“በምርጫ 97 በኢህአዴግ መንግሥት ላይ ጠንካራና ተግባራዊ ተፅዕኖ ባለመወሰዱ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ተመሳሳይ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ተግባራት ባልተደገሙ ነበር” በስዊድን የአንድነት ድጋፍ ማኅበር ተወካዮች

Ethiopia Zare (ረቡዕ ሰኔ 4 ቀን 2000 ዓ.ም. June 11, 2008)፦ ስለዚምባብዌ ተቃዋሚዎች የስዊድን ሊበራል ፓርቲ በፓርላማ ባዘጋጀው ውይይት ላይ ተገኝተው የተወያዩ ሲሆን፣ የአንድነት ፓርቲ ደጋፊዎችም ተገኝተው ምርጫ 97ን ተከትሎ ኢህአዴግ ለወሰዳቸው እርምጃዎች በወቅቱ የስዊድን መንግሥትን ጨምሮ ምዕራባውያን ተግባራዊ ተፅዕኖ ወስደው ቢሆን ኑሮ፤ በዚምባብዌና በሌሎችም የአፍሪካ ሀገራት ተመሳሳይ የምርጫ ማጭበርበር ባልተከተለ ነበር ሲሉ ተቹ።

 

ሰኞ ዕለት ሰኔ 2 ቀን 2000 ዓ.ም. ከቀኑ ሰባት ሰዓት እስከ አስር ሰዓት (13፡00 - 16፡00) በስዊድን ፓርላማ የተደረገውን ይህንኑ ውይይት የመሩት የሊበራል ፓርቲ የፓርላማ ተመራጭና የፓርቲው የውጭ ጉዳይ አፈ-ጉባዔ የሆኑት ብሪጊታ ኡህልሶን ሲሆኑ፣ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፓርቲው መሪ የነበሩትና በአሁኑ ጊዜ የከፍተኛ ትምህርት ቤቶች ሚኒስትር የሆኑት ላርሽ ሊዮንቦሪ ናቸው።

 

በዚህ ውይይት ላይ ከዚምባብዌው ተቃዋሚ ፓርቲ የ”ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ ንቅናቄ” (ኤም.ዲ.ሲ.) ፓርቲ ተወካይና መስራች እንዲሁም የፓርላማ ተመራጭ የሆኑት ዳቪድ ኮልታርት ተገኝተው በዚህ ዓመት ማርች መጨረሻ ላይ በሀገራቸው ተደርጎ የነበረውን ምርጫ ተከትሎ፣ የፕ/ት ሮበርት ሙጋቤ ገዢ ፓርቲ 50 ተቃዋሚችን መግደሉን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቶርቸር መደረጋቸውንና በሺህዎች የሚቆጠሩ ለእስር መዳረጋቸውን አስረድተዋል። በተጨማሪም የፊታችን ሰኔ 27 ቀን 2000 (June 27, 2008) በድጋሚ የሚደረገውን ምርጫ አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

 

በዚህ ውይይት ላይ “በዚምባብዌ ምን መደረግ አለበት?” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ፓናሊስቶች ቀርበው ነበር። እነርሱም በአውሮፓ የኤም.ዲ.ሲ. የአውሮፓ ተጠሪ የሆኑት ሔብሶን ማኩዊሴ፣ ጳጳስ ራግናር ፐርሴኒዩስ ከኡፕሳላ ከተማ፣ ፍሪላንስ ጋዜጠኛና ለረዥም ዓመታት የአፍሪካ ኮሮስፖንዳንት የሬል ኤፕስሉንድ እና ማያ ኦበሪ ከስዊድን አምነስቲ ናቸው።

 

የፕ/ት ሙጋቤ መንግሥት በተቃዋሚዎችና በደጋፊዎቻቸው ላይ የፈጸመውን የ50ሰዎች ግድያ፣ ሰውነታቸው በግርፋት የቆሰሉና የተጎዱ ሰዎች፣ … በፊልም ተደግፎ ለውይይቱ ቀርቦ የነበረ ሲሆን፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሙጋቤ መንግሥት ላይ ሊያሳድር ስለሚገባው ተፅዕኖ በሠፊው ውይይት ተደርጎበታል።

 

በርካታ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በዚህ ውይይት ላይ የተገኙ ሲሆን፣ በስዊድን የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ድጋፍ ማኅበር ሦስት ተወካዮችና የፓርቲው ደጋፊዎች ተገኝተዋል። የድጋፍ ማኅበሩን በመወከል ሊቀመንበሩ አቶ ታምራት አዳሙ፣ ቅንጅትን በመወከል የፓርላማ አባል የነበሩት ዶ/ር ሙሉዓለም ታረቀኝ እና የድጋፍ ማኅበሩ ዋና ፀሐፊ አቶ ስሜነህ ታምራት ተገኝተዋል።

 

በውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ ምርጫ 97ን (2005 እ.ኤ.አ.) ተከትሎ 195 ሰዎች መገደላቸውን፣ የተቃዋሚ መሪዎችና ደጋፊዎች፣ የሰብዓዊ መብት ተማጋቾች፣ የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞች ካለምንም ምክንያት መታሰራቸውን ተከትሎ በወቅቱ በአምባገነኑ የኢህአዴግ መንግሥት ላይ በተለይ ምዕራባውያን ሀገራት ጠንካራና ተግባራዊ ተፅዕኖ አድርገው ቢሆን ኑሮ፤ ዛሬ ይኸው ምርጫን ተከትሎ ተመሳሳይ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ተግባር በሌሎች የአፍሪካ ሀገሮችም ባልተደገመ ነበር በማለት በቦታው የተገኙት በስዊድን የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የድጋፍ ማኅበሩ ተወካዮች አስተያየት አዘል ትችታቸውን አቅርበዋል።

 

የሊበራል ፓርቲው የውጭ ጉዳይ አፈ-ጉባዔ የሆኑት ብሪጊታ የአንድነት ፓርቲ ደጋፊዎች የተናገሩትን አስመልክተው ምላሽ ሲሰጡ፤ ዝም ብለው እንዳልተቀመጡ፣ ለኢህአዴግ መንግሥት በጀት የሚሰጠው ድጋፍ እንዲቀንስ መደረጉን፣ ጉዳዩን ኢትዮጵያ ድረስ ሄዶ አይቶ የሚመጣ ቡድን እንደተላከ፣ ወደፊትም ጉዳዩን በአንክሮ እየተከታተሉ እንደሆነና ከተቃዋሚዎች ጋር አብረው እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል።

 

ጉዳዩን እየተከታተሉ ያሉ ወገኖች በስደት ያሉ ኢትዮጵያውያንና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በየሚኖሩበት ሀገር ላሉ መንግሥታት፣ የመንግሥት ተወካዮች፣ የፓርላማ ተወካዮች፣ ዲፕሎማቶች፣ … በኢትዮጵያ ያለው ገዢ ፓርቲን ኢ-ዴሞክራትነት በተጨባጭ ማስረጃ በማስረዳት፤ መንግሥታቱ ጫና ያሳድሩበት ዘንድ የግድ ይላል፤ ሁሉም በያለበት የድርሻውን፣ ያቅሙንና የችሎታውን ሊወጣ ይገባዋል ሲሉ አስተያየተቸውን ለኢትዮጵያ ዛሬ ሰጥተዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!