እነፕ/ር ኤፍሬም የፖለቲካ እስረኞችን አስፈቱ

Ethiopia Zare (ማክሰኞ ሐምሌ 1 ቀን 2000 ዓ.ም. July 8, 2008) ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘ ኢህአዴግ ወደ እስር ከወረወራቸው በርካታ የፖለቲካ እስረኞች ውስጥ በዛሬው ዕለት ሰላሳ አንዱ ይቅርታ ጠይቀው መፈታታቸውን ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ የደረሰው መረጃ ጠቆመ። እስረኞቹን ያስፈታው በፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስኃቅ የሚመራው የሽማግሌዎች ቡድን እንደሆነ ለማወቅ ችለናል።

 

በፕ/ር ኤፍሬም የሚመራው የሽማግሌዎቹ ሕብረት የፖለቲካ እስረኞቹን መፈታት አስመልክቶ የተፈቱትን እስረኞች ቤተሰቦች፣ ጓደኞች እንዲሁም የሀገሪቱን ህዝብ እንኳን ደስ ያላችሁ ሲል መልዕክት አስተላልፏል።

 

የፖለቲካ እስረኞቹ በዛሬው ዕለት በመፈታታቸው የሽማግሌዎቹ ሕብረት ለኢህአዴግ መንግሥት ምስጋና ያቀረበ ሲሆን፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በትዕግስት ስለተጠባበቁ ምስጋናውን አቅርቧል። ከዚህም በተጨማሪ በቅርቡ ተጨማሪ እስረኞች በይቅርታ ሊፈቱ እንደሚችሉ ያለውን ፅኑ እምነት ገልጿል።

 

በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የሚመራው አንድነት ፓርቲ ከምርጫ 97 እና ከቀድሞው ቅንጅት ጋር በተያያዘ የታሰሩትን የፖለቲካ እስረኞች ከሽማግሌዎቹ ጋር በመሆን ለማስፈታት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ይታወቃል።

 

በፕ/ር ኤፍሬም ይስኃቅ የሚመራው የሽማግሌዎች ቡድን በተለይ የፖለቲካ እስረኞችን ይቅርታ እያስጠየቀ ለማስፈታት የሚያደርገው ጥረት ከበርካታ ወገኖች ትችት እየደረሰበትና ተቃውሞ እየገጠመው እንደሆነ ይደመጣል። እየተሰነዘሩ ካሉት አስተያየቶችና የመከራከሪያ ነጥቦች ውስጥ ”የሀገራችንን የሽምግልና ባህል አራከሱት”፣ ”ከሽምግልናው ተጠቃሚው ኢህአዴግ ብቻ ነው”፣ ”ኢህአዴግ ላይ ይለሳለሳሉ”፣ ... የሚሉት ይገኙበታል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!