Teddy Afroቴዲ "ቅማል በላኝ" በማለቱ 32ኛ ዓመቱን በጨለማ ቤት አከበረ

Ethiopia Zare (ማክሰኞ ሐምሌ 8 ቀን 2000 ዓ.ም. July 15, 2008)፦ ቴዲ አፍሮ ባለፈው ዓርብ ሐምሌ 4 ቀን 2000 ዓ.ም. በዋለው ችሎት "… እኔ አንድም ሰው አልገደልኩም ሰውም አልገጨሁም። ነገር ግን በማላውቀው ነገር ሰብዓዊ መብቴ ተገፍፎ ቅማል እየበላኝ ሦስት ወር ታስሬያለሁ። …" ብሎ በመናገሩ ምክንያት ወደ ጨለማ ቤት መወርወሩንና የልደት በዓሉን ትላንት በጨለማ ቤት ማክበሩን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጹ።

 

ምንጮቻችን እንዳረጋገጡት ቤተሰቡና ጓደኞቹ ልደቱን ለማክበር ተሰባስበው ለማግኘት ቢሞክሩም እንዳልተፈቀደላቸውና ቴዎድሮስ ካሳሁንን ለማግኘት እንዳልቻሉ የታወቀ ሲሆን፣ የልደት በዓሉን በውጭ በማስታወስ እንዳሳለፉ ለማወቅ ችለናል።

 

ቴዲ ለመጀመሪያ ጊዜ በችሎት ላይ ድምፁን ያሰማ ሲሆን፣ "የተከበረው ፍርድ ቤት ስለተሰጠኝ ዕድል በጣም አመሰግናለሁ! እኔ የማምነው ይህን ሁሉ ሰው በሚያይ እግዚያብሔር ነው። ግን አንድ ነገር መናገር እፈልጋለሁ። እኔ አንድም ሰው አልገደልኩም ሰውም አልገጨሁም። ነገር ግን በማላውቀው ነገር ሰብዓዊ መብቴ ተገፍፎ ቅማል እየበላኝ ሦስት ወር ታስሬያለሁ። ፍርድ ቤቱንም ሆነ የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት የምጠይቀው ጉዳዩን በሚገባ ተረድተው በነፃ እንዲያሰናብቱኝ ነው።" ብሎ መናገሩን መዘገባችን አይዘነጋም።  ችሎቱ ተጠናቆ ወደ ቃሊቲ እንደተወሰደ የማረሚያ ቤት ፖሊሶች "ቅማል በላኝ" በማለቱ በመቆጣታቸው ወደ ጨለማ ቤት እንዳስገቡትና በአሁኑ ሰዓት ብቻውን እንደሚገኝ ለማወቅ ችለናል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ