“የመንግሥት ሥልጣን ቢሰጣቸው የግል ፕሬሱን ያጠፉት ነበር ማለት ነው?” ዐብይ ተ/ማርያም (አዲስ ነገር)

“በገዥው ፓርቲ እንዲሠሩ የተፈቀደላቸውን ጥቂት ፕሬሶች እሳቸው እያዋከቡት ነው” ዳዊት ከበደ (አውራምባ ታይምስ)

Ethiopia Zare (እሁድ ሰኔ 1 ቀን 2000 ዓ.ም. June 8, 2008)፦ የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ሠርተፍኬት ከበርካታ ውዝግብ በኋላ የተሰጣቸው አቶ አየለ ጫሚሶ ሠርተፍኬቱን ካገኙ ገና አንድ ዓመት ሳይሞላቸው ሦስት የግል ጋዜጦች ላይ ክስ መሠረቱ። “የመንግሥት ሥልጣን ቢሰጣቸውና የፖሊስ እና የዐቃቤ ሕግ አካል በእጃቸው ቢገባ ነፃ ፕሬሱን ያጠፉት ነበር ማለት ነው?” ሲል የአዲስ ነገር ማኔጂንግ ኤዲተር ሲጠይቅ፣ “በገዥው ፓርቲ እንዲሠሩ የተፈቀደላቸውን ጥቂት ፕሬሶችን እሳቸው እያዋከቡት ነው” ሲል የአውራምባ ታይምስ ዋና አዘጋጅ አቶ ዳዊት ከበደ አስተያየቱን ሰጥቷል።

 

በአቶ አየለ ጫሚሶ የሚመራው ቅንጅት፤ አዲስ ነገር በተባለው ጋዜጣ ላይ የአሜሪካን ኢምባሲ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በኤምባሲው ጠርቶ ባነጋገረበት ወቅት አቶ አየለ አለመጋበዛቸውንና አምባሳደር ዶናልድ ያማማቶ “አቶ አየለን እንደተቀዋሚ አልቆጥራቸውም” አሉ በሚል ምንጮቻቸውን ጠቅሰው ያቀረቡትን ዘገባ መነሻ በማድረግ በጋዜጣው ዋና አዘጋጅ አቶ መስፍን ነጋሽና፣ ም/ዋና አዘጋጁ አቶ ግርማ ተስፋው ላይ ክስ መስርቷል።

 

አውራምባ ታይምስ በተባለው ጋዜጣ ላይም የቀድሞው የቅንጅት የላዕላይ ምክር ቤት አባል ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ “የቅንጅቱ ስያሜ ለማንም መንገደኛ ተሰጥቷል” የሚል ቃለምልልስ ሰጥተዋል ሲሉ የጋዜጣውን ዋና አዘጋጅ ጨምሮ አራት ጋዜጠኞች ላይና ዶ/ር ያዕቆብን ጨምሮ ከሷል።

 

“ሶሬሳ” የተባለና አሁን ከገበያ የወጣን ጋዜጣም በተመሳሳይ መልኩ “የአቶ ዓባይነህ ቅንጅት ጠቅላላ ጉባዔ ሊጠራ ነው” በሚል ዘገባ ሠራ ብሎ ክስ መስርቶበታል።

 

ከተከሰሱት ጋዜጦች አንዱ የሆነውን የአዲስ ነገር ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር አቶ ዐብይ ተክለማርያምን “ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲ እንዲመሠረት የሚፈልግ አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ ለምን ተነካሁ ብሎ በሆነ ባልሆነው የግሉ ፕሬስ ላይ ክስ መመስረት ምን ያህል ያስኬዳል?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፡-

 

አንድ ፓርቲ እንደተቃዋሚዎቹ ባህሪ የሚመሠረት ስለሆነ ፓርቲው ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲ እንዲመሠረት ይፈልጋል ለማለት እንደማይቻል ገልፀው፤ ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲመሠረት የሚፈልግ ፓርቲ ዲሞክራት መሆኑን ማሳየት አለበት፤ አለበለዚያ ከፋሽን አያልፍም ብለዋል።

 

ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት አንኳር ከሆኑት ነገሮች አንዱ፤ ሃሳብን በነፃነት መግለፅ ሲሆን፣ ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የመንግሥት ሚዲያ በመንግሥት ተይዞ መንግሥት ከሚለው ውጭ የማይቀርብበት ሁኔታ እንዳለ ጠቁመዋል።

 

ገለልተኛ በሆነ መንገድ የመንግሥትንም የተቃዋሚንም ሃሳብ ለህዝብ እያስተላለፈ ያለው የግሉ ሚዲያ ነው፤ ይህንኑ ሚዲያ አናት አናቱን የሚባል፣ የሚዋከብ፣ መብቱን በተቃዋሚ ፓርቲ የሚገፈፍ ከሆነ የራሱን ሃሳብ የት ሊያቀርብ ነው? ይህ ማለት ደግሞ ለዲሞክራሲ አይታገልም ማለት ነው፣ ዓላማ የሌለው ዲሞክራሲን በስም ብቻ ይዞ የተቀመጠ ድርጅት ነው ሲሉ አቶ ዐብይ አስተያየታቸውን ገልፀዋል።

 

“ቅንጅት” የሚለውን የስያሜ ጉዳይም በሚመለከት ራሳቸውን ቅንጅት ነን እያሉ የሚጠሩ ብዙ ቡድኖች አሉ። ቦርዱ የቅንጅትን ሠርተፍኬት ከመስጠት ባለፈ ፕሬሱ እከሌን በግድ በዚህ ስም ይጥራ ብሎ ማስገደድ አይችልም። ሦስተኛ ወገን በግዴታ ይወቀውና በዚህ ይጥራው ብሎ ለማስገደድ የተቀመጠ ሕግ የለም፤ በዚህ ላይ ስያሜውን በሚመለከት ቦርዱ ከእነ ኢ/ር ኃይለ ሻውል ጋር በፍርድ ቤት እየተከራከረ ነው ያለው።

 

ፖሊስን በሚመለከት ማንም ተነስቶ እከሌ ወንጀል ሠርቷል ሲል ሄዶ መክሰስ፣ ማሰርና ዋስ አስጠርቶ መልቀቅ አይደለም፤ የፖሊስ ሥራ ጉዳዩ ያስከስሳል አያስከስስም ብሎ መመርመር አለበት። እኛ የተከሰስነው አምባሳደሩ አሉ ብለን በፃፍነው ነው፤ መጀመሪያ መጠየቅ ያለበት አምባሳደሩ እንዲያስተባብሉ ማድረግ ሲገባ እሳቸው ባልተጠየቁበት ሁኔታ ወደ ፕሬሱ መጥቶ ማዋከብ አይገባም ነበር ብለዋል።

 

አቶ አየለም ቢሆኑ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ሦስት የግል ጋዜጦች ከከሰሱ፣ የመንግሥት ሥልጣን እጃቸው ቢገባ የግሉን ፕሬስ ያጠፉት ነበር ማለት ነው? ሲሉ የአዲስ ነገር ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር አቶ ዐብይ ተክለማርያምን ይጠይቃሉ።

 

የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በበኩላቸው ከአቶ ዐብይ ሃሳብ ጋር ይስማማሉ። ፖሊስ ክስ ስለቀረበለት ብቻ እየተቀበለ አይከስም፣ ማጣራት አለበት፣ እኛ የሠራነው ቃለ ምልልስ ነው፣ የሰው ሃሳብ ነው ያስተናገድነው ግን ምንም ማጣራት ሳይደረግ አቶ አየለ ስለከሰሱ ብቻ አራት ጋዜጠኛ ላይ በአንድ ክስ ይመሰርታል ሲሉ ጠይቀዋል።

 

ገዥው ፓርቲ በትንሹም ቢሆን የፈቀደውን ነፃ ፕሬስ፣ ለዲሞክራሲ እታገላለሁ የሚል ተቃዋሚ ፓርቲ በትርኪ ሚርኪ ማዋከቡ አግባብ አይደለም ብለዋል።

 

በአቶ አየለ የሚመራው ቅንጅት የላዕላይ ምክር ቤት አባል እና የሕግ አማካሪ የሆኑት አቶ ተሾመ ወልደ ምህረት ስለጉዳዩ እንደገለጹት፤ ያለ ጠንካራ ፕሬስ ምንም ዓይነት ዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ሊኖር ይችላል ብለው እንደማያምኑ፤ በግላቸውም የወጣውን ረቂቅ የፕሬስ አዋጅ እንደማይደግፉ ገልጸዋል።

 

ነገር ግን ሦስቱም ጋዜጦች ከሕግ ውጭ የፓርቲውን ስም የሚነካና የሚያጎድፍ ነገር ከመጻፋቸው በተጨማሪ እንዲያስተባብሉ ሲጠየቁ ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸው፤ ጋዜጠኞች ደግሞ ተገቢውን ሥራ እያከናወኑ በገለልተኛና ሚዛናዊነት ወደ አንድ ወገን ያጋደለ ሳይሆን ያለአድሎ መዘገብ አለባቸው ብለዋል።

 

“ጠንካራ ፕሬስ እንዲኖር እንፈልጋለን በሆነ ባልሆነው ወደ ጣቢያ እንዲሄዱ አንፈልግም፣ ሚዲያው የህዝብ ሚዲያ መሆኑ ታውቆ ምክንያታዊ የሆኑ ዘገባዎች ከቀረቡ እና ስሕተት ተሠርቶ ይስተካከል ሲባል ማስተባበያ ሊሰጥበት ካልተቻለ፣ ከሕግ ውጭ ወደ የት መሄድ እንችላለን?” ሲሉ አቶ ተሾመ መልስ ሰጥተዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ