Andenet General Assembly 20080614

Ethiopia Zare (ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2000 ዓ.ም. June 14, 2008)፦ በዛሬው ዕለት ሁለት ጊዜ የኢህአዴግ ፖሊሶች አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊያደርገው አቅዶት የነበረውን የመሥራች ጉባዔውን ለማጨናገፍ ያደረጉት ሙከራ የተሳካላቸው ቢሆንም፤ ጉባዔውን እስከመጨረሻው ሊያስቀሩት እንደማይችሉ ከአዲስ አበባ ያሰባሰብናቸው መረጃዎች ጠቁመዋል።

 

ፖሊስ በዛሬው ዕለት ጠዋት በኢምፔሪያል ሆቴል እንዳይካሄድ ያገደውን ጉባዔ ከሰዓት በኋላም በአንድነት ጽ/ቤት ቅጽር ግቢ ውስጥ በጉባዔው ለመሳተፍ የተሰበሰቡትን መሥራቾች “የስብሰባ ፈቃድ የላችሁም” በሚል ስብሰባው እንዳይካሄድ ማድረጉን እየተከታተልን መዘገባችን ይታወቃል።

 

በመሥራች ጉባዔው ለመሳተፍ ከተለያዩ ክልልሎች የመጡትን ተሰብሳቢዎች ጨምሮ ነዋሪነታቸው በአዲስ ከሆኑት ጋር በድምሩ ወደ 400 የሚሆኑ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ አብዛኖቹ የመሥራች ጉባዔው ተሳታፊዎች ወጣቶች ሲሆኑ፤ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የሴቶች ተሳትፎ ተበራክቶ ታይቷል። ወጣቶቹ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስና በተለያዩ መስኮች ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው የሚገኙበት ሲሆን፣ ፓይለቶችም ጭምር እንዳሉበት ለማረጋገጥ ችለናል።

 

ከእነዚህም ሌላ ፓርቲው በተከታታይ ሲያደርጋቸው በነበሩት ስብሰባዎች ላይ ሳይገኙ የቀሩ ሁሉ በዛሬው ዕለት የተገኙ ሲሆን፣ የቀድሞ የቅንጅት መሪዎች ከእስር ከተፈቱ በኋላ በኢንጂንየር ኃይሉንና በእነ ወ/ት ብርቱካን የሚመሩትን ቡድኖች ሲያሸማግሉ የነበሩ ወጣቶችም እንደተገኙ ለመረዳት ችለናል። በስፍራው የተገኙት ወገኖች ከተጠበቀው በላይ ሰዎች መገኘታቸውን ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልጸው፤ ለአንድነት ፓርቲ ምሥረታ ብዙዎች ቀና አመለካከት እንዳላቸውና በፓርቲው ላይ ያላቸውን ጠንካራ እምነት ያሳያል ሲሉ ያላቸውን አስተያየት ሰጥተዋል።

 

Andenet party general assebmbly, 20080614, Addis Abeba

 

ጉባዔው በኢምፔሪያል ሆቴል የመሰብሰቢያ አዳራሽ እንደማይካሄድ ከታወቀ በኋላ በተለይ በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑ የመሥራች ጉባዔው ተሳታፊ የሆኑ ወጣቶች በሚያስገርም ሁኔታና ፍጥነት ጉባዔው በፓርቲው ጽሕፈት ቤት ቅጽር ግቢ ውስጥ በተሳካ ሁኔታ ይካሄድ ዘንድ ያስፈልጋሉ ተብለው የታሰቡ ቁሳቁሶችን ወንበር፣ ድንኳን፣ ስክሪን፣ … በመከራየትና አስተካክሎ ቦታ ቦታቸውን ለማስያዝ ሲያደርጉ የነበረውን ጥረት መመልከቱ የሚያስገርም እንደነበር ለመረዳት ችለናል።

 

እነዚህ ወጣቶች ጉባዔው በዛሬው ዕለት ይደረግ ዘንድ የበኩላቸውን ድርሻ የተወጡና በሚገርም ሁኔታ ይሯሯጡ እንደነበር በወቅቱ በስፍራው ከነበሩ ገለልተኛ ወገኞች ተረድተናል።

 

የፓርቲው መሥራች ተሰብሳቢዎች በዛሬው ዕለት በገዥው ፓርቲ ከፍተኛ ጫና የደረሰባቸው ቢሆንም፤ ጉባዔው እንዲካሄድ ካላቸው ጽኑ ፍላጎት አንጻር እስከመጨረሻው ድረስ ጫናውን ተቋቁመው መንፈሰ ጠንካራነታቸውን በጨዋ ኢትዮጵያዊ መልክ ማሳየታቸውን ጉዳዩን ከተከታተሉ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ለመረዳት ችለናል።

 

ለፓርቲው ቅርብ ከሆኑ ምንጮቻችን እንደተረዳነው ከሆነ ገዥው ፓርቲ የፖሊስ ኃይልን በተዘዋዋሪ መንገድ በመጠቀም የዛሬውን ጉባዔ ለማሰናከል ያደረገው ጥረት ለጊዜው የተሳካለት ቢሆንም፤ ፓርቲው ሰኞ ዕለት ለሚመለከታቸው አካላት በሙሉ፤ በተለይም ከአዲስ አበባ መስተዳድር እና ክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የስብሰባ ፈቃድ ለማግኘት የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግ ለማወቅ ችለናል።

 

Prof. Mesfin ´W/Mariam

አንድነት ፓርቲ ሠላማዊ ትግል ብቸኛ አማራጭ ነው ብሎ የሚያምን ከመሆኑ አንጻር ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ እገዛበታለሁ በሚለው በራሱ ሕገ መንግሥት ሕግጋት በመጠቀም የፓርቲውን እውቅና ለማረጋገጥ ጥረት እንደሚያደርግ ለፓርቲው ቅርበት ካላቸው ወገኖች ከደረሱን መረጃዎች ለመረዳት ችለናል።

 

በዚህም መሠረት ሕገ መንግሥቱ በሚደነግገው መሠረት አንድ ፓርቲ ወይንም ወገን ህዝባዊ ስብሰባ፣ ሠላማዊ ሰልፍ፣ … ለማድረግ ለክልሉ መስተዳድርና ለፖሊስ ማመልከቻ ባቀረበ በ48 ሰዓታት (ሁለት ቀናት) ውስጥ ማመልከቻ ከቀረበለት የመንግሥት አካል ምላሽ ካላገኘ ስብሰባውን ማካሄድ እንደሚቻል ይፈቅዳል። በመሆኑም ተነገ ወዲያ የፊታችን ሰኞ የፈቃድ ማመልከቻው አስፈላጊ በሆኑት የመንግሥት አካላት የሚገባ ሲሆን፤ የመንግሥት አካላቱ ፈቃድ የማይሰጡ ቢሆን እንኳን፤ ጉባዔው ቢዘገይ እስከ ረቡዕ ሰኔ 11 ቀን 2000 ዓ.ም. (ጁን 18 ቀን 2008 እ.ኤ.አ.) እንደሆነ ለፓርቲው ቅርብ የሆኑት የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገልጸዋል።

 

በተለይም ከክልል ከተሞች የመጡት የጉባዔው ተሳታፊዎች ምንም አይነት ተስፋ መቁረጥ የማይታይባቸው እንደነበረና፤ ይህ የገዥው ፓርቲ ጫና የበለጠ አቀራርቧቸውና አጠንክሯቸው እንደነበር ለፓርቲው ቅርበት ያላቸው ወገኖች ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ በመገረም ገልጸዋል።

 

በዚህ ጉዳይ ላይ ዘወትር አስተያየት የሚሰጡን የፖለቲካ ተንታኞች በበኩላቸው ደግሞ ሠላማዊ ትግል ከፍተኛ መስዋዕትነትን የሚጠይቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ አንድነት ፓርቲ የመረጠው የትግል ስልት ሠላማዊ የትግል ስልት እንደመሆኑ መጠንና ከወያኔ/ኢህአዴግ ባህሪ አንጻር የአንድነት ፓርቲን አባላትና አመራሮች ብቻ ሳይሆን በተለይም ደጋፊዎቻቸውን በቀላሉ ተስፋ ሊያስቆርጥ የሚችሉ ክስተቶች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

 

Andenet General Assembly, 20080614, Addis Abeba

 

እነኚሁ ለኢትዮጵያ ዛሬ ቅርብ የሆኑ የፖለቲካ ተንታኞች “የወያኔ/ኢህአዴግ የመጀመሪያ ተግባሩና ዓላማው በውጭ ሀገራት በስደት ያለውን ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራ ከአንድነት ፓርቲ እና ሠላማዊ ትግል ያዋጣል ከሚሉት ፓርቲዎች ጋር ማለያየት ነው” በማለት ያስረዳሉ። ይህንንም ሲያብራሩ፤ “በተለይ ዲያስፖራው የሚኖርባቸውን ሀገራት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ከሀገሩ ኢትዮጵያ ጋር በማወዳደርና በሚኖርባቸው ሀገራት የሚያየው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በገዛ ሀገሩ እንዲሰፍኑ ከመሻቱ ጽኑ ፍላጎት አንጻር ጋር በተያያዘ መልኩ በቀላሉ ተስፋ የሚቆርጥበትን መንገድ የወያኔ/ኢህአዴግ ገዢ ፓርቲ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ እያካሄደ ነው” ይላሉ፤ እነኚሁ የፖለቲካ ተንታኞች።

 

ኢህአዴግ እገዛበታለሁ የሚለውን ሕገ መንግሥት ራሱ እየጣሰ መገኘቱን ከመቼውን ጊዜ በላይ እያሳየ መሆኑን የገለጹት እነኝሁ የፖለቲካ ተንታኞች በሀገራችን ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይሰፍን ዘንድ የሚታገል፣ ዜጋ ነኝ እና ያገባኛል የሚል ወገን በያለበት የሚችለውን ያህል ተስፋ ሳይቆርጥና የወያኔ/ኢህአዴግ ገዢ ፓርቲ፣ በየዕለቱ የሀገሪቱን ህዝብ፣ ተቀናቃኝ እና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎቹን ተስፋ ለማስቆረጥ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ከመቼውም የበለጠ መታገል እንዳለበትና ጊዜው የሚጠይቀው ቀላል የመስዋዕትነት ጥያቄ ሊሆን እንደሚገባው አስምረውበት ማለፍ እንደሚፈልጉ የፖለቲካ ተንታኞቹ ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ገልጸዋል።

 

እነኚሁ ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ቅርብት ያላቸው የፖለቲካ ተንታኞች አክለው እንዳስረዱት ከሆነ፤ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰብ መብቱን ለማስከበር መክፈል የሚገባውን መስዋዕትነት መክፈል ያለበት ወቅት ቢኖር አሁን መሆኑን ገልጸው፤ ኃላፊነቱ የሁሉም ኢትዮጵያዊ መሆኑን አስረድተዋል። አክለውም  በሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር መከፈል ያለበት መስዋዕትነት ትዕግስት አስጨራሽ ሊሆን እንደሚችል ሳይገልጹ አላለፉም።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!