"የምርጫ ቦርድ የፈቃድ ደብዳቤ የላችሁም" ፖሊስ

"ስብሰባውን ለማካሄድ ከደህንነት ፈቃድ ተሰጥቷል" ኢምፔሪያል ሆቴል

Ethiopia Zare (ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2000 ዓ.ም. June 14, 2008)፦ ዛሬ ጠዋት ጠቅላላ የፓርቲውን የመሥራች ጉባኤው የጠራው አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ የስብሰባ ቦታው በፖሊስ በመከልከሉ ምክንያት በኢምፔሪያል ሆቴል ይደረግ የነበረው ስብሰባ በድርጅቱ ቢሮ ለማካሄድ መታቀዱ የተገለጸ ሲሆን፣ ዛሬ ጠዋት ኢምፔሪያል ሆቴል በፖሊስ መከበቡን ታማኝ ምንጮቻችን ገለጹ።

 

ትናንት ከሰዓት በኋላ የቀድሞው ቅንጅት ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ስብሰባው የተከለከለበት ምክንያት የገርጂ ፖሊስ አዛዥ በሰጠው ትዕዛዝ መሆኑን በመስማት የጣቢያውን አዛዥ ለማነጋገር ሙከራ ያደረገች ሲሆን፣ ስብሰባው ሕገወጥ በመሆኑ ምክንያት እንደታገደ ገልጾላት፣ ከዚህ በላይ ምንም ማለት እንደማይችልና የክፍለ ከተማው አዛዥ ጋር መነጋገር እንደሚኖርባት ተናግሯል።

 

የቦሌ ክፍለ ከተማ አዛዥ ቢሮ በመሄድ አዛዡን ለማነጋገር ጥረት ያደረገችው ወ/ት ብርቱካን "ፈቃድ ስለሌላችሁ፣ ሕገወጥ ነው" የሚል ምላሽ እንደተሰጣት ለማወቅ ተችሏል። ወ/ት ብርቱካንም በሕጉ መሠረት ፈቃድ የሚያስፈልገው ለሠላማዊ ሰልፍ እና ከቤት ውስጥ ለሚደረግ ስብሰባ መሆኑን ለማስረዳት ጥረት ያደረገች ቢሆንም፤ አዛዡ የግድ ፈቃድ እንደሚያስፈልግ ነግሯታል።

 

ወ/ት ብርቱካንም ለቤት ውስጥ ስብሰባ ፈቃድ ከመስተዳድሩ እንደማያስፈልግ አስረድታዋለች። አዛዡም የምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ስለሌላችሁ ስብሰባው ሕገወጥ ነው በማለት መልስ የሰጣት ሲሆን፤ "ሠርግ እንኳን ፈቃድ ይጠይቃል፤ ያለፈቃድ እንዴት ስብሰባ ታደርጋላችሁ" ሲል መመለሱ ታውቋል።

 

በተያያዘም የኢምፔሪያል ሆቴል አስተዳደር ማናቸውም ስብሰባ ሲካሄድ እንደሚያደርገው ሁሉ ከደህንነት ቢሮ ጋር በመነጋገር ስብሰባውን ያሳወቀ ሲሆን፣ የደህንነት ቢሮውም ስብሰባው መካሄድ ይችላል ሲል ፈቃድ መስጠቱን ለመረዳት ችለናል።

 

"አንድነት ፓርቲ እልህ አስጨራሽ የፖለቲካ ትንቅንቅ ውስጥ ቢሆንም የወያኔን አገዛዝ ማን አለብኝነት ከማጋለጣቸውም በላይ ወያኔ የፖለቲካ ጭንቀት ውስጥ መግባቱን ለኅብረተሰቡና ለዓለም ማኅበረሰብ የሚያጋልጡበት ሂደት ውስጥ መሆናቸውን ያሳያል። ስለሆነም በሂደቱ እስከመጨረሻው መግፋትና የአገዛዙን ማንነት እርቃኑን ማውጣት ይገባል" ሲሉ የዘወትር ተባባሪያችን የፖለቲካ ተንታኝ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

 

ውድ አንባብያን፦ ሄደቱን እየተከታተልን ለማቅረብ እንሞክራለን።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!