“ሕፃናት ብቻ 6 ሚሊየን ተርበዋል” ቢቢሲ

“ሕፃናቱ 75 ሺህ ብቻ ናቸው” ኢህአዴግ

“20 ሚሊየን ዶላር ያስፈልጋል” ኢህአዴግ

“ኢትዮጵያ ለገጠማት የምግብ እጥረት 197 ሚሊየን ዶላር እርዳታ ያስፈልጋታል” ተመድ

“ድርቁ በሱማሌ፣ ከፊል ኦሮሚያና ደቡብ ላይ ነው የተከሰተው” አቶ አዲሱ ለገሠ

“ድርቁ በምዕራብ አርሲ፣ በሻሸመኔ፣ በደቡብ አዋሳ ዙሪያ፣ በወላይታ ዞንና በምሥራቅ ሐረርጌ ተሰራጭቷል” ዩኒሲኤፍ

“በግብርናው ባሀብቶች እንዲሳተፉበት ካልተደረገ መቼም ቢሆን በምግብ ራሣችንን አንችልም” የተከበሩ አቶ ቡልቻ ደመቅሣ

Ethiopia Zare (ማክሰኞ ሰኔ 3 ቀን 2000 ዓ.ም. June 10, 2008)፦ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ድርቅ አስመልክቶ ኢህአዴግ የተጎጂዎችን ቁጥር ዝቅ አድርጎ እየተናገረ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የውጭ ሚዲያዎች፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ለጋሽ ድርጅቶች አኀዙ ከፍተኛ መሆኑን እየገለጹ ይገኛሉ። ሁሉም ወገኖች በዚህ የበልግ ዝናብ እጥረትን ተከትሎ ሀገሪቱን እያጠቃ ባለው ድርቅ ላይ የሚሉትን የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ በጽሑፍና በምስል በማቀናበር እንደሚከተለው አቅርቦታል።

 

ቢቢሲን ጨምሮ የተለያዩ የውጭ ማዲያዎች የረሃብተኛውን ቁጥር በሕፃናት ብቻ 6 ሚሊዮን ያደረሱት ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ 126 ሺ አስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን በመጥቀስ በምስል የተደገፈ ዘገባቸውን በማቅረብ ላይ ናቸው። ዓለም አቀፍ የሕፃናት አድን ድርጅት (ዩኒሲኤፍ) ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት በተከሰተው ድርቅ ክፉኛ መጐዳታቸውን አረጋግጧል። በቁጥርም ከመንግሥት በእጅጉ በሰፋ ልዩነት ይጠቅሳቸዋል። እንደ ዩኒሲኤፍ ከሆነ የተራቡ ሕፃናት ቁጥር 5 ሚሊዮን ሲሆን 126ሺው የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ካልደረሰላቸው ከፊታቸው አስከፊ ሁኔታ ይጠብቃቸዋል።

 

ከ2003 በኋላ እንዲህ አይነት አስከፊ አደጋ እንዳላጋጠመ የሚጠቅሰው ዩኒሲኤፍ፣ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት ችግር ውስጥ ላሉ ሕፃናት ለአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ 50 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፣ 5 ሚሊዮን ሕፃናትም እርዳታ የሚጠብቁ ናቸው ብሏል።

 

በኢትዮጵያ በኩል የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው 75ሺ ሕፃናት ናቸው። ለእነዚህም 20 ሚሊየን ዶላር ያስፈልጋል። በመኸር ዝናብ ዕጥረት ሳቢያ የተራቡት 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ህዝቦች አሁን ወደ 4 ነጥብ 5 እንደደረሰ የሚገልፀው የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ለሕፃናት ከሚያስፈልገው አልሚ ምግብ ውጪ 300 ሺ ሜትሪክ ቶን እህል ያስፈልጋል። እስካሁን ከለጋሾች የተገኘው 36 ሺ ሜትሪክ ቶን ብቻ ነው። መንግሥት ክፍተቱን ለመሙላት ለመጠባበቂያ የተቀመጠውን እህል እየተጠቀመ ሲሆን፣ ለጋሾች እርዳታ እንዲሰጡት ባለፈው ማክሰኞ ጠይቋል።

 

ለጋሾች የሚጠበቀውን ያህል መለገስ ያልቻሉት የምግብ እህል 64 ከመቶ የዋጋ ጭማሪ በማሳየቱ መሆኑን ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ገለፃ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን፣ የተረጂዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ለጋሾች ለእርዳታ ጥሪው ምላሽ እንዲሰጡ ጠይቋል።

 

የግብርና ገጠር ልማት ሚኒስቴር ባወጣው ሪፖርት እንደጠቀሰው የበልግ ዝናብ እጥረት የወቅቱን አምራቾችና አርብቶ አደሮችን ማጥቃቱን በመግለፅ፣ የውሃ የምግብና የግጦሽ እጦት አጋጥሟል። ለዚህም የተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚመለከተው መ/ቤትና ለጋሾች ተረጂዎችን በመለየት እርዳታ እየተሰጣቸው ሲሆን፣ በቅርቡም ዝናብ መጣል በመጀመሩ ችግሩ እየተቃለለ መሆኑን ይጠቅሳል። ችግሩን ለማቃለል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ጉዳዮን በማጋነን የሚያቀርቡ አካላት መኖራቸውን የግብርና እና የገጠር ልማት ሚኒስትሩ አዲሱ ለገሠ ገልፀዋል። እንደ አቶ አዲሱ ገለፃ የምርት ዕድገት የለም ብሎ ለማጣጣል ቁጥሩን አግነው አቅርበውታል። ይህን የሚያደርጉት ምንም ዓይነት እርዳታ የማይሰጡን እና መኖሪያና የገቢ ምንጭ ሊያደርጉ የሚፈልጉ አባላት ናቸው ብለዋል።

 

ስለረሃቡ የተዘገበው

የአካባቢው ዶክተሮች ከ400 በላይ ሕፃናት በምግብ እጦት እየተሰቃዩ መሆኑን ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን፣ የእርዳታ ሰጪ ሠራተኞች እንደገለጹት በረሃብ ከተጠቁ 120 ሺ ሕፃናት መሀከል በገንዘብ እጥረት የተነሳ። የሕክምና ክትትል ማግኘት የቻሉት 33 ሺ ሕፃናት ብቻ ናቸው።

 

“በኢትዮጵያ አብዛኛዎቹ ቦታዎች የድርቅ ችግር ተከስቷል” የሚሉት የዩኒሲኤፍ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ቢዮርን ዩንግክቪስት “የምግብ ዋጋ መናር ችግሩን የከፋ እንዲሆን አድርጎብናል፤ ይህ ዓለም አቀፋዊ ክስተት ደግሞ የተመድ የዓለም ምግብ ፕሮግራም እርዳታ የማድረግ አቅሙ ውሱን እንዲሆን አድርጓል” የሚል ገለፃ ሰጥተዋል። በዓለም ዙሪያ የምግብ ዋጋ መጨመሩ ደግሞ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በጀት ከያዘው 60 በመቶ ያነሰ ምግብ እንዲያቀርብ ብቻ የሚያደርገው መሆኑን ገምቷል።

 

ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገራት ናይጄሪያን በመከተል በሁለተኛ ደረጃ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላት ኢትዮጵያ ለገጠማት የምግብ እጥረት 197 ሚሊዮን ዶላር የሚያስፈልጋት መሆኑን የተመድ ተቋማት በመግለጽ ላይ ናቸው። እንደ እርዳታ ሠራተኞች ገለፃ የእርዳታው ገንዘብ በቻይናና ማያንማር ለደረሱት ድንገተኛ የተፈጥሮ አደጋዎች እንዲውሉ መደረጋቸው ሌላ አሳሳቢ ችግር ሆኖ ተገኝቷል።

 

በደቡብ ኢትዮጵያ በረሃብ የተጎሳቆሉ የ1977 ተጎጂዎችን መሰል ሕፃናት በየዕለቱ ወደ ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎችና ቤተክርስቲያናት ያድራሉ። የዓለም ምግብ ፕሮግራም ባወጣው ሪፓርት ከ80 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ውስጥ፣ ስምንት ሚሊዮን መደበኛ እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው በተጨማሪ 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚሆኑት ከነኀሴ እስከ መስከረም ባለው ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው እየገለጸ ይገኛል።

 

የእህል ዋጋው ማሻቀብ ግን የተገኘውን ዕድገት እንድታጣ አስገድዷታል ይላሉ የእርዳታ ሠራተኞች። ይህ ማለት ደግሞ የአሁኑ የኢትዮጵያ ትውልድ በዓለም የከፋውን ረሃብ እንዲጋፈጥ ያደርገዋል። ባለፈው የረሃብና የድርቅ ጊዜ የ24 ዓመት ወጣት የነበረው ተስፋዬ ሃድጉ በአሁኑ ወቅት የሦስት ልጆች አባት ነው።

 

“ለምን እዚህ እንደሆንኩ ሊገባኝ አልቻለም፤ ምናልባት የእግዚአብሔር ፍቃድ ሆኖ ነው” በማለት ምሬቱን የሚገልጸው ተስፋዬ፣ “ሆኖም ግን ስለልጆቼ እየተጨነቅሁ ነው፤ በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ ቦታዎች ምንም ምግብ እንደሌለ ሰዎች በመናገር ላይ ናቸው፤ ዓለም እንደገና እንዲረዳን እንፈልጋለን” ብሏል።

 

በሻሸመኔ የተወለደችው አልፊ ገለቱ የተሰኘች የዘጠኝ ወር ሕፃን በአካባቢው ወደሚገኝ ክሊኒክ ባመራችበት ወቅት 10 ፓውንድ (4 ነጥብ 5 ኪሎ ግራም) ብቻ እንደምትመዝን የጠቆመው የሮይተርስ ሪፖርት፣ የሕፃኗ ዓይን ሲንቀዋለል፣ እጆቿ የውሃ መምጠጫ “ስትሮው” እንደሚያክል በመግለጽ ነበር ሪፖርቱን ያቀረበው። በመንደራቸው ምግብ የሚባል ነገር መታጣቱን የምትናገረው የሕፃኗ እናት ለሣምንታት ከጡቷ በስተቀር ምንም ዓይነት ምግብ ለመስጠት እንዳልቻለች ነው የተናገረችው።

 

ይህ ሆኖ ሳለ የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዩን ለዓለም ለማሳወቅ ዳተኛ የሆነበት መንገድ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማትን እንዳስገረመ ዘገባው ያትታል። የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መንግሥት ይህ አደጋ መከሰቱ በይፋ ለማሳወቅ አልደፈረም ይላል።

 

የዩኤስ አሜሪካ አንድ ተቋም ባለፈው ጥር ሰጥቶት በነበረው ማስጠንቀቂያ፣ በደቡባዊ ሶማሌ ክልል የሚታየው ሁኔታ አሳሳቢና በአፋጣኝ መፍትሄ ሊፈለግለት እንደሚገባ ነበር ያሳሰበው። በየካቲት ወር መጣል የነበረበት ዝናብ በመጥፋቱ በቆሎዎች በእርሻ ማሳው ላይ ክው ብለው እንዲቀሩ በማስገደዱ የዋጋ ግሽበቱ እንዲያሻቅብ አድርጓል።

 

የደቡብ ኢትዮጵያ ሆስፒታሎች የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘታቸው በታመሙ ሕፃናት ተጣቧል። መጋቢት 26 አቶ መለስ ለፓርላማ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ከድርቅ ጋር በተያያዘ ሞት ተከስቷል መባሉን “ውሸት” ብለው መመለሳቸውን የገለጸው የሮይተር ሪፖርት፤ እስካለፈው ሣምንት ድረስ የኢትዮጵያ አደጋ መከላከል ሠራተኞች ወደ ሻሸመኔ ሆነ የድርቅ ስጋት ወዳለባት ደቡባዊ አካባቢ በይፋ አለማምራታቸውን ገልጿል።

 

ድርቁን ይፋ ያላደረገው መንግሥት ባለፈው ዓመት 10 ከመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገቡን ነው የገለጸው። ዶክተር ዊዝአውት ቦርደርስ (ድንበር የለሽ ዶክተሮች) የተሰኘው ተቋም ከአዲስ አበባ 150 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ከተማ ክሊኒክ በከፈተባቸው የመጀመሪያ ሣምንት ቀናት ብቻ 277 በረሃብ የተጎዱ ሕፃናትን ተቀብሏል። በገጠራማ መንደሮች ያለው ሁኔታ ደግሞ የከፋ ሆኗል። ከሻሸመኔ ሁለት ሰዓት የመንገድ ርቀት ላይ በምትገኘው ሴራሮ አካባቢን የተመለከቱ የእርዳታ ተቋማት ባልደረባዎች በአንድ ዕኩለ ቀን ብቻ 55 ሕፃናት መሞታቸውን ገልጸዋል። ይሁንና አዲሱ ክሊኒክ ውስጥ ከገቡ በረሃብ ከተጎዱ ሕፃናት የሞቱት አራት ብቻ ሲሆኑ በሚሰጣቸው የተመጣጠነ ምግብና ወተት ማገገም ችለዋል። ለዚህ መሰሉ እርዳታ የሚያስፈልገው 50 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን የገለጸው ዩኒሲኤፍ ለጋሾች ግን መስጠት የቻሉት ስድስት ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑን ገልጿል።

 

የዩኒሲኤፍ ኮሙኒኬሽን ኦፊሠር አቶ እንድርያስ ጌታቸው ስለጉዳዩ ሀገር ውስጥ ላለ አንድ ሚድያ እንደገለጹት፤ ድርቁ በድንበር አካባቢ ያሉ የአፋርና ሱማሌ ክልሎችን፤ ከፊል የኦሮሚያ ዝቅተኛ ቦታዎችን፣ አርብቶ አደር አካባቢዎችን እንዲሁም ደቡብ ቦረናን በስፋት የተጠቃ መሆኑን ገልፀው፤ ከዚህም በተጨማሪ ችግሩ እየሰፋ በመምጣቱ በደቡብ የወላይታ፣ ከንባታ እና የሲዳማ ዞኖችን በኦሮሚያ ምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌን እያዳረሰ ነው። በነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ህዝቦች በቤታቸው የሚበላ የሌላቸው እርዳታ ጠባቂዎች ናቸው።

 

መንግሥት በሰበሰበው መረጃ 75 ሺ ሕፃናት እንደተጐዱ እየገለፀ ቢሆንም እንደ ዩኒሲኤፍ ግምት በሚቀጥሉት ሦስት ወራት 126 ሺ ሕፃናት በድርቁ ሊጠቁ ስለሚችሉ ለዚህ ተዘጋጅቶ ምላሽ ለመስጠት የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራ እየሠራ መሆኑን አቶ እንድርያስ ገልጸዋል። ሕፃናቱ ከምግብ በተጨማሪ መድኃኒት ነክ ምግቦች ካልተሰጣቸው የመሞት ዕድላቸው ከ25 እስከ 30 በመቶ ይሆናል።

 

ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት የተፈጠረው ድርቅ በሀገር ውስጥ ምርት የተሸፈነ እንደነበር ያስታወሱት አቶ እንድርያስ፣ ያሁኑ በጣም የተለየና ሕፃናቱን በከፍተኛ ሁኔታ የጐዳ በመሆኑ፤ የሚያስፈልገው ከኦቾሎኒ የተሠራው ምግብ በሀገር ውስጥ የሚገኝ ባለመሆኑ ድርጅታቸው በሚዲያ የእርዳታ ጥሪ ለማስተላለፍ እንደተገደደ ይናገራሉ። እስካሁን በተገኘው ንጥረ ምግብ የተወሰኑ ሕፃናቶች በሆስፒታል ተኝተው እየተሰጣቸው በመሆኑ አቅማቸው እየተመለሰ ነው እንደ አቶ እንድርያስ ገለፃ፤ መንግሥት የገለፃቸው 75ሺ ሕፃናት አፋጣኝ እርዳታ ሊደርስላቸው ይገባል።

 

ዝናብ መጣል መጀመሩ ችግሩን ያቃልል እንደሆን የተጠየቁት አቶ እንድርያስ፣ ችግሩን ያረጋጋው እንደሆን እንጂ መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል ጠቁመዋል። ምክንያቱም ሠብል ተዘርቶ ለምርት እስኪደርስ የተወሰኑ ወራቶችን ማስጠበቁ አይቀርም። ድርቁ በአሁን ሰዓት የተሰራጨባቸው ምዕራብ አርሲ፣ ሻሸመኔ፣ ደቡብ አዋሳ ዙሪያ፣ ወላይታ ዞንና ምሥራቅ ሐረርጌ ሲሆኑ ዩኒሲኤፍ ከተ.መ.ድና (የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት) ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በተስማማው መሠረት 30 ሚሊየን ዶላር ጠይቆ ነበር። የችግሩ ስፋት እየተባባሰ ሲመጣ ግን 50 ሚሊየን ዶላር ማስፈለጉን አቶ እንድርያስ ገልፀው፣ እስካሁን ለመድኃኒት ነክ ምግቦች ብቻ 7 ሚሊየን ዶላር በብድር በመውሰድ ግዥ ፈጽመዋል። በዩኒሲኤፍ በኩል እስካሁን በረሃቡ ምክንያት የሞተ ሰው እንዳልታለየ የገለፁት አቶ እንድርያስ፣ በተፈጥሮ የሞቱና በረሃብ የሞቱትን መለየት ያስፈልጋል ብለዋል።

 

የግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስትሩ አቶ አዲሱ ለገሰም የዘጠኝ ወር ሪፖርታቸውን ለፖርላማ ባሰሙበት ወቅት አንድም የሰው ሕይወት በድርቅ ምክንያት አልጠፋም ብለዋል።

 

የግብርና ምርትን በተመለከተ በየዓመቱ ዕድገት እየታየ እንደነበረ በሪፖርታቸው አመልክተው በያዝነው ዓመት ግን ከታቀደው 28 ሜትሪክ ቶን የሠብል እህል ምርት የተገኘው 16 ነጥብ 4 ሜትሪክ ቶን ብቻ ነው። አቶ አዲሱ ለዚህ ያቀረቡት ምክንያት ገበሬው ወደ ተሻለ ገቢ ወደ የሚያስገኙ ምርቶች ፊቱን በማዞሩ መሆኑን ነው።

 

በፓርላማው ውይይት

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሪፖርት እንደሚያመለክተው ዘንድሮ ለማግኘት ከታቀዱ ምርቶች ግባቸውን እንዳልመቱ፤ ሆኖም ከዚህ ለመሸሽ ሲባል ከአምናው የተሻለ ነው እየተባለ መታለፈ የለበትም ያሉት ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ እናስመዘግበዋለን ወይም አስመዝግበናል በምትሉት ዕድገት አልስማማም ብለዋል።

 

ሌላው የፓርላማ አባል አቶ ልደቱ አያሌው፣ የዘንድሮ ምርት ከታቀደው 40 በመቶ የውጭ ንግድ 56 በመቶ ክፍተት እያሳየ እና ተጨማሪ መሬት ወደ እርሻ ገብቶ እንዴት ምርታማ ነን ለማለት ይቻላል? ኢህአዴግ ለ17 ዓመታት የተከተለው ግብርና መር ፖሊሲና 85 በመቶ ህዝብ ገበሬ በሆነበት ሀገር እንዴት የምግብ እጥረት ሊፈጠር ይችላል? ያሉ ሲሆን፤ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በበኩላቸው ሪፖርቱ፣ ለሜካናይዜሽንና ለሠፋፊ መስኖ ልማት ትኩረት ያልሰጠ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህ ፕሮግራም ትኩረት ተሰጥቶት ካልተሠራና ባሀብቶች እንዲሳተፉበት ካልተደረገ መቼም ቢሆን በምግብ ራሣችንን አንችልም ያሉ ሲሆን፣ በተጨማሪም የምርት ጉድለት እየታየ ዋጋ እየጨመረ ዕድገት አለ በግድ ተቀበሉ እየተባልን ነው። ዕድገት ግን የለም። ሀገራችን እያደገች አይደለም ብለዋል። የተራቡና ለችግር የተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ለምክር ቤቱ መቅረብ እንዳለበት፣ የጉዳቱ መጠንና እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ መገለፅ እንዳለበት ተጠቅሷል።

 

አቶ አዲሱ በበኩላቸው የምርት ዕድገት ከዓመት ዓመት እየተሻሻለ እንደመጣ ዘንድሮ ከውጭም ከውስጥም የተከሰተው የዋጋ ንረትና የዝናብ እጥረት በተፈጠረው ችግር ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል። በድርቅ ምክንያት በተፈጠረው አደጋ እስካሁን አንድም ሰው እንዳልሞተ የገለፁት አቶ አዲሱ፣ ተጐጂዎቹ እስካሁን ባለው መረጃ በሴፍቲ ኔት የታቀፉትን ጨምሮ 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብቻ ናቸው። በሱማሌ፣ ከፊል ኦሮሚያና ደቡብ ላይ በተከሰተው ድርቅ የተጐዱ ሕፃናት መኖራቸውን የተናገሩት አቶ አዲሱ ቁጥራቸው እንደሚባለው 6 ሚሊየን አይደለም። በአካባቢው የተወለዱ ሕፃናት ቁጥር ራሱ 6 ሚሊየን አይሞላም ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት በድርቅ ምክንያት የተከሰተውን ችግር ከ2 እስከ 3 ወራት ባለው ጊዜ ወደ ነበረበት እንደሚመልሰው በርግጠኝነት እየተናገረ ነው።

 

ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በድርቅና በችጋር የምትጠቃበት ምክንያት

ሀገራችን ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በድርቅ፣ በረሃብ፣ በችጋር መጠቃትዋን አስመልክቶ የተለያዩ ወገኖች የየራሳቸውን ምክንያት የሚሰነዝሩ መሆኑ ይታወቃል። ብዙዎች የሚስማሙባቸውና ቅድሚያ የሚሰጧቸው ዋንኛ ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው።

 

1ኛ በሀገሪቱ እስካሁን ድረስ መልካም አስተዳደርን (ጉድ ገቨርነንስ) የሚተገብር አገዛዝ ሥልጣን ላይ አለመውጣቱ፣

2ኛ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ እስከዛሬ ድረስ በሀገሪቱ ባለመመለሱ፣ 85 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ ገበሬ የመሬት ባለቤትነት መብት ስለሌው፣

3ኛ በተለይ የኢህአዴግ አገዛዝ ለግብርናው ትኩረት ሰጥቶ የሀገሪቱ ግብርና ላለፉት ሦስት ሺህ ዓመታት በበሬ ከማረስና ከዝናብ ጥገኝነት ተላቅቆ ወደ መስኖና ሜካናይዜሽን እንዲያድግ ምንም ዓይነት ጥረት አለማድረጉ፣

4ኛ እንዲሁም ለአካባቢያዊ ድርቅ መከሰት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያደረገ ያለው የበረሃማነትን ችግር ለመፍታት ጠቃሚነቱ አጠያያቂ ያልሆነውን የችግኝ ተከላ ሂደት በአግባቡ በሀገሪቱ ውስጥ አለመከናወኑ የሚሉት ዋና ምክንያቶች እንደሆኑ ይታወቃል።

 

ኢህአዴግን ጨምሮ ባለፉት አርባ ዓመታት ሀገሪቱን ሲያስተዳድሩ የኖሩት አገዛዞች ኢ-ዴሞክራትና አምባገነን በመሆናቸው ምክንያት ከህዝብና ከሀገር ጥቅም ይልቅ ትኩረታቸው በሥልጣን መቆየታቸው ላይ ብቻ ስለነበርና ስለሆነ፣ ሀገሪቱ በምግብ እህል ለዘለቄታው ራስዋን የምትችልበትን መንገድ ለመቀየስ አለመቻላቸው በብዙኀኑ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆኑ ወገኖች ዘንድ ይታመናል።

 

የአጼው፣ የደርግ እና የኢህአዴግ አገዛዞች በዚህ በድርቁ ጉዳይ ላይ ከሚያመሳስሏቸው በርካታ ነገሮች ውስጥ አንዱ ሦስቱም መንግሥታት በሀገሪቱ ድርቅ ሊከሰት እንደሚችል እየተነገራቸው “ውሸት ነው!” ብለው ሸምጥጠው መካዳቸው እንደሆነ ይታወቃል። በዚህም ምክንያት እርዳታ ለጋሽ ወገኖችና ሀገሮች ድርቁ የከፋ ችግር ከማስከተሉ በፊት ሊታደጉት የሚችሉበትን መንገድ መዝጋታቸው ያመሳስላቸዋል።

 

ድርቅ፣ ረሃብና ችጋሩን አስመልክቶ የተለያዩ የቴሌቭዥን ሚዲያዎች የዘገቡትን እንደሚከተለው በቅደም ተከተል አቅርበነዋል፦

 

ቢቢሲ፣ “ኢትዮጵያውያን ሕፃናት ለችጋር ተጋልጠዋል”

ማክሰኞ ግንቦት 12 ቀን 2000 ዓ.ም. (May 20, 2008)

 

ቢቢሲ፣ “ኢትዮጵያ አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋታል”

ሰኞ ግንቦት 25 ቀን 2000 ዓ.ም. (June 2, 2008)

የኤልዛቤጥ ብለንት ሪፖርት

 

ፍራንስ 24፣ “ኢትዮጵያ ከምግብ ችግር ጋር የምታደርገው ትንቅንቅ”

ሰኞ ግንቦት 25 ቀን 2000 ዓ.ም. (June 2, 2008)

 

 

ፍራንስ 24፣ “ኢትዮጵያ ለረሃብ ተጋለጠች”

ኀሙስ ግንቦት 28 ቀን 2000 ዓ.ም. (June 5, 2008)

 

ቢቢሲ፣ “ኢትዮጵያ ለምግብ እህል እጥረት ተጋለጠች”

ሰኞ ሰኔ 2 ቀን 2000 ዓ.ም. (June 9, 2008)

 

ቢቢሲ፣ “እንግሊዝ ለኢትዮጵያ ዕርዳታ ለመስጠት ቃል ገባች

ሰኞ ሰኔ 2 ቀን 2000 ዓ.ም. (June 9, 2008)

 

ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ፦

ውድ አንባብያን! ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም "ገበሬው ነፃነት ካላገኘ ሁል ጊዜ በኢትዮጵያ ችጋር ይኖራል" ሲሉ በሰጡት ቃለምልልስ መጋቢት 26 ቀን 2000 ዓ.ም. (April 4, 2008) መዘገባችን ይታወሳል። ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ ይህንን ቃለምልልስ ያነቡ ዘንድ እንጋብዛለን። (ቃለምልልሱን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!