አዲስ አበባ ፀጥ እንዳለች ውላ አመሸች
Voters queue early in the morning to cast their votes in Ethiopia’s general election, Sunday May 24, 2015, in Addis Ababa, Ethiopia. Ethiopians voted Sunday in national and regional elections, the country’s first since the 2012 death of its longtime leader, but the ruling party is expected to maintain its iron-clad grip on power. (Mulugeata Ayene/Associated Press)

Ethiopia Zare (እሁድ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. May 24, 2015)፡-  ዛሬ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት የተካሄደውና የተጠናቀቀው ምርጫ ከዚህ ቀደም ከተደረጉት አራት ምርጫዎች እጅግ የቀዘቀዘ መሆኑ ታወቀ። ተቃዋሚዎች ፓርቲዎች በታዛቢነት የመደቧቸው ሰዎች ምርጫውን እንዳይታዘቡ ጫና እንደተደረገባቸው ብሎም እንደታሰሩባቸው ገልጠዋል፤ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ በምርጫ ከተሳተፉት ፓርቲዎች ምንም አይነት ቅሬታ እንዳልደረሰው ገልጧል።

የኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ ዘጋቢ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ ከተማዋ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ፀጥ እንዳለች ውላ ማምሸትዋን ገልጠውለታል። የመንግሥት መገናኛ ብዙኀን በተደጋጋሚ ሠላማዊ ምርጫ እያሉ ስለነበር የአገሪቱ ሕዝብ ረብሻ ይነሳ ይሆናል የሚል ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደነበር ጠቁመዋል። በሌሎች ክልሎች የሚገኙ ዘመዶቻቸው ሳይቀሩ የዚህ ስጋት ሰለባዎች ከመሆናቸው የተነሳ ከክፍለሀገር ድረስ በመደወል አዲስ አበባ ያሉ ዘመዶቻቸውን ከቤት እንዳይወጡ ማስጠንቀቃቸውን ለማወቅ ችለናል።

በምርጫ ዕለት አዲስ አበባን ጨምሮ የተለያዩ ከተሞች ለምን ቀዘቀዙ? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ግለሰቦች ከሰጡዋቸው ምክንያቶች ውስጥ፤ ሕዝቡ ከዚህ ምርጫ ምንም የመንግሥት ለውጥ እንደማይሆን በመረዳቱ ነው የሚለው አብዝኀው የሚስማማበት እንደሆነ ለመረዳት ችለናል።

በታዛቢዎቻቸው ላይ ጫና እና እስር እንደደረሰባቸው የገለጡት ሰማያዊ ፓርቲ፣ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ፣ መድረክ፣ መኢአድ እና ኢዴፓ ናቸው። በአዲስ አበባ በሚገኙት የቦሌ፣ የአዲሱ ገበያ እና ሌሎች የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ የሰማያዊ ፓርቲ ታዛቢዎች ምርጫውን እንዳይታዘቡ መባረራቸውን፤ በሐዋሳ ከተማ ሦስት አራተኛ የሚሆኑ ታዛቢዎቹ መታሰራቸውን የገለጡት የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች፤ በሐዋሳ አንዳንዶቹ በቁም እስር መልክ ቤታቸው በሚሊሺያ መከበቡን ገልጠዋል። ከዚህም ሌላ በኦሮሚያ፣ በደቡብ እና በአማራ ክልል ታዛቢዎቻቸው መባረራቸውን አስታውቀዋል።

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ በሐዋሳ ታዛቢዎቹ ከምርጫ ጣቢያዎች እንደተባረሩበት ገልጧል። መድረክ በበኩሉ በዚያው ከተማ ስድሳ በመቶ የሚሆኑ ታዛቢዎች እንደታሰሩበት አልሸሸገም።

ኢዴፓ በበኩሉ ሁለት የምርጫ ታዛቢዎቹ በባህር ዳር ከተማ ፎቶራፍ የሌለው መታወቂያ ነው የያዛችሁት ተብለው መባረራቸውን ገልጧል። ከነዚህ ፓርቲዎች በተጨማሪ፣ መኢአድ በሰሜን ሸዋ በታዛቢዎቹ ላይ በደረሰባቸው ወከባ እና ጫና ምክንያት ታዛቢዎቹ በምርጫ ጣቢያዎች ተገኝተው መታዘብ እንዳልቻሉ ገልጧል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ይፋዊ አቤቱታና ቅሬታ ከየትኛውም ፓርቲ እንዳልደረሰው አስታውቋል። 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!