ESAT in Stockholm, 28 Feb. 2015ለኢሳት መዝሙር ተበረከተ

Ethiopia Zare: ቅዳሜ የካቲት 21 ቀን 2007 ዓ.ም. (ፌብሪዋሪ 28 ቀን 2015 ዓ.ም.) በስዊድን የተደረገው የኢሳት መርጃ ዝግጅት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁ ተገለጸ። ዝግጅቱ ከቀኑ ሰባት ሰዓት (13፡ 00) የተጀመረ ሲሆን፣ የዕለቱን ዝግጅት የመሩት ወ/ሮ መቅደስ ወርቁ የስዊድን የኢሳት ድጋፍ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና አቶ በረከት ንጉሱ ነበሩ።

ESAT in Stockholm, 28 Feb. 2015

በቦታው ላይ ዝግጅቱን ለመካፈል የመጡ በርካታ ኢትዮጵያውያን የተገኙ ሲሆን፣ በክብር እንግድነት የተገኙት ደግሞ ታዋቂዎቹ የኢሳት ጋዤጠኞች መሳይ መኮንን፣ አበበ ቶላ (አቤ ቶክቻው) እንዲሁም ስዊድናዊው ጋዜጠኛ ዮሀን ፐርሾን ናቸው። ጋዜጠኛ ዮሀን ኢትዮጵያ ውስጥ በእስር ከተንገላቱት ስዊድናውያን ጋዜጠኞች ውስጥ አንዱ መሆናቸው ይታወቃል።

ESAT in Stockholm, 28 Feb. 2015

ዝግጅቱን በጸሎት የከፈቱ በክርስትና ኃይማኖት በኩል ቄስ ፍስሀ ተስፋዬ፣ ሙስሊሙን በመወከል ደግሞ የተናገሩት ሀጂ ሁሴን ሺፋ ሲሆኑ፤ የጸሎቱ ሥነሥርዓት ካበቃ በኃላ ወ/ሮ መቅደስ ወርቁ ስለስዊድን የኢሳት ድጋፍ ኮሚቴ አቅም መጎልበት፣ ገቢ ማስገኛ ፕሮጀክት ስለመንደፍ እና ኢሳት ከተመዘገበበት ክፍል ጋር የስራ ትብብር ስለማድረጉ፣ እንዲሁም የድጋፍ ኮሚቴው የሚገለገልበት ድረገጽ ስለ መከፈቱ ገልጸው፤ ወደፊትም ስለተያዙት እቅዶች ማብራሪያ ሰጥተዋል። በመጨረሻም ለኢሳት አሰራር ያልተቋረጠ ትብብር እያደረገ ላለው ለስዊድን የኢትዮጵያ ድምጽ ራድዮ እና ለፎከስ ቴሌቭዥን ምስጋና አቅርበዋል።

ESAT in Stockholm, 28 Feb. 2015

ቀጥሎ የእንግዶቹን ማንነት በሚገልጽ ትውውቅ ከተደረገ በኋላ ገጣሚ ማትያስ ከተማ (ወለላዬ) «... ባቡር ተመረቀ» በሚል ርዕስ ያገራችንን ሁኔታ የሚገልጽ ምጸት የተላበሰ ግጥም አቅርቧል። ከወለላዬ በተጨማሪ አቶ ማትያስ እንግዳዬ ደግሞ ኢሳትን የሚያወድስ ግጥም አቅርበዋል።

ESAT in Stockholm, 28 Feb. 2015

ከዚህ በኋላ ስዊድናዊው ጋዜጠኛ ዮሀን ፐርሾን ንግግር አድርጓል። በንግግሩም ኢትዮጵያ ውስጥ በእስር የቆየበትን ጊዜ የሚገልጽ «438 dagar» (438 ቀናት) በሚል በስዊድን ቋንቋ ከጋዜጠኛ ማርቲን ሺቤ ጋር የጻፉት መጽሐፍ በእንግሊዘኛ ተተርጉሞ ለስርጭት መብቃቱን አብስረዋል። አዲስ የጀመሩትም ”ብላንክ ስፖት” የተሰኘ ፕሮጀክት (https://www.blankspotproject.se) መኖሩን አሳውቀዋል።

ከዚህ ቀጥሎ የቀረበው በአይነቱ አዲስ የሆነው ለኢሳት የተበረከተው «ኢሳት የኛ ፋና» የተባለው የኢሳትን ግዙፍ ስራ የሚገልጽ መዝሙር ሲሆን፣ መዝሙሩ በሴቶችና በወንዶች ዘማርያን በሙዚቃ ታጅቦ ለመጀመሪያ ጊዜ ለህዝብ ቀርቧል።

ESAT in Stockholm, 28 Feb. 2015

የዚህን መዝሙር ግጥም የጻፈው ገጣሚ ማትያስ ከተማ (ወለላዬ) ሲሆን፣ ዜማውን ያቀናበሩት ደግሞ አቶ ሚካኤል ወንድማገኝ (መርሶ) መሆናቸውን ለማወቅ ችለናል። የመዝሙሩን ሃሳብ አፍላቂና አስተባባሪ ወ/ሮ መቅደስ ወርቁ እንደሆኑ በተጨማሪ ለመረዳት ችለናል። ግጥሙን ለደረሱት፣ ዜማውን ላቀናበሩት፣ ለዘማሪያኑ እና በመዝሙሩ ዙርያ ተሳትፎ ላበረከቱት የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል። በመጨረሻም የመዝሙሩ ዋና ቅጂ ለጋዜጠኛ መሳይ መኮንን ለኢሳት እንዲያደርስ በአደራ የተሰጠ ሲሆን፣ አቶ አለማየሁ በቀለ ደግሞ በበኩላቸው ያዘጋጁት የኢሳት አርማ እና ጹሁፍ ያለበት በጨርቅ ተሰርቶ የተወጠረ የጥበብ ሥራ ለኢሳት ድጋፍ ኮሚቴ በስጦታ አበርክተዋል።

ESAT in Stockholm, 28 Feb. 2015

ቀጥሎ መድረኩን የያዘው ጋዜጠኛ አበበ ቶላ (አቤ ቶክቻው) ሲሆን፣ አቤ በተለመደ ጣፋጭ አቀራረቡ «ሥልጣንና አይሮፕላን እላይ ላይ ሆነው ሲያዩት ደስ ይላል» በሚል መርኅ-ሀሳብ የኢትዮጵያን ፖለቲካ የሚነካ መጣጥፍ አቅርቧል። ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን ደግሞ ለኢሳት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ያለውን ችግር በማብራራት የገለጸ ሲሆን፣ የኢሳት ትልቁ ስቱዲዮ ከኢሳት ግዙፍነት ጋር የማይመጣጠን መሆኑን አሳውቋል።

ስለዚህ ኢሳትን ለማጠናከር ሁላችንም መስራት ይገባናል ብሏል። እንዲሁም በኤርትራ ቆይታው ጊዜ የተቀነባበረውን ምስል ለታዳሚው አሳይቷል። ጋዜጠኛ ሳዲቅ አህመድ በስካይፕ ቀርቦ የቻይናና፣ የበርማ እንዲሁም የወያኔ ኢትዮጵያ ሶሻሊስታዊ አገዛዞች ያላቸውን መመሳሰልና የአስተዳደር ሁኔታ በማብራራት ገለጻ አድርጓል።

ESAT in Stockholm, 28 Feb. 2015

ከሳዲቅ ንግግግር ማብቂያ በኋላ በአቤ ቶክቻው አጫራችነት የጣይቱ ሆቴል የቀድሞ ምስል ለጨረታ የቀረበ ሲሆን፣ ጨረታው በደመቀ ሁኔታ ከፍተኛ ፉክክር ተደርጎበት በ64 ሽህ የስዊድን ክሮነር ለአሸናፊዋ ለወ/ሮ የትምወርቅ ተሰጥቷል። መጨረሻ ባለው ሰዓት ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን በኤርትራ የትጥቅ ትግል ስለመኖሩ፣ የትግል እንቅስቃሴውን የሚያሳይ ቪድዮ አሳይቷል። በቪዲዮው ላይ ከተለያዩ ታጋዮች ጋር የተደረጉ ቃለምልልሶችና እንቅስቃሴ የታየ ሲሆን፣ ስለአንዳንድ ታጋዮችም የጀግንነት ስራ ማብራሪያ ሰጥቷል። ከዚህ በኋላ ዝግጅቱ ተጠናቆ ህዝቡ ተሸኝቷል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ