Teddy Afro- ክሱን ተከላከል ተባለ

- ወዳጅ ዘመዶቹ በእንባ ተራጭተዋል

Ethiopia Zare (ሰኞ ሐምሌ 14 ቀን 2000 ዓ.ም. July 21, 2008)፦ አዲስ አበባ በፍተኛ ዝናብ ተውጣለች። ዝናቡን ከምንም ያልቆጠሩ የቴዲ አፍሮ ቤተሰቦች፣ ጓደኞችና አድናቂዎቹ በከፍተኛው ፍርድ ቤት መግቢያ በር ላይ በተለመደው ሁኔታ ሰልፍ ይዘዋል። ከላይ ስለሚወርድባቸው ዝናብ አንድም ያዘነ ፖሊስ አለነበረም። “ምናለበት ውስጥ ገብተን ብንጠብቅ?” የሚለው ጥያቄም መልስ አላገኘም። በተለመደው ሰዓት ከጠዋቱ 2፡45 ሲሆን፣ ወደ ግቢው እንድንገባ ተፈቀደ።

 

ግን ሌላ ሁለተኛ ሰልፍ ይጠብቀን ነበርና የአዳራሹ መግቢያ ላይ ለሁለተኛ ሰልፍ ቆምን። ሁሉም እርስ በርሱ ይነጋገራል። አንዳንዱ “ዛሬማ ይፈታል” በማለት ተስፋን ይሰጣል፤ ሌላው ደግሞ ”በፍጹም አይፈታም” ሲል ”እስቲ አታሙዋርቱ ሁሉንም እዚያው እንሰማዋለን” ሲል ሌላው ይቆጣል። ”ሞባይል ስልካችሁን አጥፉ” ፖሊሱ ደግሞ ይጮሃል።

 

ዝናቡ ጋብ ቢልም ማካፋቱን ግን አልተወም ነበር። ከስር ደግሞ ጭቃው መቆሚያ አሳጥቷል። በዛ ላይ ደግሞ ጉንዳኑ። ዞር ዞር ብዬ ስመለከት ሁሉም የራሱን ጨዋታ ይጫወታል ብቻዬን የተማረርኩ መሰለኝና ወደ ጓደኞቼ ጨዋታ ተመለስኩ።

 

ለአንድ ሰዓት ያህል በዚህ ሁኔታ ከቆምን በኋላ ”ጋዜጠኞች ቅድሚያ ግቡ” ተባለ፤ አመስግነን ወደ ውስጥ ዘለቅን። አዳራሹ ወዲያው ሞላ ውጭ የቆሙ በርካታ ተመልካቾች በአዳራሽ ጥበት እንዳይገቡ ተከለከሉ።

 

ቴዲ አፍሮ እንደሚፈታ ተስፋ ያደረበት ይመስላል ከወትሮ በተለየ ሁኔታ ሙሉ ሱፍ ለብሷል። ፈገግ እያለ ለቤተሰቦቹ ሠላምታ ይሰጣል። በእጁ የያዘውን መጽሐፍ አንዴ ያነባዋል፣ አንዴ ደግሞ ያስቀምጠዋል ለ40 ደቂቃ ያህል ዳኛውን በአዳራሹ ውስጥ ጠበቅን።

 

ከጠዋቱ 3፡55 ሲል ችሎቱ ተሰየመ። ዳኛ ልዑል ገ/ማርያም፣ ዓቃቤ ሕግ ፍቃዱ ጸጋ እና ተከሳሽ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ከጠበቃ ሚሊዮን አሰፋ ጋር መቅረቡ ከተረጋገጠ በኋላ ፍርድ ቤቱ ሥራውን ጀመረ። መዝገቡ የተቀጠረው የዓቃቤ ሕግን ክስና ማስረጃ መርምሮ ብይን ለመስጠት መሆኑን በመግለጽ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ ብይን መስጠቱን በመጠቆም በንባብ ማሰማት ጀመረ።

 

ሁሉም ዝም አለ፣ ፍፁም ፀጥታ በፍርድ ቤቱ አዳራሽ ሰፈነ። ዓቃቤ ሕግ፣ ጠበቃውና ቴዲም ጀርባቸውን ለተመልካቹ ሰጥተው የዳኛውን ዓይን ዓይን ይመለከታሉ። ተመልካቹ ፊቱን ወደ ዳኛው መቀመጫ እንደተከለ ቀርቷል።

 

ዳኛው መናገር ጀመሩ፤ በቴዎድሮስ ካሳሁን ላይ የቀረበውን ክስና ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን ማስረጃ ዝርዝር በንባብ ካሰሙ በኋላ ”… የቀረበውን ክስ በሚመለከት የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችም ሆነ የሰነድ ማስረጃው በሚገባ ስላስረዳ ተከሳሹ የቀረበበትን ክስ መከላከያ ማስረጃ በማቅረብ ይከላከል” ካሉ በኋላ ወረቀታቸውን መለስ መለስ አድርገው ቀና አሉ።

 

ቴዲ አንገቱን አቀረቀረ። አንድም ትንፋሽ ያሰማ ሰው አልነበረም፣ ቴዲ ወደ ጠበቃው ዘወር አለና ወረቀትና ስክሪብቶ ጠይቆ ተሰጠው የሆነ ነገር ጫር ጫር አደረገ።

 

”የመከላከያ ማስረጃ አላችሁ?” ዳኛው ጠየቁ ”አዎ አለን የተከበረው ፍርድ ቤት” ጠበቃው መልስ ሰጡ።  ዳኛው ”እንደሚታወቀው የፍርድ ቤቱ የሥራ ጊዜ እየተጠናቀቀ ነው፤ ስለዚህ ያው ለሚቀጥለው ዓመት መሻገሩ ነው …” በማለት ጠበቃውን ቀና ብለው ተመለቱ፣ ዝም አለ ”ፍርድ ቤት የሚከፈተው መስከረም 27 ነው። መስከረም 28 ደግሞ 48 ምስክሮች የሚሰማበት ችሎት አለኝ። ስለዚህ መቼ እናድርገው?” ብለው ዳኛው ጠየቁ።  ”ፍርድ ቤቱ በተመቸው ጊዜ ያድርገው” ሲል ጠበቃው ሚሊዮን አሰፋ መልስ ሰጠ፤ ዳኛ ልዑል ገ/ማርያም ”እንግዲያውስ መስከረም 29 እናድርገው” የመከላከያ ማስረጃ ለመስማት ለመስከረም 29 ቀን 2001 ዓ.ም. ቀጥረናል” አሉና መዘገቡን ዘግተው ተነሱ።

 

ቴዲም የሚቀጥሉትን 75 ቀናት ቃሊቲ ወደሚገኘው እስር ቤት ለማሳለፍ ተነሳ፤ ሌባ ጣቱን ወደ ሰማይ አድርጎ ”አንተ ታውቃለህ” በሚል ብሶቱን ለፈጣሪው አሰማ። ”ቴዲዬ አይዞህ እግዚያብሔር ካንተ ጋር ይሁን!” በለቅሶ የተመልካቹ ድምፅ ተከተለው። እየደጋገመ እጁን ወደ ሰማይ እያሳየ አዳራሹን ለቆ ወጣ።

 

ርቆ እስኪሄድ ከአዳራሹ እንዳንወጣ ተከለከልን እንደተለመደው በደህንነቶች ቪዲዮ ካሜራ እየተቀረጽን፣ ሲፈቀድልን ወጣን። ቤተሰቦቹና አድናቂዎቹ ከአዳራሹም ከወጡ በኋላ ለቅሶአቸውን አላቁዋረጡም ነበር። የፍርድ ቤቱን ግቢ ያጣበቡት ፌደራል ፖሊሶች ማንም በግቢው እንዲቆም አልፈቀዱም ሁሉንም እየገፈታተሩ ማስወጣት ጀመሩ። ከግቢው ከወጣን በኋላ ”ምን ተባለ?” እያለ ለሚጠይቀው ውስጥ መግባት ላልታደለው በርካታ ሰው ጉዳዩን እየነገሩ ማለፍ ግድ ነበር።

 

የክሱ አመጣጥና ሂደት

ቴዲ አፍሮ ረቡዕ ጥቅምት 22 ቀን 1999 ዓ.ም. ከካናዳ ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል። ዓርብ ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. በሲ.ኤም.ሲ. ይኖርበት ከነበረው መኖሪያ ቤቱ “ሰው ገጭተህ አምልጠሃል” በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ እስር ቤት ይገባል። ሜክሲኮ በሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ ነክ ፍርድ ቤት የሰባት ቀን የጊዜ ቀጠሮም ተጠይቆበት ወደ ታሰረበት ጣቢያ ይመለሳል።

 

ቅዳሜ ጥቅምት 25 ቀን 1999 ዓ.ም. ከታሰረበት ጣቢያ የ50 ሺህ ብር ዋስትና አስይዞ ይለቀቃል። በቀጠሮው መሰረትም ፍርድ ቤት ሲቀርብ፤ ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን አጠናቆ ለሚመለከተው አካል ያስተላለፈ መሆኑን በመግለጽ የቀጠሮ መዝገቡ እንዲዘጋለት ጠይቆ መዝገቡ ተዘግቷል።

 

ጉዳዩን የያዘው ፖሊስም ኅዳር 7 ቀን 1999 ዓ.ም. በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 2749/99 ቁጥር 8206/ወ/መ18 በተጻፈ መሸኛ ደብዳቤ “ቴዎድሮስ ካሣሁን ገርማሞ ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ከአስር ደቂቃ ሲሆን በአራዳ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 17 ክልል በቤተ መንግሥት አካባቢ ንብረትነቱ የግላቸው በሆነው ኮድ 2-59868 አዲስ አበባ BMW አውቶሞቢል መኪናቸው ደጉ ይበልጣል የተባለ እግረኛ ገጭተው ገድለው ካመለጡ በኋላ፣ በፍለጋ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ የተደረገባቸው ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት የምርመራ መዝገቡ ተጠናቆ ከዚህ ሸኚ ደብዳቤ ጋር ተልኳል።” የሚል ደብዳቤ ጽፎና ምርመራውን ማጠናቀቁን ገልጾ መዝገቡን ለአዲስ አበባ ፍትህ ሚኒስቴር ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስተላለፈ።

 

ስለ ሟች “ፎርቹን” ጋዜጣ አውጥቶት የነበረው የሕይወት ታሪክ

ቴዲ አፍሮ በመኪና ገጭቶ ገድሎታል በሚል የተጠረጠረበትን የሟች ደጉ ይበልጣል የሕይወት ታሪክ “ፎርቹን” የተባለ የእንግሊዘኛ ጋዜጣ የሟች አባት አቶ ታምሩ ተፈሪን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ሟች ከጎጃም መጥቶ ሽሮ ሜዳ አካባቢ ከአጎቱ ጋር ይኖር የነበረ የ18 ዓመት ወጣት ነው። ደጉ መጠጥ ከሚጠጡ ልጆች ጋር በመግጠሙ ቤቱን ጥሎ ለጎዳና ሕይወት ይዳረጋል። ነገር ግን በሣምንት አንዴ ወይም ሁለቴ ወደ ቤተሰቦቹ በመምጣት ይጠይቃቸው እንደነበር ነው። ዓርብ ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. ደጉ በመኪና አደጋ መሞቱ ተነግሯቸው አስከሬኑን ከምኒልክ ሆስፒታል ወስደው በእንጦጦ ቁስቋም ማርያም ቤተክርስቲያን መቅበራቸውን ጋዜጣው ዘግቦ ነበር።

 

ቴዲ በወቅቱ ለአዲስ አድማስና ሪፖርተር ጋዜጣ የሰጠው መልስ

“ሰውን የሚያህል ክቡር ነገር ገጭቼ ላመልጥ አልችልም፣ እኔ ድርጊቱ ተፈጸመ በተባለበት ቦታ አልነበርኩም፣ 'ሰው ገጭቶ አምልጧል' የተባለው ወሬ ሐሰትና ጉዳዩም ክብሬን የሚነካ ነው” ነበር ያለው።

 

ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በኋላ የተቀሰቀሰው የቴዲ ክስና የፍርድ ሂደት

ረቡዕ ሚያዝያ 8 ቀን 2000 ዓ.ም.

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስምንተኛ ወንጀል ችሎት፤ (ለሁለት ዓመታት የዘለቀውንና የቅንጅት አመራሮች ... የተከሰሱበትን የሁለተኛ ወንጀል ችሎት በቀኝ ዳኝነት ሲያስችሉ በነበሩት) ዳኛ አቶ ልዑል ገብረማርያም ከጠዋቱ 3 ሰዓት ከ30 ደቂቃ የተሰየመው ችሎት ከጠዋቱ 5 ሰዓት አካባቢ ሲሆን በወንጀል መዝገብ ቁጥር 06226 የተከሰሰው ተከሳሽ እንዲቀርብ ጥሪ አስተላለፉ።

 

ችሎቱ መደበኛ በመሆኑና በዕለቱ በህዝብ ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈው የታዋቂው ዘፋኝ የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን መዝገብ መሆኑን በችሎት ታዳሚው የሚታወቅ ባለመሆኑ፤ ቴዲ አፍሮ ከጠበቃው ጋር ወደ ተከሳሽ ሳጥን ገብቶ ሲቆም የችሎት ተከታታይ ዓይን ወደ ሣጥኑ ተወረወረ።

 

ዳኛው፤ መዝገቡ በችሎት ተከፍቶ ሊቀርብ የቻለበትን ምክንያት ማሰማት ጀመሩ፣ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በቴዎድሮስ ካሳሁን ያቀረበው ክስ “መጠጥ ጠጥቶ ካለመንጃ ፈቃድ በማሽከርከር ሰው ገጭቶ ከገደለ በኋላ ምንም እርዳታ ሳያደርግ አምልጧል” የሚል ነው። ዓቃቤ ሕግ በክሱ ላይ የጠቀሰው አንቀጽ በ1997 ዓ.ም. በወጣው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የወንጀል ሕግ፤ በቸልተኝነት ሰው መግደል የሚለውን አንቀጽ 543 ንዑስ ቁጥር 3 መተላለፍ የሚል ነው።

 

የቴዲ አፍሮ ጠበቃ አቶ ሚሊዮን አሰፋ ደንበኛቸው ቴዎድሮስ ካሳሁን በዋስ እንዲፈታና ጉዳዩን በውጭ ሆኖ እንዲከታተል ያቀረቡት አቤቱታ በዓቃቤ ሕግ ተቃውሞ ስለገጠመው በዋስትናው ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ።

 

ሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን 2000 ዓ.ም.

ፍርድ ቤቱ በዋስትናው ጥያቄ ላይ ትዕዛዝ ይሰጣል ተብሎ ሲጠበቅ፣ ዓቃቤ ሕግ ክሱን እንዲያሻሻል ትዕዛዝ አስተላለፈ።

 

ረቡዕ ሚያዝያ 15 ቀን 2000 ዓ.ም.

በዚህ ዕለት ዓቃቤ ሕግ ክሱን አሻሽሎ አቀረበ። ”ቴዲ አፍሮ መንጃ ፍቃድ ሳይኖረው ጥቅምት 23 ቀን ከለሊቱ በ7 ሰዓት ከአራት ኪሎ ወደ ካሳንችስ በሚወስደው መንገድ ሲያሽከረክር ለእግረኛ ቅድሚያ መስጠት ሲገባው ቅድሚያ በመከልከል ሙዋች ደጉ ይበልጣል የተባለን የ18 ዓመት ወጣት ገጭቶ ገድሏል። ከዚያም መርዳት ሲገባው ምንም እርዳታ ሳያደርግ አምልጧል” የሚል ሲሆን፣ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘም ከአምስት ዓመት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጣ የሚጠይቅ ነበር።

 

ቴዲ አፍሮ የእምነት ክህደት ቃሉን ሲጠየቅ ”ድርጊቱን አልፈፀምኩም ጥፋተኛም አይደለሁም” ሲል የእምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል። ዋስትናውን በሚመለከት ጠበቃውና ዓቃቤ ሕግ ክርክር ቢያደርጉም ማክሰኞ ሚያዚያ 21 ቀን 2000 ዓ.ም. ጠዋት የተሰየመው ችሎት ዋስትናውን ከልክሎታል።

 

ኀሙስ ግንቦት 14 ቀን 2000 ዓ.ም. የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች

ዓቃቤ ሕግ አሉኝ ካላቸው አራቱ ውስጥ ሦስቱን አቅርቦ አስመስክሩዋል። ሦስቱም የቀረቡት ምስክሮች ፖሊሶች ነበሩ።

 

የመጀመሪያው ምስክር ኮንስታብል ከበደ ወየሳ ሲሆን፣ ከዓቃቤ ሕግ፣ ከቴዲ ጠበቃ እና ከዳኛው ከተሰነዘሩለት ዋና፣ መስቀለኛ እና ማጣሪያ ጥያቄዎች ምስክርነቱን አስረድቷል። እንደዓቃቤ ሕግ የመጀመሪያ ምስክር አገላለጽ ከሆነ ጥቀምት 23 ቀን 2000 ዓ.ም.፣ ከሌሊቱ 7 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ላይ፣ በተለምዶ “ፊት በር” እየተባለ በሚጠራው አካባቢ፣ የጥበቃ ሥራ እየሠራ ባለበት ወቅት፣ አንድ አረንጓዴ የቤት መኪና፣ ግራና ቀኝ በሁለት ላዳ ታክሲ ታጅቦ በፍጥነት እየበረረች ትመጣለች፣ ምስክሩ በ20 ሜትር ርቀት ላይ ሆነው ይመለከታል። አንድ ሰው ደግሞ፣ ከቀበሌው አካባቢ (ከቀኝ ወደ ግራ) አስፋልቱን ወደ ቤተ መንግሥት ሲያቋርጥ፣ መሃል አስፋልት ላይ ይወድቃል። ያች ስትበር የነበረችው አረንጓዴ መኪና፣ የተኛውን ሰው ገጭታው ትሄዳለች። መኪናውን ሮጦ ይከተልና ታርጋ ቁጥሩን ይመዘግባል።

 

በአራት ኪሎ ግንብ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ፣ በሥራ ላይ የሚገኘውን የሥራ ባልደረባውን ጠርቶ፣ ወደ ወደቀው ልጅ ሲሄድ፣ የመጠጥ መንፈስ እንዳለውና ሕይወቱ እንደነበረች ተመልክቷል። ከዛም ከ5 ደቂቃ በኋላ ሕይወቱ አልፏል። ስልክ ደውሎም ጉዳዩን ለፖሊስ ማሳወቁን ገልጿል። በማግስቱም ትራፊክ ጽ/ቤት ሄዶ ቃሉን መስጠቱን፣ መኪናዋን እዚያ ሲያያት እንዳወቃት ገልጾ፣ ተከሳሹን ቴዲ አፍሮን ግን አላውቀውም ብሏል።

 

የሁለተኛው ምስክር ኮንስታብል ታምራት ዱላ ቃልም ተመሳሳይ ነበር። አማርኛ ቋንቋ አጥርቶ መናገር ባለመቻሉ የሚለው አይሰማም፣ በጣም እየፈጠነ የሚናገር በመሆኑም፣ ዳኛው “እንደው አስተርጓሚ የሚፈልግ ዓይነት ነገር እኮ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። ጠበቃውና ዓቃቤ ሕጉም ሲጠይቁ ዳኛው በመካከል እየገቡ ይጠይቁ፣ እንዲብራራም ያደርጉ ነበር። ይሄ ምስክር በተጠቀሰው ቀንና ሰዓት፣ ግንብ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የጥበቃ ሥራ እየሠራ እያለ፣ አንድ አረንጓዴ መኪና በሁለት ላዳ ታክሲዎች መካከል በከፍተኛ ፍጥነት እየበረረች ስትመጣ፣ ፊሽካ ነፍቶ ፍጥነቱን እንዲቀንስ ለማድረግ እንደሞከረ ገልጾ፤ ትንሽ ቆይቶ ጓደኛው ከሼራተን አካባቢ፣ በእጁ “ና! ና!” ብሎ እንደጠራውና፣ ስለተፈጸመው እንደነገረው፣ ከዛም ወደ ልጁ ሲሄዱ የልጁ ሕይወት እንደነበር፣ ከአምስት ደቂቃ በኋላ ደግሞ መጥፋቱን ገልጾ፣ ለፖሊስ ደውሎ እንደተናገረ መስክሯል። ስለሟች የአለባበሱንና የኑሮውን ሁኔታ እንዲናገር ሲጠየቅ፣ እዛ አካባቢ ለረጅም ጊዜ መሥራቱንና፣ ልጁ የጎዳና ተዳዳሪ መሆኑን ገልጾ፣ መጠጥ እየጠጣ ሲወድቅ እንደሚያውቀው ተናግሯል።

 

ሦስተኛ ምስክር ሆነው የቀረቡት የፕላን ምስክር ሲሆኑ፣ አደጋው ከደረሰ በኋላ በቦታው ተገኝተው ፕላን ማንሳታቸውን ተናግረዋል፣ ስለ ፕላኑም አስረድተዋል። ባነሱት ፕላን ላይ ስለተፃፈው ነገር፣ ከጠበቃው መስቀለኛ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። የታርጋ ቁጥሩን መዝግቤያለሁ ያሉት አንደኛው ምስክር፣ ፕላኑ ሲነሳ በቦታው መኖራቸውን አረጋግጠው ፈርመው እያለ፣ በዚሁ ፕላን ላይ ፕላን አንሺው ደግሞ “ፕላኑን ተመልከቼዋለሁ የሰሌዳ ቁጥሩ ያልታወቀ ተሽከርካሪ ሰው ገጭቶና ገድሎ ያመለጠ ስለሆነ፣ በማስረጃ ጭምር በአስቸኳይ ይጣራ” ብለው ጽፈዋል። በወቅቱም የሰሌዳ ቁጥር የያዘ የዓይን ምስክር ካለ፣ ለምን ይሄ ተፃፈ? በሚል ጥያቄ አቅርቧል። እንደ አሠራር የታርጋ ቁጥር የሚያሠፍሩት ገጭቶ ያላመለጠና ሹፌሩ እዛው ኖሮ በፕላኑ ላይ ሲፈርም እንደሆነ ገልጸዋል።

 

ጠበቃው ከእኝህ ምስክር ጋር ስለሟች አወዳደቅ፣ ስለ መኪናው አገጫጭ፣ በርካታ መስቀለኛ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን ስለ ግጭቱም ከኮንስታብሎቹ ጠይቄ የተረዳሁት ነው ያሉትን ፕላን አንሺው ሲገልጹ “ሟች ከጓደኛው ጋር እየተጓተተ አስፋልቱን በማቋረጥ ላይ እያለ ይወድቃል። በወደቀበት በዚያው ፍጥነት በመኪናው ተገጭቷል። ገጪው መኪናም ልጆቹ ሲያቋርጡ አይቷቸዋል” የሚል ነበር።

 

የምስክሮቹ ቃል፣ ከተሰማ በኋላ፣ ዓቃቤ ሕግ አንዱን ምስክር በአድራሻው ስላላገኘው ምስክሩ ለፖሊስ የሰጠው ቃል ከመዝገቡ ጋር እንዲያያዝለት ጠይቆ ተፈቅዶለታል።

 

ዓቃቤ ሕግ ያለው ማስረጃ፣ ምን እንደሚያስረዳለት አጠቃሎ እንዲያቀርብ ዳኛው ትዕዛዝ ሲሰጡ፣ ጠበቃው ከጊዜ አንፃር ምላሻቸውን እዛው ለመስጠት ተዘጋጅተው መምጣታቸውን በመግለጽ የተከራከሩ ቢሆንም፣ ጥያቄያቸው ተቀባይነት ባለማግኘቱ ዓቃቤ ሕግ በጽሑፍ አጠቃሎ የሚያቀርበውን የማስረጃ ዝርዝር ሂደት ለመጠባበቅ ለግንቦት 27 ቀን 2000 ዓ.ም. ተቀጥሯል።

 

ሦስቱም የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች የመረበሽ፣ የመደናገጥ፣ የመርበትበትና የመንተባተብ ሁኔታ ይታይባቸው የነበረ ሲሆን፣ አንዳንዴም ይሰጡት የነበረው ምስክርነት እርስ በእርሱ ይጋጭ ነበር። በተለይ ደግሞ ፖሊሶች ከመሆናቸው አንጻር ሁኔታቸው በችሎት የነበረው ተመልካች የምስክሮች ቃል በሚሰማበት ወቅት፣ ምስክሮች ለሚቀርብላቸው ጥያቄ የሚሰጡት ምላሽ በሚፈጥርባቸው ስሜት፣ የማጉረምረም ድምፅ ሲያሰሙ የነበረ ሲሆን ከዳኛም፣ ከፖሊስም ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።

 

ረቡዕ ግንቦት 27 ቀን 2000 ዓ.ም.

ዓቃቤ ሕግ በታዘዘው መሰረት ያቀረባቸው ስድስት የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ለችሎቱ ምን እንደሚያስረዱለት ያቀረበ ሲሆን፣ አንደኛ የአደጋ ቦታ ፕላን ሲሆን፣ ተከሳሽ የሚያሽከረክረው መኪና በቤተ መንግሥት አካባቢ ከላይ ሲመጣ ሟች ደጉ ይበልጣልን ከሩቁ ማየት ስለሚችል ከአደጋው ማትረፍ ይቻለው የነበረ ቢሆንም ሳያተርፈው መቅረቱን ያስረዳልኛል በማለት ያቀረበ ሲሆን፤ የተቀሩት አምስቱ ደግሞ መኪናውን የሚያሳይ ፎቶግራፍ (በትራፊክ ቢሮ አካባቢ)፤ ከምንሊክ ሆስፒታል የአስከሬን ምርመራ የም/ወረቀት (ኦሪጅናል ያልሆነና የመርማሪው ስም ኢሳያስ ብቻ ተብሎ በእጅ የተጻፈበትና የዶክተር ፊርማ ያላረፈበት)፤ አስከሬኑ ቀና ተደርጎ የተነሳ ፎቶግራፍ፤ መኪናው አደጋ ከማድረሱ በፊት ምንም አይነት የቴክኒክ ብልሽት ያልነበረው መሆኑን አስረድቷል።

 

የቴዲ አፍሮ ጠበቃም በተራው ዓቃቤ ሕግ ያቀረባቸው የማስረጃ ዝርዝር መግለጫዎች ተቃውሟል። ጠበቃው፤ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ማስረጃ ተከሳሽ በጎማ ሄዶበታል የሚል ሲሆን፣ የሟች አስከሬን የተገኘው ሰውነቱ ተቀጥቅጦና ተሰባብሮ ነው በማለት ተቃውሞውን ያቀረበ ሲሆን፣ እስከዛሬ በፍርድ ቤቶች ሕግ መሰረት የአስከሬን ምርመራ በሁለት ዶክተሮች ተመርምሮና ተፈርሞበት መቅረብ የሚገባው ኦሪጅናል የአስከሬን ምርመራ ውጤት በአንድ ኢሳያስ ተብሎ በቀረበ ኦሪጅናል ባልሆነ የምስክር ወረቀት መቅረቡ አግባብ አለመሆኑን አመላክቷል።

 

በተጨማሪም የቀረበው የፕላን ማስረጃ ያልታወቀ መኪና ገጭቶ ማምለጡን ከመግለጹ ውጭ የተከሳሽ መኪና ወይንም ተከሳሹ ገጭቶ ማምለጡን የማይገልጽ ሲሆን፣ የመኪናውን አይነትና ታርጋ ቁጥር ያልታወቀ መሆኑን ከማስረዳት ያለፈ የተከሳሽ መኪና ስለመግጨቱ የቀረበ የፕላን ማስረጃ ባለመኖሩ ደንበኛዬን ጥርጣሬ ውስጥ የሚከት ነገር ስለሌለ በነፃ ይሰናበትልኝ በማለት ጠይቋል።

 

ዳኛውም "ኦሪጅናል የአስከሬን ምርመራ ወረቀት ይቅረብ" ሲሉ፣ የተከሳሽ ጠበቃ "ዓቃቤ ሕግ የለኝም ብሏል ባለው ውሳኔ ይሰጥ" ብሎ ሊያስረዳ ቢሞክርም፤ ዳኛ ልዑል "ጠበቃ ስነሥርዓት! አንዴ ትዕዛዝ ተሰጥቷል" በማለት ከገሰጹ በኋላ፤ "አሰራር ነው" በማለት ተከሳሽ ቴዲ አፍሮ መከላከል ሳያስፈልገው በነፃ እንዲሰናበት ወይንም ደግሞ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ማስረጃ ጥርጣሬ ውስጥ የሚጥለው ከሆነ ይከላከል የሚል ብይን ለመስጠት ለሰኔ 27 ቀን 2000 ዓ.ም. በመቅጠር ችሎቱን በትነዋል።

 

ዓርብ ሰኔ 27 ቀን 2000 ዓ.ም.

ዓቃቤ ሕግ ኦሪጅናሉ ነው በማለት ያቀረበው የሰነድ ማስረጃ ሟች ደጉ ይበልጣል በ22/2/9 ዓ.ም. ሞቶ በ23/2/99 ዓ.ም. አስከሬኑ ተመርምሯል የሚል ሲሆን፣ ቴዎድሮስ የተከሰሰው በ23/2/99 ከሌሊቱ 8 ሰዓት ሟቹን ገድሎ አምልጧል የሚል ነው በመሆኑ ጠበቃው ደንበኛቸው በነፃ እንዲሰናበት ይጠይቃል። ዓቃቤ ሕግ የምኒልክ ሆስፒታል ስህተት እንጂ የእኔ ስህተት አይደለም፤ ማስተካከያ አመጣለሁ በማለቱ ማስረጃው ማስተካከያ ተደርጎበት ይቀርባል።

 

ለሁለተኛ ጊዜ ማስተካከያ ተደርጎበት የመጣው የሰነድ ማስረጃ ከዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ መቆጣጠሪያ እና ምርመራ መምሪያ በሸኚ ደብዳቤ የተላከ ሲሆን፣ ደብዳቤው "በ12/10/2000 ዓ.ም. በደብዳቤ ቁጥር 20307/ወ/መ/42 ሟች ደጉ ይበልጣል በ22/02/99 ዓ.ም. ሕወታቸው አልፎ በ23/02/99 ዓ.ም. የአስክሬን ምርመራ የተደረገላቸው መሆኑን የሚገልፅ በቁጥር 856/44/99 በ04/03/99 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ የላክንላችሁ የአስክሬን ምርመራ ውጤት ማስተካከያ ተደርጎ እንዲላክላችሁ መጠየቃችሁ ይታወቃል።

 

"በመሆኑም ሟች ደጉ ይበልጣል በ23/02/99 ዓ.ም. ሕወታቸው አልፎ በዕለቱ አስክሬናቸው ወደ አስክሬን ክፍል ገብቶ የአስክሬን ምርመራው በ24/02/99 ዓ.ም. የተደረገላቸው መሆኑን እያረጋገጥን፣ ስህተቱ የተከሰተው በወቅቱ የነበሩት የአስክሬን መርማሪ ባለሙያ ወደ ዋናው መዝገብ በሚያሰፍሩበት ወቅት በተከሰተ ግድፈት መሆኑን እየገለጽን ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ እንጠይቃለን።" የሚል ነው።

 

ከዚህ ሸኚ ደብዳቤ ጋር ተያይዞ የተላከው የአስከሬን ምርመራ የምስክር ወረቀት ሟች ደጉ ይበልጣል በ23/2/99 ዓ.ም. አስከሬኑ ወደ ምርመራ ክፍሉ ገብቶ በ24/2/99 ዓ.ም. ተመርምሮ ወጥቷል የሚል ነው።

 

የቴዲ ጠበቃም ደንበኛው የተከሰሰበት ቀንና ሟች የሞተበት ቀን ተመሳሳይ ባለመሆኑ ክሱ ውድቅ እንዲደረግና ደንበኛው እንዲለቀቅለት ቢጠይቅም፤ ዳኛው "መመርመር አለበት" በማለት ለሣምንት ቀጠሮ ሰጥተው ችሎቱን ከበተኑ በኋላ በጽ/ቤት በኩል የምኒልክ ሆስፒታል ባለሙያ ችሎት ተገኝተው ጉዳዩን እንዲያስረዱ ያዛሉ።

 

ዓርብ ሐምሌ 4 ቀን 2000 ዓ.ም.

ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) በቀረበበት ክስ ላይ ሁለት ዓይነት ቀን ያለው የሰነድ ማስረጃ ሰጥቷል የተባለው የዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ባለሙያ ፍርድ ቤት ቀርቦ እንዲያስረዳ በታዘዘው መሰረት የኩባ ዜግነት ያላቸው የአስክሬን መርማሪ ፍ/ቤት ቀርበው የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ ከውጭ በመጣ አስተርጓሚ ሥራውን የሠራው ፍርድ ቤቱ፣ ባለሙያውን ስለ ሟች አስክሬን ጠይቀዋል። አስክሬኑን የመረመሩት ሐኪም ሴት መሆናቸውንና አሁን አገር ውስጥ እንደሌሉ ገልጸው፣ አሁን በቦታው ላይ ያሉት ራሳቸው እንደመሆናቸው ጉዳዩን ማጣራታቸውን አስረድተዋል። የመጀመሪያዋ ሐኪም አስክሬኑን ሲመረምሩ ሟች ደጉ ይበልጣል በ23/02/99 ዓ.ም. ሕወታቸው አልፎ በዕለቱ አስክሬናቸው ወደ አስክሬን ክፍል ገብቶ የአስክሬን ምርመራው በ24/02/99 ዓ.ም. ተደርጎላቸዋል የሚል ማስረጃ መጻፋቸውንና ይኸው ማስረጃ ወደ መዝገብ ሲገለበጥ ሟች ደጉ ይበልጣል በ22/2/99 ዓ.ም. አስከሬኑ ገብቶ በ23/2/99 ዓ.ም. ተመርምሮ ወጥቶአል ተብሎ መጻፉን መስክረዋል።

 

ማስረጃው ከመዝገቡ ላይ ተገልብጦ ለፖሊስ መሰጠቱን ከተናገሩ በኋላ ፖሊስ ይህንኑ ማስረጃ እንዲስተካከልለት ሲጠይቅ ከመጀመሪያዋ ሐኪም የእጅ ጽሑፍ ላይ አይተው ሟች ደጉ ይበልጣል በ23/02/99 ዓ.ም. ሕወታቸው አልፎ በዕለቱ አስክሬናቸው ወደ አስክሬን ክፍል ገብቶ የአስክሬን ምርመራው በ24/02/99 ዓ.ም. ተደርጎላቸዋል የሚል ማስተካከያ እንደሰጡ ተናግረዋል።

 

ቴዲ አፍሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ችሎት የተናገረ ሲሆን፣ "የተከበረው ፍርድ ቤት ስለተሰጠኝ ዕድል በጣም አመሰግናለሁ! እኔ የማምነው ይህን ሁሉ ሰው በሚያይ እግዚያብሔር ነው። ግን አንድ ነገር መናገር እፈልጋለሁ። እኔ አንድም ሰው አልገደልኩም ሰውም አልገጨሁም። ነገር ግን በማላውቀው ነገር ሰብዓዊ መብቴ ተገፍፎ ቅማል እየበላኝ ሦስት ወር ታስሬያለሁ። ፍርድ ቤቱንም ሆነ የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት የምጠይቀው ጉዳዩን በሚገባ ተረድተው በነፃ እንዲሰናብቱኝ ነው።" ሲል ተደምጧል። በዚህን ሰዓት ወላጅ እናቱን ጨምሮ በርካታ ሰው ድምፁን አውጥቶ ሲያለቅስ ተሰምቷል። ዳኛው ጉዳዩን ገለልተኛ ሆነው በማየት ላይ መሆናቸውን አስረድተው የግራ ቀኙን ክርክር መርምረው ለሰኞ ሐምሌ 14 ቀን 2000 ዓ.ም. በነፃ ይሰናበት ወይም ደግሞ ይከላከል የሚለውን ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ሰጥቶ ተበትኖ ነበር።

 

ያልተለመዱ ሁነቶች - በቴዲ ችሎት

- የቴዲ አፍሮ ጉዳይ ፖለቲካዊ መምሰሉና ጠበቃው አቶ ሚሊዮን አሰፋ የኢህአዴግ ደጋፊና የምርጫ ቦርድ ጠበቃ ሆኖ፣ የቅንጀት አመራሮች እስር ቤት በነበሩበት ወቅት እስሩን ደግፎ ሞት ሊፈረድባቸው ይገባል እያለ በመንግሥት ራዲዮና በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በየቀኑ መግለጫ ሲሰጥ የነበረ ጠበቃ መሆኑ፤

 

- ሁለተኛ ወንጀል ችሎት የነበሩትና ለሁለት ዓመታት የዘለቀውንና የቅንጅት አመራሮች ... የተከሰሱበትን ችሎት በቀኝ ዳኝነት ሲያስችሉ የነበሩት አቶ ልዑል ወ/ማርያም በድንገት 8ኛ ወንጀል ችሎት መገኘት፤

 

- ምኒልክ ሆስፒታል በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ኦርጅናል የአስከሬን የምርመራ ውጤትን 'ተሳስቷል' በሚል መቀየሩ፤

 

- ችሎት በሚኖርበት ጊዜ በርካታ ቁጥር ያላቸው ደህንነቶች ችሎቱን ማጨናነቃቸውና ችሎት ተከታታዩን ሰው ማስጨነቃቸው፤

 

- የቅንጅት አመራሮችን ሲጠብቁ የነበሩ የፌደራል እና የአዲስ አበባ ፖሊሶች ሳይታክቱ በችሎት በመገኘት ጥብቅ ቁጥጥር ማድረጋቸው፤

 

- ቃሊቲ ከገባ በኋላ ለብቻው መታሰሩ፤

 

- ከተወሰኑ ሰዎች በስተቀር ማንም እንዳይጠይቀው መከልከሉ፤ በመኪና ሰው ገጭተሃል በሚል ተጠርጥሮ ለታሰረ ሰው ያልተለመዱ ድርጊቶች ናቸው።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ