"ሥራ አስፈታናችሁ፤ እናንተም ሂዱ እኛም መሄዳችን ነው" ፕ/ር መስፍን

Ethiopia Zare (ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2000 ዓ.ም. June 14, 2008)፦ በኢምፔሪያል ሆቴል አካባቢ ብዛት ያለው የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ጉባዔተኞች የተነኙ ሲሆን፣ ብዛት ያላቸው ወጣቶችም የድርጅቱ መስራች በመሆን የተገኙ መሆናቸውን አረጋግጠናል። ወጣቶቹ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የነበሩና በተለያዩ ቦታዎች በኃላፊነት የሚሠሩ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ምንጮቻችን ገልጸዋል።

 

ዛሬ በኢምፔሪያል ሆቴል ይካሄድ የነበረው ስብሰባ በፖሊስ ኃይሎች ከታገደ በኋላ ስብሰባው ላይ ለመካፈል የመጡት ተወካዮች ስብሰባው ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ (በኢትዮጵያ አቆጣጠር) በአንድነት ቢሮ እንደሚደረግ በወ/ት ብርቱካን ከተገለጸላቸው በኋላ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ለአራት ሰዓት ሃያ ጉዳይ (9:40 AM) አካባቢ ተሰብሳቢዎቹን በሁለት አውቶቡስና በተለያዩ የግል መኪናዎች በመጫን ወደ ዋና ቢሮ የተወሰዱ መሆኑ ታውቋል።

 

ተሰብሳቢዎቹ አራቱም የመግቢያ በር በፖሊስ ከታጠረበት የኢምፔርያል ሆቴል ሲወጡም ለፓሊሶቹ "ሥራ አስፈታናችሁ፤ እናንተም ሂዱ እኛም መሄዳችን ነው" በማለት አንጋፋው የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና የቅንጅት ብሎም የአንድነት መስራች ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ለፖሊሶቹ በመንገር ለጥበቃ የተሰበሰቡትን ፖሊሶች በማሳቅ የተለዩ ሲሆን፣ በርካታ ፖሊሶችም ለፕ/ሩ ያላቸውን አክብሮት ማሳየታቸውን ምንጮቻችን ከስፍራው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

 

በአንድነት ጽሕፈት ቤት የድንኳን ተከላ እየተካሄደ ሲሆን፣ ስብሰባውም በቢሮ ግቢ ውስጥ የሚካሄድ መሆኑን ለመረዳት ችለናል።

 

"ይህ ስብሰባ ስኬታማ እንዲሆን በየትኛውም መልኩ ሀገራቸው ውስጥ በመሆን የጨካኙን አገዛዝ እኩይ ሥራ በተግባር እየተፈታተኑ ያሉ ብርቅዬ ልጆች ገድል ዛሬ እየተሠራ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለኝም። ይህ ሂደት ደግሞ የተቃዋሚው ጎራ በቃኝ፣ መረረኝ በማለት ወያኔ ወዳዘጋጀው ወጥመድ ውስጥ እንዲገባ ሆን ተብሎ የሚሸረብ ሴራ ነው" የሚሉ አስተያየት ሰጭዎች፤ "የአንድነት ፓርቲ ጉባዔተኞች የሚያካሂዱት እልህ አስጨራሽ ትግል በውጭ ሀገራት የሚኖሩ የዴሞክራሲ ደጋፊዎችን ሙሉ ትብብር የሚጠይቅ ሲሆን፣ የድርጅቱን ጠቅላላ ውሳኔ በመደገፍ አብሯቸው መቆም ይገባዋል እንጅ፤ ወያኔ በሚያደርገው እንዲህ አይነት ዓይን ያወጣ እኩይነት ላይ በሚፈጠር ጥላቻ አገዛዙ ወዳዘጋጀው ወጥመድ ውስጥ እንዲገቡ መገፋፋት የለበትም" ሲሉ አስተያየታቸውን አክለዋል።

 

ማሳሰቢያ

 

አስተያየት በመስጠት የሚተባበሩን የፖለቲካ ተንታኝ ስብሰባው እስኪጠናቀቅ ከጎናችን በመሆን ለሚያደርጉልን ትብብር እያመሰገንን፣ ስብሰባው የሚደርስበትን ሂደት በመከታተልና በፍቶግራፍ በማስደገፍ የምናቀርብ መሆኑን እንገልጻለን።

 

ኢትዮጵያ ዛሬ

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!