ልዩ ጥንቅር - በአንድነት ፓርቲ ምስረታ ላይ

የመሪዎቹን አጭር ታሪክ/Profile ይዘናል

Andenet Leaders

Ethiopia Zare (ዓርብ ሰኔ 13 ቀን 2000 ዓ.ም. June 20, 2008)፦ ሰኔ 7 ቀን 2000 ዓ.ም. በኢምፔሪያል ሆቴል ጠቅላላ ጉባዔ በማድረግ አመራር ለመምረጥ በዝግጅት ላይ የነበረው አንድነት ፖርቲ በዕለቱ ባይሳካለትም ከትናንት በስቲያ ረቡዕ ሰኔ 11 ቀን 2000 ዓ.ም. በተለምዶ ሪቼ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው የድርጅቱ ጽ/ቤት በድንኳን ውስጥ ጠቅላላ ጉባዔ ተደርጓል።

 

ቅዳሜ ጠዋት በኢምፔሪያል ሆቴል የተገኙት ወጣቶች የመስከረም 14ቱን የግሎባል ሆቴል የቅንጅት ውህደት ትውስታ በትንሹ ያጭራል።

 

ለፓርቲው ምስረታ ሰዎች እንደሚገኙ ተገምቷል። በዛ ድንኳን ውስጥ ግን ከ300 ሰው በላይ ፖርቲ ለመመስረት ሲል ይሰባሰባል ብሎ የገመተ አልነበረም።

 

ዕረቡ ሰኔ 11 ቀን ጠበብ ባለው የድርጅቱ ግቢ ሙሉ በመሉ ድንኳን ተጥሎ በሩ ላይ አነስተኛ ባንዲራ ተሰቅሏል።

 

ከተለያዩ ክልሎች የመጡትን ጨምሮ 300 የጠቅላላ ጉባዔ አባላት የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፖርቲ ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብን አፅድቆ ስድስት ሰዓታት የፈጀ ምርጫ አድርጎ አመራሮቹን መረጠ።

 

ተመራጮቹ በመጀመሪያ 105 ተጠቁመው በነጨረሻ ወደ 60 የብሔራዊ ምክር ቤት አባልነት አልፈዋል። ብሔራዊ ምክር ቤቱ ተሰብስብቦ ከነዚህ ውስጥ 18 የሥራ አስፈፃሚ እና ስድስት አመራር ተመርጧል።

 

ምርጫው ተጠናቆ ውጤቱ የተነገረው ከምሽቱ 2ሰዓት ከ30 ደቂቃ ላይ ሲሆን፤ የፖርቲው ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ም/ሊቀመንበርና የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው፣ ም/ሊቀመንበርና የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ዶ/ር ያቆብ ኃ/ማርያም ፣ ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ ም/ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ አቶ ተመስገን ዘውዴ ም/ሊቀመንበርና የፋይናንስ ጉዳይ ኃላፊ እንዲሁም አቶ አሥራት ጣሴ የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ ሆነው ተመርጠዋል። ከውጤቱ በኋላ ተመራጮቹ እጅ ለእጅ ተያይዘው ለፓርቲው ያዘጋጁትን መዝሙር ዘምረዋል።

 

ከአመራር አባላቱ ጋር ተጨማሪ ሆነው የተመረጡት የሥራ አስፈፃሚ አባላት፤ አቶ አስቻለው ከተማ፣ አቶ እንዳልካቸው ሞላ፣ ወ/ሮ ሸዋዬ ኪሮስ፣ አቶ ክፍሌ ጥግነህ፣ አቶ አክሉ ግርግሬ፣ አቶ የኔነህ ሙላተ፣ አቶ ታምራት ታረቀኝ፣ አቶ አምሃ ዳኜ፣ ወ/ሮ ላቀች ደገፉ፣ አቶ መስፍን ጌታቸው፣ አቶ ብሩ ብርመጂ እና አቶ ፈጠነ ተሾመ ናቸው።

 

በብሔራዊ ምክር ቤቱ ወስጥ 19ኙ የቅንጅት የቀድሞ የላዕላይ ምክር ቤት አባላት፣ 16ቱ የተሟሉ አባላት ሲሆኑ፣ የተቀሩት 25 አባላት በምርጫ የተጠቃለሉ ናቸው።

 

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ:-

W/t Birtukan34 ዓመት ሆኖአቸዋል። በአዲስ አበባ በፈረንሳይ ለጋሲዮን ተወልደው፣ ሚያዝያ 23 ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በየካቲት 12 ትምህርት ቤት የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ጨርሰዋል። በአዲስ አበባ ዮኒቨርስቲም በሕግ የትምህርት ዘርፍ በዲግሪ ተመርቀዋል።

 

በፊዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በረዳት ዳኝነት ከዛም በዳኝነት አገልግለዋል። በግል የጥብቅና ፈቃድ በማውጣት ለተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች የጥብቅና ሥራ ሲሰሩ ቆይተዋል።

 

የፖለቲካ ተሳትፎ

በ1992 ዓ.ም. ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግል ተወዳዳሪ በመሆን በእጩነት ቀርበው የነበረ ሲሆን በወቅቱ ሳይሳካላቸው ቀርቷል። በ1997 ዓ.ም. ቀስተ ደመናን ተቀላቅለው ከዚያም ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፖርቲ ውህደት ሲፈጥር በተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበርነት ተመርጠው ብዙም ሳይቆዩ ወደ እስር አምርተዋል። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ አዲስ ለተቋቋመው የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፖርቲ ሊቀመንበር በመሆን ተመርጠዋል።

 

ወ/ት ብርቱካን “ያለፍንበት ውጣ ውረድ እና በህዝብ ላይ የተፈጠረው ስሜት አሳዛኝ ነው። ኀዘኑ እኛንም ጎድቶናል። ግን መሠረታዊ ችግሩን አይተንና አውቀነው ለመማር ዕድል አግኝተናል። ይህ ሁሉ ውጣ ውረድ ከዚህ በኋላ የምንሰራውን ነገር ቀላል ያደርግልናል። ያለፈው ሁሉ ቁጭት አሳድሮብናል። ፓርቲያችን ግልጽ፣ ተጠያቂነትን የተላበሰ አሰራር ይዞ፤ ከምንም በላይ በድርጅቱ ፖለቲካዊ እምነቶች ላይ ክርክርና ውይይት በማድረግ መግባባትን ፈጥረንና የፖለቲካ አስተሳሰብ እንዲኖር በማድረግ የፖርቲውን የውስጥ አሰራሮች አጠንክረን የመግባባት ባህል እንዲዳብር እናደርጋለን።

 

“በሁሉም አባላት አስተሳሰብ ውስጥ የድርጅቱን ትልቁን ዓላማ፣ (በኢትዮጵያን የዲሞክራሲያዊ ስርዓትን መገንባት) በሚመለከለት በቂ ግንዛቤ እንዲጨብጡ የሚያደርግ እና ሁሉም አባል ስለዓላማው የሚያስብበት ፖርቲ እንዲሆን ጠንክረን እንሰራለን።” ሲሉ ሃሳባቸውን ገልፀውልናል። የፖርቲው ሕጋዊነት ከተረጋገጠም በኋላ የመጀመሪያው ሥራቸው ፖርቲውን ማጠንከር እንደሆነ ተናግረዋል።

 

ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው

Eng. Gizachewሐምሌ 13 ቀን 1942 ዓ.ም. ጅሩ በሚባል አካባቢ የተወለዱት ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው የአንድነት ፖርቲ ም/ሊቀመንበርና የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ሆነው ተመርጠዋል።

 

አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በተወለዱበት አካባቢ ጅሁር ት/ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በደብረ ብርሃን ኃይለማርያም ማሞ ትምህርት ቤት፣ ከዛም በባህር ዳር ቴክኒካል ኢንስቲትዩት ከተማሩ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኬሚካል ኢንጂነሪንግ እስከ ሦስተኛ ዓመት ተምረው በዝውውር ጋና ዩኒቨርስቲ ኦፍ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ይዘዋል።

 

በስኳር ኮርፖሬሽን በምርት ሥራ አስኪያጅነት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ከተቋቋመ ጀምሮ ደግሞ እስከ ምክትል ኮሚሽነር ሆነው ሰርተዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቴክኖሎጂ ፋልቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት እየሰሩ ይገኛሉ።

 

የፖለቲካ ተሳትፎአቸው

በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ንቅናቄ መሪ፣ በመኢአድ እና በቅንጅት የሥራ አስፈፃሚ ሆነው ላለፉት 10 ዓመታት በፖለቲካ ተሳትፈዋል። በምርጫ 97 ከትግል አጋሮቻቸው ጋር በመሆን ለ20 ወራት በቃሊቲ እስር ቤት ታስረው ተፈተዋል።

 

ኢ/ር ግዛቸው አንድነት በፓርቲ ግልጽ የሆነ አሰራርን እንደሚከትል፣ በአገሪቱ ዲሞክራሲያዊ የሆነ ሥርዓት እንዲሰፍን ፓርቲያቸው ካለፉት ስህተቶቹ ተምሮ ጠንክሮ እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል።

 

ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም

Dr. Yakobe የአንድነት ፖርቲ ም/ሊቀመንበርና የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ሆነው ተመርጠዋል።ምርጫ ቦርድ ለፖለቲካው ህጋዊ ሰርተፍኬት ከሰጠበት ጊዜ ጀምሮም በዚህ ስልጣናቸው ፖርቲውን ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ያገለግሉታል።

 

ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ እምደብር ቀበሌ ነው የተወለዱት። 64 ዓመታቸውን የደፈኑት ዶ/ር ያዕቆብ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የተወለዱበት ከጨረሱ በኋላ በጄኔራል ዊንጌት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታተሉ።

 

ሐረር ሚሊቴሪ አካዳሚ ለአንድ ዓመት ቆይተው ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አመሩ። ከዩኒቨርስተው በሕግ ትምህርት በዲግሪ ተመረቁ። ከዛም ከሎስ አንጀለስ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ ማስተርሳቸውን ወሰዱ። ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሱም አቶ አባቢያ አበጀባር ከሚባል ጓደኛቸው ጋር የሕግ ቢሮ ከፍተው ለአራት ዓመት እንደሰሩ አብዮቱ ፈነዳ። ከሦስት ጓደኞቻቸው ጋር "ይገደሉ" የሚል ትዕዛዝ መውጣቱን ሲሰሙ ጠፍተው ወደ ኬንያ ያመራሉ። በኬንያ አንድ ዓመት ከቆዩ በኋላ የፒ.ኤች.ዲ. ስኮላር ሺፕ አግኝተው ወደ አሜሪካን ያቀናሉ። ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ አሜሪካን አገር በሚገኝ አንድ ዩኒቨርስቲ ለረጅም ዓመት ካስተማሩ በኋላ የተባበሩት መንግሥታት የሩዋንዳ ዓለም አቀፍ ዓቃቤ ሕግ ሆነው በመቀጠር ሰርተዋል።

 

ከዚያም ወደ ዩኒቨርስቲው ተመልሰው በተባባሪ ፕሮፌሰርነት ከሰሩ በኋላ በድጋሚ ለሦስት ዓመታት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የሕግ አማካሪ ሆነው በካሜሮን ናይጄሪያ በተፈጠረው ረብሻ የወሰን ውዝግብ ለመፍታት በተቋቋመው የጋራ ኮሚሽን ከፍተኛ የሕግ አማካሪ ሆነው ለሁለት ዓመት ከሰሩ በኋላ ጠ/ሚኒስትር መለስ "በ1997 ዓ.ም. ነፃ ምርጫ ይደረጋል" በማለታቸው የተባበሩት መንግሥታት ያላቸውን ሥራ ጥለው ተሰናብተው ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን ተናግረዋል።

 

ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም የአንድነት ፖርቲ ም/ሊቀመንበርና የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ሆነው ተመርጠዋል። ምርጫ ቦርድ ለፖለቲካው ሕጋዊ ሰርተፍኬት ከሰጠበት ጊዜ ጀምሮም በዚህ ስልጣናቸው ፖርቲውን ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ያገለግሉታል።

 

ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ

Dr. Hailuትውልዳቸው ማይጨው ከተማ ነው። አንደኛ ደረጃን እዛው ካጠናቀቁ በኋላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አዲስ አበባ ኮኮበ ፅባህ ተምረዋል። በኮተቤ መምህራን ማሰልጠኛ በአንደኛ ደረጃ መምህርነት ሰልጥነው በኮረምና ደሴ በመምህርነት አገልግለዋል።

 

አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገብተው ሁለት ዓመት እንደተማሩ በአሜሪካን አገር ኒዮርክ ዩኒቨርስቲ ለመጀመሪያ ዲግሪ፤ ዋሽንግተን ጆርጅ ታውን ዩኒቨርስቲ ደግሞ ማስተርሳቸውን ከጨረሱ በኋላ በባህርዳር ፖሊ ቴክኒክ ኢንስቲትዩት ሦስት ዓመት አስተምረው ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተዛውረው ለአንድ ዓመት አስተምረዋል።

 

ከዛም ወደ አሜሪካ ተመልሰው የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ይዘዋል። በዛው ዩኒቨርስቲ ማስተማር እንደጀመሩ አብዮቱ በመፈንዳቱ የማስተማሩን ቦታ መልቀቂያ አስገብተው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እንግሊዘኛ ቋንቋና ስነጽሁፍ ማስተማር ጀመሩ የቋንቋና ስነ-ፅሁፍ ዲፖርትመንትም ዲን ሆነው አገለገሉ።

 

ኮ/ል መንግሥቱ ኃ/ማርያም ሪፐፕሊክ ለማቋቋም እያሰብኩ ነው ብሎ "ኢሠፓኮ" መሰረተ ያኔ ዩኒቨርስቲን ለቀው የኢሠፓኮ የብሔረሰብ ጉዳዮች መምሪያ ም/ኃላፊና የሸንጎ አባል ሆነው ለዘጠኝ ዓመት እዛው ቆዩ።

 

ኢህአዴግ ሲገባ ከኢትዮጵያ ውጭ የነበሩ ቢሆንም ሲመጡ አመራር የነበራችሁ እየመጣችሁ አመልክቱ ሲባል ሄደው አመለከቱ። ለአምስት ሣምንታት ታስረው ተፈቱ። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የትርፍ ሰዓት መምህር የነበሩ ሲሆን፣ በ1989 ዓ.ም. ከ40 የዩኒቨርሲቲ መምህራን ጋር አብረው ተባበሩ።

 

የፖለቲካ ተሳትፎአቸው

የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ማኅበር የዋሽንግተን ቻፕተር ሊቀመንበር የነበሩት ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ ከፖለቲካው ወጥተው ማስተማር ላይ ቢቀጥሉም በመጨረሻ ኢዴአፖ- መድህንን ተቀላቀሉ። ም/ሊቀመንበር ሆነው እየሰሩ ፖርቲው ቅንጅትን በተቀላቀለበት ወቅት እዛ ቀሩ። ለ20 ወራት ለእስርም ተዳረጉ።

 

ዶ/ር ኃይሉ የ72 ዓመት አዛውንት ሆነዋል። አንዲት ሴትና አንድ ወንድ ልጅ አላቸው። ለአንድነት ፓርቲ ም/ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆነው ተመርጠዋል።

 

"ህዝቡ ከቅንጅት ሲጠብቅ የነበረውን ይጠብቅ። አንድነት ፖርቲ ለውጥ ለማምጣትና ህዝቡን የሥልጣን ባለቤት ለማድረግ ዲሞክራሲና ነፃነት በሀገሪቷ ላይ እንዲሰፍን ለማድረግ እንሠራለን” ብለዋል።

 

የፖርቲው ጥንካሬ ሊለካ የሚገባው በግለሰቦች አይደለም። በርግጥ ግለሰቦች በፖርቲው ውስጥ የማይናቅ አስተዋጽኦ አላቸው። ግን ሁሌም አዳዲስና ጠንካራ መሪዎች ይፈጠራሉ። አንድነት ፖርቲም ካለፉት ስህተቶች ተምሮ ልዩነቶቹን አቻችሎ ጠንካራ ፖርቲ ይሆናል ብለው ተስፋቸውን ገልፀዋል።

 

ሁኔታዎች አመቺ ላይሆኑ ይችላሉ። ይህ ደግሞ የትግል አንዱ ገጽታ ነው። ሁኔታዎች አስቸጋሪ በሆኑ ቦታዎች ሁሉ የመንፈስ ጥንካሬ ይጠይቃል፣ ለውጥ ለማምጣት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢፈጠሩ እንኳን ጠንካራ ፖርቲ እንመሰርታለን ብለዋል።

 

አቶ ተመስገን ዘውዴ

Ato Temesgenኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የሚያይ ሰው ፖለቲከኛ መሆናቸውን ያውቃል። ፖርላማ በገቡ ቁጥር በተለይ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ባሉበት ወቅት አንድ ነገርም ቢሆን ጣል ይደረግባቸዋል።

 

አቶ ተመስገን ዘውዴ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ጋሞ ጐፋ ዞን በሳውለ ቡልቂ አካባቢ በ1944 ዓ.ም. ተወለዱ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአካባቢው በሚገኝ ትምህርት ቤት ከተከታተሉ በኋላ ንግድ ሥራ ትምህርት ቤት ለአራት ዓመት መደበኛ ስልጠና ወሰዱ። ውጤታቸው ጥሩ ስለነበር በእዛው ት/ቤት በመምህርነት አገለገሉ።

 

ከእዛም ባገኙት ስኮላር ሺኘ አሜሪካን አገር "ፖልኩዊን" በተባለ ዩኒቨርሲቲ ለአራት ዓመት በንግድ ሥራ አስተዳደር የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ይዘዋል።

 

ሂውስተን በሚገኝ የዘይት ፈላጊ ኩባንያ ውስጥ ለስምንት ዓመታት ከሰሩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በአድማስ ዩኒቨርስቲ ለኮሌጅ በረዳት ካምፖስ ዲንነት እና በመምህርነት በማገልገል ላይ እያሉ ምርጫ 97 ሲመጣ ሥራቸውን ጥለው ወደ ፖለቲካው መግባታቸው አስረድተዋል።

 

በቀበሌ 05 መርካቶ በቅንጅት ስም ተወዳድረው አሸናፊ በመሆናቸው ፖርላማውን ተቀላቅለዋል። አቶ ተመስገን የቅንጅት አመራሮች ከእስር ሲፈቱ እነ ብርቱካን ሚደቅሳን ተቀላቀሉ። አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፖርቲ ለመመስረት በጋራ መሥራት ጀምረዋል። ለዚህም ምስረታ የፖርቲው ምክትል ሊቀመንበርና የፋይናንስ ጉዳይ ኃላፊ ሆነው ተመርጠዋል።

 

አቶ አሥራት ጣሴ

Ato Asratአቶ አሥራት ጣሴ የተወለዱት የዛሬ 60 ዓመት በሸዋ ክፍለ ሀገር ነው። አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ በየነ መርዕድ ትምህርት ቤት ሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት ተምረው 11ኛ ክፍል እንደጨረሱ 12ኛን በዕደማርያም በተባለው ትምህርት ቤት አጠናቀቁ።

 

የሦስት ወንድ ልጆችና የአንድ ሴት ልጅ አባት የሆኑት አቶ አሥራት ጣሴ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በታሪክ በቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ዩኒቨርስቲ ሲወስዱ ማስተርስ ዲግሪያቸውን በአሜሪካን አገር "ዩኒቨርስቲ ኦፍ አሪዞና" በትምህርት አስተዳደርና አመራር አጠናቀዋል።

 

በወለጋ ክፍለ ሀገር ሁለተኛ ደረጃ መምህር ሆነው ሁለት ዓመት፣ የኃይስኩል ዳይሬክተር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በመምህርነት በአካዳሚክና አስተዳደር ምክትል ኃላፊ ሆነው በጠቅላላው ለ10 ዓመታት አገልግለዋል።

 

ከዛም የከፍተኛ ትምህርት ኮሚሽን ውስጥ የስኮላር ሺፕ ጉዳዮች ዋና ኃላፊ ሆነው ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ ዋና መቀመጫቸውን በጀርመን ሀገር ቦን ከተማ ሆኖ ኢትዮጵያ ተማሪዎች ጉዳይ በጀርመን፣ በቼክ፣ በስሎቫኪያ፣ በቡልጋሪያ፣ በሃንጋሪ በአማካሪነት ሰርተዋል።

 

አቶ አሥራት ጣሴ በኩዊንስ ኮሌጅ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ሲሰሩ ነበር።

 

የፖለቲካ ተሳትፎአቸው

በ1960ዎቹ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተበታተኑ ድርጅቶች አንድ መስመር ሲይዙና ተቀላቅለው አንድ ማኅበር ሲመሰርቱ ተሳትፎ ነበራቸው።

 

ኢዴአፖ - መድህን ቅንጅትን እስከተቀላቀለበት ምርጫ 97 ድረስ እዛ ነበሩ ከዚያም ቅንጅት ሲመሰረት እዛው ቀሩ ብዙም ሳይቆይ እሳቸውም ለ20 ወራት ታስረው ተፈቱ።

 

አቶ አሥራት ጣሴ የአንድነት ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ሆነው ተመርጠዋል።

 

ከፖርቲው የሚጠበቀው

ሁሉም ተመራጮች ፓርቲው ይጠበቅበታል ያሉት ተመሳሳይ ነገር ነው። "ከውጣ ውረዶች በኋላ አንድነት መስርተን ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመታገል ቆርጠን ተነስተናል" ብለዋል።

 

ፕሮፌሠር መስፍን ወልደማርያም 

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የአንድነት ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል ሆነው ተመርጠዋል። ሁለት ጥያቄዎችን አቀረብንላቸው - አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፖርቲ ጠንካራ ከመሆን የሚያግደው አንዳች ነገር የለም። የህዝቡ ፍላጎት የፖርቲው ጥንካሬ ይሆናል። የፖርቲውን ዓላማ ጠንቅቆ በማወቅ በፖርቲው ዙሪያ በመደራጀት፣ ፖርቲው የራሴ ነው ብሎ በሚያምን ህዝብ ከተደገፈ ያ ነው የፖርቲ ጥንካሬ ማለት።

 

ይሄ ሁሉ ችግር እያለ ለፓርቲው ምስረታ ከኡጋዴን፣ አፋር፣ ትግራይ እና ሌሎች ክልሎች ተጉዘው መጥተው ነበር። በኃይማኖት፣ በዘርና በቋንቋ ልዩነት ያልተከፈለን አንድነት ፖርቲ ለመመስረት አብዛኛው ሰው ተገኝቷል።

 

ስለ ወ/ት ብርቱካን የአመራር ብቃት

ብቃት ኖሮአት ሕግ ተማረች፣ ብቃት ኖሮአት ዳኛ ሆነች፣ ብቃት ኖሮአት ለአንድ ዓመት ያህል ፖርቲውን መርታለች። በዚህ ላይ ፖርቲው በሴት ሲመራ ብዙ ሴቶችን ታበረታታለች፣ ከወጣቶች ጋር በእኩልነት የትግል መንፈስ ተግባብታ ትሰራለች።

 

ወጣት ስለሺ ጠና

የቅንጅት የቀድሞ የላዕላይ ምክር ቤት አባል እና የአሁኑ አንድነት ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆነውን አቶ ስለሺ ጠናን ወ/ት ብርቱካን የአመራር ብቃት አላት ወይ ስንል ጥያቄ አቀርበንለታል።

 

የፓርቲ ሊቀመንበር ሆና ስለተመረጠችው ወ/ት ብርቱካን የአመራር ብቃት ያለኝን የግል አስተያየት ልስጥ፣ አንድ አመራር ብቃት አለው የለውም የሚል መለኪያ የሚመጣለት መወሰን ባለበት ቦታ ላይ ይወስናል ወይ? አቋም መያዝ ባለበት ቦታ ላይ አቋም ይይዛል ወይ? በአንድ ፖርቲ ያሉ ሰዎችን አስተባብሮ አቻችሎ በዙሪያው ያሉ ሰዎችን አግባብቶ እንዲሰሩ ማድረግ ይችላል ወይ? የሚለው መመዘኛ ይመስለኛል። ወ/ት ብርቱካንን ከዚህ አንፃር ስመዝናት፣ አስቸጋሪና ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ውሣኔ በመስጠት፣ አቋሟን ደፍራ በማሳወቅ፣ በአጠገቧ ካሉ ሰዎች ጋርም ተግባብቶ ለመሥራት ትሞክራለች። ብቃት ያለው አመራር የሚጠይቀውን መስፈርት አሟልቶ ለመቀጠል በዙሪያዋ ካሉ ሰዎች ሁሉ የተሻለች ሆና ተመርጣለች ባይ ነኝ።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!