አንድነት ፓርቲ ስሙን ተከለከለ
Ethiopia Zare (ኀሙስ ሐምሌ 10 ቀን 2000 ዓ.ም. July 17, 2008)፦ “አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ” በሚል ስያሜ ፓርቲ ለማቋቋም ጠቅላላ ጉባዔውን አካሂዶና አስፈላጊውን ማስረጃዎችና ፎርማሊቲዎች አሟልተው ባለፈው ሣምንት ረቡዕ ለምርጫ ቦርድ ፈቃድ መጠየቂያ ማመልከቻውን ያስገቡትና መሥራቾቹ “አንድነት” የሚለውን ስም መጠቀም እንደማይችሉ ምርጫ ቦርድ በዛሬው ዕለት መግለጹን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮቻችን ገለጹ።
እነኚሁ ምንጮቻችን እንደገለጹት ከሆነ ፓርቲው በሕጋዊ መንገድ ለመቋቋም ያስችለኛል በሚል ያቀረበውን ሰነድ ለቦርዱ ከመቅረቡ በፊት ጽሕፈት ቤቱ ተመልክቶ አስር ነጥቦችን በመዘርዘር እንደገና ሰነዱ ተሟልቶ እንዲቀርብለት በዛሬው ዕለት አዝዟል።
ምርጫ ቦርድ ከዘረዘራቸው አስር ነጥቦች ውስጥ “አንድነት” የሚለው የሰው ስም ስለሆነና ሕጉ ደግሞ ይህንን ስለማይፈቅድ ቃሉን መጠቀም እንደማይቻል ገልጾ፣ ለቦርዱ ከመቅረቡ በፊት እንዲስተካከል የሚለው ይገኝበታል።
ፓርቲው ለምርጫ ቦርድ ያስገባውን ሰነዶች የመረመረው የቦርዱ ጽሕፈት ቤት ለመሥራች አባላቱ በጻፈው በዚሁ ደብዳቤ ላይ፤ የድጋፍ ፊርማ ሳይፈርሙ፣ መስራች አባላት ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ስሞች በመኖራቸው፣ በፕሮግራሙና በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ያሉትን ቃላቶችና ሌሎች ነገሮችን አስተካክለው እንዲቀርቡ ገልጿል።
በመጨረሻም የቦርዱ ጽሕፈት ቤት ተጓድለዋል፣ ይቀየሩ ብሎ ያላቸውና የጠቀሳቸው አስር ዝርዝር ነጥቦች ተሟልተው ሲቀርቡለት ጥያቄውን ለቦርዱ እንደሚያቀርብ ለመሥራቾቹ በጻፈው ደብዳቤ ገልጿል።
የአንድነት አመራሮች የምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት ደብዳቤው ከደረሳቸውን በኋላ በጉዳዩ ላይ ስብሰባ እንደተቀመጡ ምንጮቻችን ገልጸዋል።
“አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ” የሚለውን ፓርቲ ለማቋቋም ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልተው ማመልከቻ ያስገቡት ከቀድሞው “ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ” ፓርቲ ከፍተኛ የአመራር አባላቶች መከፋፈል በኋላ 19 በሚሆኑ የላዕላይ ምክር ቤት አባላት መሆናቸው ይታወቃል።