የስብሰባ አዳራሽ መከልከል ጉባዔውን እንደማያስቀረው ተገለጸ 

Ethiopia Zare (ዓርብ ሰኔ 6 ቀን 2000 ዓ.ም. June 13, 2008)፦ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ነገ ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2000 ዓ.ም. የሚያደርገው የመሥረታ ጠቅላላ ጉባዔ በስብሰባ አዳራሽ መከልከል ምክንያት እንደማይስተጓጎል ኢንጂንየር ግዛቸው ሺፈራው ገለጹ። ጠቅላላ ጉባዔው በአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ነገ ከሰዓት በኋላ ይደረጋል ብለዋል።

 

ኢንጂንየር ግዛቸው ይህንን የገለጹት ለቅንጅት ሰሜን አሜሪካ የድጋፍ ማኅበር ህዝብ ግንኙነት ሲሆን፣ ጉባዔው በኢምፔሪያል ሆቴል የስብሰባ አዳራሽ ሊካሄድ ታቅዶ እንደነበር ኢንጂንየሩ ገልጸዋል። እንደኢንጂንየሩ ገለጻ ከሆነ ገዥው ፓርቲ "ፈቃድ የላቸውም" የሚል ምክንያት ለሆቴሉ በመስጠት ስብሰባውን በሆቴሉ አዳራሽ እንዳያደርጉ በተዘዋዋሪ መንገድ ጉባዔው እንዳይደረግ መሰናክል ፈጥሯል። ነገር ግን አንድነት ፓርቲ ጉባዔውን እንዳያደርግ በቀጥታ ከገዥው ፓርቲ ምንም ዓይነት ክልከላ እንዳልተደረገበት አክለው ገልጸዋል።

 

በዚህም ምክንያት የፓርቲው አመራር አባላት ዛሬ ማምሻውን አስቸኳይ ስብሰባ አድርገው አንድ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ታውቋል። ይኸውም ነገ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ በሁለት ሰዓት ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የመሥራች ጉባዔው ተሳታፊዎች በሆቴሉ ከተገኙ በኋላ ጉባዔው በአንድነት ጽሕፈት ቤት ከሰዓት በኋላ እንዲደሚካሄድ ማሳወቅና፤ ጉባዔውን በጽ/ቤቱ ማካሄድ ይሆናል። ጉባዔው ነገ ከሰዓት በኋላ እና እሁድ ተካሂዶ፤ እሁድ እንደሚጠናቀቅ ታውቋል።

 

በፓርቲው እምነት የቦታ መከልከሉ የመሥራች ጉባዔውን የሚያደናቅፈው መስሎ እንዳልታየ ኢንጂንየሩ ገልጸው፤ የሠላማዊ ትግሉ የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ በመኾኑ ጉባዔውን ለማደናቀፍ በተደረገው ሙከራ ምክንያት ጉባዔው እንደማይሰናከልና በፓርቲው ጽ/ቤት እንደሚካሄድ አስረድተዋል።

 

በዚህ መሥራች ጉባዔ ላይ ተሳታፊ የሆኑት የየክልሎቹ ተወካዮች አዲስ አበባ መግባታቸውን ገልጸዋል። በዚህ ጉባዔ ላይ ዲፕሎማቶች፣ ታዋቂ የሀገር ሽማግሌዎችና ምሁራን ጥሪ ተደርጎላቸዋል።

 

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዜና የቅንጅት ሰሜን አሜሪካ የድጋፍ ማኅበር ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ከላከው መግለጫ እንደተረዳነው ከሆነ የመሥራች ጉባዔውን አስመልክቶ ነገ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት (9 AM) ጀምሮ በተለያዩ ሀገራት ያሉ የሚዲያ አውታሮች (ራዲዮ፣ ድረ ገጾች፣ ጋዜጠኞች፣ ...) ጉባዔውን ይከታተሉ ዘንድ ጥሪ አስተላልፏል። ጉባዔው በቴሌ ኮንፈረንስም ጭምር የሚካሄድ ሲሆን፣ ከዚሀም በተጨማሪ በፓልቶክ "Special Coverage of Andenet Party Formation" የተሰኘ አዲስ ክፍል ተከፍቶ ጉባዔውን በቀጥታ ለማስተላለፍ ማቀዱን ከመግለጫው ለመረዳት ችለናል።

 

ኢንጂንየር ግዛቸው ከቅንጅት ሰሜን አሜሪካ የድጋፍ ማኅበር ህዝብ ግንኙነት ጋር ያደረጉትን ቃለምልልስ ለማድመጥ ከዚህ በታች የማጫወቻ ቁልፉን (Play Button) ይጫኑ!

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!