Aboy Zenawi Asres, 82የሕይወት ታሪካቸውን ይዘናል (ተጨማሪ ዘገባ)

PM Meles ZenawiEthiopia Zare (ኀሙስ ሰኔ 19 ቀን 2000 ዓ.ም. June 26, 2008)፦ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ወላጅ አባት የሆኑት አቶ ዜናዊ አስረስ ትናንት ረቡዕ ሰኔ 18 ቀን 2000 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም ማረፋቸውን የአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ምንጮች ገለጹ።

አቶ ዜናዊ ለስድስት ወራት ታምመው የአልጋ ቁራኛ ሆነው መሰንበታቸውን እነዚሁ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገልጸዋል። አቶ ዜናዊ በጠና ከታመሙበት ጊዜ አንስቶ አራት ኪሎ በሚገኘው ቤተመንግሥት ተኝተው እንደነበር ለማወቅ ችለናል።

ምንጮቻችን እንደገለጹት ከሆነ የቀብር ስነ-ሥርዓታቸው የሚፈጸመው አድዋ ሲሆን፣ ዛሬ አስከሬናቸው ከቤተመንግሥት ወደ አድዋ ተወስዷል።

አቦይ ዜናዊ አስረስ፣ ከአባታቸው ከደጃዝማች አስረስ ተሰማ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ዘውዲቱ መንገሻ ዓርብ ጥር 14 ቀን 1918 ዓ.ም. አድዋ ውስጥ ተወለዱ።

በ1924 ዓ.ም. ሚሽን ትምህርት ቤት ገብተው እና በሥላሴ ቤተክርስቲያን ውስጥ መጻፍና ማንበብ እየተማሩ እያለ ጣሊያን ሲመጣ ከአባታቸው ጋር በረሃ ገቡ፣ በ1928 ዓ.ም. በረሃ ተመለሱ። አባታቸው ከሞቱ በኋላ ከአራተኛ ክፍል ትምህርታቸውን አቋርጠዋል።

አባታቸው ከ1914 ዓ.ም. ጀምሮ የአጼ ኃይለሥላሴ የሀገር ውስጥ ደህንነት ፖሊስ ሠራተኛ የነበሩ ሲሆን፣ በ1936 ዓ.ም. ሕይወታቸው ሲያልፍ አጼ ኃይለሥላሴ ከአዲስ አበባ ባለሥልጣኖች ልከው 500 ብር የእዝን አሰጥተዋቸው ነበር።

አባታቸው ላይዘን ኦፊሰር የነበሩ በመሆኑ እሳቸው ሲሞቱ ለአቶ ዜናዊ ሥራ እንዲሰጣቸው ቢነገርም እንቢ ብለው የወላጆቻቸውን ንብረት ማስተዳደር ቀጠሉ።

በሕይወት ዘመናቸው አቦይ ዜናዊ 13 ልጆች ያፈሩ ቢሆንም ከአንዳቸውም እርዳታ እንዳላገኙ በሕይወት በነበሩ ወቅት ይገልጻሉ።

ልጃቸው አቶ መለስ የሕክምና ባለሙያ እንዲሆን ይፈልጉ እንደነበር በሕይወት እያሉ የገለጹት አቦይ ዜናዊ፣ ልጃቸው መለስን እና አባይ ፀሐዬ ታጋዮች በነበሩበት ወቅት ከጫካ መጥተው ለአንድ ወር ከሁለት ሣምንት ደብቀው አስቀምጠዋቸው እንደነበር ገልጸው ነበር።

አቦይ ዜናዊ በአድዋ ከተማ ይኖሩ የነበረ ሲሆን፣ ለሕክምና በመጡበት በአዲስ አበባ በሰማንያ ሁለት ዓመታቸው ሕይወታቸው ሊያልፍ መቻሉ ታውቋል።

ነገ ዓርብ የቀብር ሥነሥርዓታቸው በአድዋ ከተማ ይፈፀማል ተብሎ ይጠበቃል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!