የሕግ ባለሙያው ዶ/ር ሸክስፒር ፈይሳ ንግግር ያደርጋል

አሁንም የኢትዮጵያዊያኖች የድረሱልኝ ጥሪ እየተሰማ ነው

Ethiopia Zare (ሐሙስ ኅዳር 5 ቀን 2006 ዓ.ም. November 14, 2013)፦ በካናዳ የንግድ መናገሻ በሆነችው ቶሮንቶ ከተማ በሳኡዲት አረቢያ በኢትዮጵያዊያኖች ላይ የሚፈጸመውን ግፍ በመቃወምና በአሰቃቂ ሁናቴ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች የሻማ ማብራት ስነስርአት ነገ አርብ እንደሚካሄድ ይፋ ተደረገ።

 

በአረብ ሀገራት በተለይ በሳውዲት አረቢያ ሰሞኑን በዜጎች ላይ የሚፈጸመውን በፌሮ ብረት የሚፈጸም ድብደባ፣ በስለት፣ በጭካኔ በህጻናቶችና በሴቶች ላይ የሚፈጸመው አሰቃቂ ወከባና እንግልት ብሎም በሴቶች እህቶች ላይ እየደረሰ ያለው አስገድዶ መድፈር ያስቆጣቸው ኢትዮጵያዊያን በአለማቀፍ ደረጃ ማለትም በርካታ ኢትዮጵያዊያን የሚኖሩባት ዋሽንግተን ዲሲን ጨምሮ በዋና ዋና የአውሮፓ ሀገራት ዛሬ ሀሙስ በሳውዲት አረቢያ ኤምባሲዎችና ካውንስለር ቢሮዎች ደጃፍ ላይ ታላላቅ ሰላማዊ ሰልፎች የተደረጉ ሲሆን በቶሮንቶ-ካናዳ ኢትዮጵያዊያኖች ነገ አርብ ኖቬምበር 15/2013 ከ4pm-6pm በQueen's Park, Toronto በመውጣት አጋርነታቸውን እንደሚያሳዩ አዘጋጆቹ ገልጸው ነዋሪነቱ በሲያትል ዋሽንግተን የሆነው የህግ ባለሙያ ዶ/ር ሸክስፒር ፈይሳ በቦታው ተገኝቶ በቀጣይነት በኢትዮጵያዊያን ላይ የሚፈጸመውን የሰብአዊ መብት ጥሰት አስመልክቶ ንግግር እንደሚያደርግ ይፋ አድርገዋል።

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የተቃዋሚ ድርጅቶች በሳኡዲት አረቢያ በኢትዮጵያዊያን ላይ የሚፈጸመውን ግፍ በመቃወም መልእክቶቻቸውን ያስተላለፉ ሲሆን ነገ አርብ የሰማያዊ ፓርቲ አዲስ አበባ በሚገኘው የሳኡዲት አረቢያ ኤምባሲ በር ላይ ኢትዮጵያዊያኖች ጥቁር ልብስ በመልበስ ተቃውሟቸውን እንዲያሰሙ ጥሪ ማቅረቡ የሚታወቅ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድንም ቅዳሜ ከናይጄሪያ አቻው ጋር በሚያደርገው ግጥሚያ ላይ ጥቁር ሪባን አስረው እንዲጫወቱ ጠይቋል።

በሳኡዲት አረቢያ በኢትዮጵያዊያኖች ላይ የሚፈጸመውን መከራ በተለያዩ አለማት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን በማነጋገር ላይ ያለ ሲሆን ቁጣቸውንም በአደባባይና በተለያዩ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሀን በማሰማት ላይ ይገኛሉ።

ይህንኑ ዘግናኝ ጭፍጨፋና እንግልት በመቃወም በተለያዩ የአለም አቀፍ ከተሞች የሻማ ማብራት ስነ ስርአትና የተቃውሞ ሰልፎች የሚደረጉ ሲሆን በአውስትራሊያ በመጭው ሰኞ፤ በቫንኩቨር ካናዳ ደግሞ እሁድ ጠዋት ሮብሰን ስኩዌር በተባለው ቦታ ኢትዮጵያዊያኖች የሻማ ማብራት ስነ ስርአት እንደሚያደርጉ ለማወቅ ተችሏል።

በሳኡዲት አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሚደርስባቸውን ግፍ በቪድዮ ምስል በማስደገፍ ጥሪያቸውን ሲያስተላልፉ ቆይተዋል።

የቪድዮ መልዕክት ምስል አንድ

የቪድዮ መልዕክት ምስል ሁለት

የቪድዮ መልዕክት ምስል ሦስት

ከዝግጅት ክፍሉ በአሰቃቂው ፈተና ውስጥ ላላችሁ፣ ህይወታቸው በግፍ ለተነጠቀባቸው በአጠቃላይ በዚህ ዘግናኝ ጭፍጨፋና እንግልት ሙሉ ልባችሁ በኀዘን ለተነካ ኢትዮጵያዊያንና የተጠያቂ ቤተሰቦች በሙሉ መጽናናትንና ብርታትን ታገኙ ዘንድ ከልብ እንመኛለን።

የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!