አርቲስት በኃይሉ መንገሻ Artist Behailu Mengeshaአለምፀሐይ ወዳጆ
በኢትዮጵያ የትያትር ሙያ ተደናቂና ተወዳጅ የነበረው አርቲስት በኃይሉ መንገሻ በተወለደ በ57 ዓመቱ ማርች 3/2013 (የካቲት 24/2005) ዓ.ም. ነዋሪ ሆኖ በቆየበት በሰሜን አሜሪካ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

 

አርቲስት በኃይሉ መንገሻ ከአባቱ ከአቶ መንገሻ ከበደና ከእናቱ ከወ/ሮ አየለች ተክለወልድ የካቲት 1 ቀን 1948 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ነበር የተወለደው። የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአዲስ አበባ መድኃኒዓለም ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አጠናቅቆ፤ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የ2 ዓመት በቴአትር ሞያ ሠልጥኗል። በማከታተልም በታንዛንያ በሚሊተሪ ሣይንስ ትምህርት ሁለት ዓመት የተማረ ሲሆን፤ ወደ ሶቪየት ህብረት በመጓዝ በሞስኮ የቴአትር ኪነጥበብ አካዳሚ ለ5 ዓመታት ትምህርቱን በመከታተል በቴአትር ዝግጅት (ማስተር ኦፍ አርትስ) ዲግሪውን አግኝቷል።

 

ወደ ሀገሩ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት በተለያዩ የኃላፊነት ሥፍራዎች ላይ ሠርቷል። ከእነዚህም በጥቂቱ የቴአትር ክፍል ኃላፊ፣ የፕሮግራምና ፕሮዳክሽን ኃላፊ፣ ከፍተኛ ቴአትር አዘጋጅ፣ አርቲስቲክ ዳይሬክተር ሆኖ አገልግሏል።

 

ከ1984 ጀምሮ በክልል 14 የባህልና የስፖርት ቢሮ የሚሰጠውን ከፍተኛ የሙያ እገዛ በመቀጠል በአርቲስቲክ ዳይሬክተርነት፣ በቴአትር፣ በሙዚቃ በሥዕልና ሥነጽሁፍ የሥነጥበባት ማስተባበሪያ ቡድን መሪ፣ በሥነጥበባት ዋና ክፍል ኃላፊነት፣ በፊልም ትምህርት መምህርነት፣ በትወና ሞያ በወጣቶች አሰልጣኝነት አገልግሏል።

 

በሥራውና በሙያው የሚያሳየው ከፍተኛ መሻሻል ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የቴአትርና የባህል አዳራሽ ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆን ለ6 ዓመታት ያህል አገልግሏል። በኃይሉ በተውኔት ሙያ ውስጥ በትወናና በአዘጋጅነት ከመሥራቱ ሌላ በፊልም ተዋናይነት ያለውን ችሎታና ሙያ አሣይቷል። The adventure of Tom Sweyer፣ The Big Battalions "የክትነሽ" ቪዲዮ ፊልም አባውቃውና ጋዜጠኛው ላይ ተሳትፏል።

 

በመድረክ ቴአትር ደግሞ የአርባ ቀኑ መዘዝ፣ ሀሁ በስድስት ወር፣ አፅም በየገዱ፣ አቦጊዳ ቀይሶ፣ እና ሐምሌት ላይ በተዋናይነት ተሣትፏል። በቴአትር አዘጋጅነት ሞያው የእጮኛው ሚዜ፣ አንቺን አሉ፣ ቅኝት፣ ውጫሌ 17፣ ፍቅር በአሜሪካ፣ የደም ቀለበት፣ የከርቸሌው ዘፋኝ እና የምሽት ፍቅረኞችን አዘጋጅቶ በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፏል።

 

በኃይሉ ጥር 30/1979 ከወ/ሮ ዓለምእሸት ከዱ ጋር ህጋዊ ጋብቻ በማድረግ የአንድ ልጅ አባትና የሁለት የልጅ ልጆች ባለፀጋ ነው። ከሴፕቴምበር 10 ቀን 2005 ጀምሮ ወደ አሜሪካን በመሄድ ከቤተሰቡ ጋር እየኖረ በጤናው ላይ በደረሰበት ችግር በተለያዩ ሆስፒታሎች የተለያዩ ሕክምናዎችን ሲያደርግ ቆይቷል። ይሁንና በኃይሉ የጤና መታወኩ ከሚወደው ሙያው ሳይነጥለው ከጣይቱ የባህል ማዕከል ጋር በመሆን በተለያዩ የአሜሪካ ስቴቶች ካናዳን ጨምሮ እየተጓዘ በሙያው ተመልካቹን ሲያስደስት ከመቆየቱም ሌላ በየወሩ የግጥም ምሽት ላይ በሚያቀርባቸው ድንቅዬ የጥናትና የሙያ ፅሁፎች ተሣታፊዎችን እያሳቀ በማስተማር ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል።

 

በኃይሉ ዕድሜውን ሙሉ ከገበረለት ሙያው ድንቅ ውጤት በተጨማሪ በግል ባህሪው እጅግ ተወዳጅና ተፈቃሪ ሰው ነበር። የታመመ ጠያቂ፣ የተጣላ አስታራቂ፣ የሞተ ቀባሪ፣ ያዘነና የተከፋ መካሪ፣ የሁሉ ቤተሰብ የሁሉ ወንድም የሁሉ ልጅ የሁሉ ጓደኛ ነበር። በደረሰበት ልዩ ልዩ የጤና እክል ላይ ሁሉ እንደ ቀለደና እንዳፌዘ ፈጣሪውን አንድም ቀን ሳያማርር ይህችን ምድር የተሰናበተ ለሁላችን አርኣያ የሚሆን የጥሩ ሰው ምሣሌ ነበር። የሱን ፅናትና ጥንካሬ የሱን ሰው አፍቃሪነት ለሁላችንም ያድለን። እግዚአብሔር ነፍሱን ከአብርሃምና ከይስሐቅ ጎን በገነት እንዲያኖራትና ቤተሰቡን ወዳጆቹን ዘመዶቹንና ጓደኞቹን መፅናናት እንዲሰጣቸው እንፀልያለን።

 

የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ዝግጅት ክፍልም በዚህ አጋጣሚ ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጅ ዘመዶቹ፣ ለጓደኞቹና ለመላው አፍቃሪው ሁሉ መፅናናትን ትመኛለች።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!