ “ብራቮ ሳሚ!! ... ብራቮ ሳሚ! ... ወዘተ” በማለት አድናቆቱን በኦህታ እና በጭብጨባ ቸሮታል። በመድረኩ ላይ ከከንቲባው ጋር የችቦ ነበልባሉን በጋራ ያጠፋው ወጣት ሳሙኤል ለተሰበሰበው ህዝብ አስተያየቱን እንዲሰጥ የተጋበዘ ሲሆን፣ በአጭር ቃላት “እጅግ ውብ እና ግሩም አጋጣሚ ነበር።” ሲል የተሰማውን ደስታ ገልጿል።

 

ይህ በኦሎምፒክ ታሪክ ከፍተኛ የደህንነት እና የፓሊስ ጥበቃ እንደሚደረግለት የተነገረለት የለንደኑ 2012 ኦሎምፒክ የጎዳና ላይ የችቦ ማብራት ስነስርአት ላይ የተገኘው ከምደረ አሜሪካ ከላስ ቬጋስ ከተማ የሚሰራጨው የህብር ራዲዮ የምዕራብ አውሮፓ ልዩ ዘጋቢ (ይህ ጸሃፊ) ለወጣቱ ኢትዮጵያዊ ችቦ አብሪ ምን እንደተሰማው ላቀረበለት ጥያቄ “የህዝቡ ቁጥር እና የሞራል ድጋፍ ከገመትኩት በላይ ነበር። በዚህ ታላቅ እና ታሪካዊ ፕሮግራም ላይ አገሬን እና ማህበረሰቡን ወክዮ በመገኘቴ በጣም እድለኛ ነኝ። ይህንንም አጋጣሚ ለሰጠኝ ፈጣሪ አምሰግናለሁ። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በማለዳ ተነስተው በኒው ሃም ክፍለ ከተማ ጎዳናዎች ላይ በመቆም ድጋፋቸውን ለሰጡኝ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቼ እና ለመላው የኦሎምፒክ ቤተሰብ ልባዊ ምስጋናዩን አቀርባልሁ።” ብሏል።

 

የችቦውን ማብራት ስነስርአት ምክንያት በማደረግ የተለያዩ የአፍሪካ፣ የካሪቤያን፣ የእስያ እና የአውሮፓ ዘመናዊ እና ባህላዊ የጎዳና ላይ ትርኢቶች የኦሎምፒኩ ችቦ በሚጓዝባቸው ጎዳናዎች ላይ የታዩ ሲሆን፤ ለፕሮግራሙ ስኬት እና ለደህንነት ሲባል በርካታ አውራ ጎዳናዎች ለሰአታት ከትራንስፖርት አገልግሎት ከመስጠት ታግደው ነበር። ወጣት ዲያቆን ሳሙኤል በአሁን ሰአት በሚማርበት ኮሌጅ ትምህርቱ ከሚያደርጋቸው የተለያዩ የስፖርት እና የተማሪዎች እንቅስቃሲዎች በተጨማሪ በተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች በመሳተፉ ይህንን ታሪካዊ የሆነውን የኦሎምፒክ ችቦ እንዲያበሩ ከተመረጡ ታዋቂ እና ስመ ጥሩ ሰዎች ጋር ችቦ እንዲያበራ በአዘጋጅ ኮሜቴዎቹ የተመረጠ እና ለወደፊቱም ቢሆን ተስፋ የሚጣልበት ወጣት ኢትዮጵያዊ መሆኑ የኦሎምፒክ ችቦ አዘጋጆቹ መስክረውለታል።

ወጣት ዲያቆን ሳሙኤል ብርሃኑ Samuel Berhanu 

በለንደኑ የ2012 እኤአ ኦሎምፒክ ውድድር ከሁለት መቶ አገሮች የተውጣጡ ጠንካራ የአለም አትሌቶች ይሳተፋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም ለዚህ ውድድር ሰላሳ አምስት አትሌቶችን መርጣ መላኳ እና ከዚህ ቀደም በተካሄዱት ተመሳሳይ የኦሎምፒክ ውድድሮች ላይ የተሳተፉ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ሰላሳ ስምንት ሜዳሌያዎችን በማግኘት የሃገራቸው ሰንደቅ አላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አድርገዋል።


ለተጨማሪ ማብራሪያዎች ወይም ጥያቄዎች ጸሃፊውን በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ያገኛሉ።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ