ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ፊደል በላፕቶፕና በዲስክቶፕ ተቀርጾ አገልግሎት መስጠት ቻለ

The first Amharic, Geez laptop

Ethiopia Zare (ዓርብ ጥር 6 ቀን 2008 ዓ.ም. January 15, 2016)፡- ጋዜጠኛና ፀሐፊ ገነት አየለ የኢትዮጵያ ፊደላት እንደሌሎቹ የቋንቋ ፊደላት በላፕቶፕና በዴስክቶፕ ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀርጸው ለተጠቃሚዎች አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ መቻላቸውን ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ችለናል። ይኸው የመጀመሪያው በኢትዮጵያ ፊደል የሚጽፍ ኮምፒዩተር በገበያ ላይ መዋሉ ታውቋል።

በዚህ ወይዘሮዋ በጥቅም ላይ እንዲውል ባደረጉት ኮምፒዩተር በቀጥታ የኢትዮጵያን ፊደላት በመምታት መጻፍ እንዲቻል ከማድረጋቸውም በላይ በእንግሊዘኛው ቋንቋ ፊደል በምንጠቀም ጊዜ ሁለቴና ሦስቴ ከምንመታቸው ፊደላት እንድንድን በማድረጋቸው እጅግ ብዙ ጽሁፍ በአጭር ጊዜ ለመጻፍ እንድንችል መንገዱን ከፍተዋል። እንዲሁም የአማርኛ ፊደላችን እተገቢው ቦታ ላይ በማረፋቸው ቋንቋችን ለወግ ማዕረግ በመብቃቱ ወ/ሮ ገነትን ሲያስመሰግን ተጠቃሚው ኩራትና ደስታ እንዲሰማው አድርጓል።

Genet Ayele ጋዜጠኛና ፀሐፊ ገነት አየለወ/ሮ ገነት ስለዚሁ ጉዳይ ሲያስረዱ ለታሪካችንና ለቋንቋችን ካለኝ ፍቅር በመነሳት ለብዙ ምዕተ ዓመታት የበለጸገውን ታሪካችንን ብቻ ሳይሆን ቋንቋችንንም የበለጠ ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሳደግ በመቻሌ ከፍ ያለ ደስታ ይሰማኛል በማለት ገልጸዋል። በዚህ ኮምፒዩተር በመጠቀም መጻፍና መማር በቀላሉ እንዲቻል፣ ፋይል ለማድረግ፣ መረጃ ለመለዋወጥና ለማስተላለፍም እንዲመች በሌሎች ቋንቋዎች መሠራት የሚቻለው በራሳችን ቋንቋ እንዲሠራበት መንገዱ መቀየሱን አብራርተዋል።

በተጨማሪም ብዙ የአማርኛ ጽሑፍ ክምችቶች በኢንተርኔት ውስጥ ተበራክተው እንዲቀመጡ የሚያግዙ የአማርኛ ላይብረሪ እንዲኖር የራሳቸውን ድርሻ ማበርከታቸውን ገልጸው፤ ለቋንቋችን መስፋፋትና መበልጸግ ሁላችንም የራሳችንን ድርሻ ማበርከትና በጉዳዩም ልንተጋበት የሚገባን መሆኑን አስገንዝበዋል።

ይኽንኑ በኢትዮጵያ ቋንቋ የሚሠራ የመጀመሪያውን ኮምፒዩተር ለማዘዝም ሆነ ስለአጠቃላይ የፈጠራ ሥራው የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢትዮፓስ የተሰኘውን ድረ ገጽ http://ethiopass.visascol.com በመጎብኘት የበለጠ መረጃ ማግኘት እንደሚቻል ለመረዳት ችለናል።

ጋዜጠኛና ፀሐፊ ገነት አየለ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የእንግሊዘኛ ቋንቋ ዝግጅት ክፍል የሠሩ ሲሆን፣ ቀጥለውም ገነት ኢንተርፕራይዝን በማቋቋም ዝነኛውን “ቤዛ” ጋዜጣ አሳታሚ ነበሩ። “ገነት” የተሰኘውን የመጀመሪያው የሴቶች ጋዜጣ በአሳታሚነት እና በዋና አዘጋጅነት መስራታቸው ይታወቃል። ከቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ ከሌ/ኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማርያም ጋር በግንባር በመገናኘት ቃለ መጠይቅ አድርጋላቸው “የሌተናንት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማርያም ትዝታዎች” በሚል ርዕስ ሁለት መጻሕፍትን አሳትመዋል።

ወ/ሮ ገነት አየለ ነዋሪነታቸው በፈረንሣይ ዋና ከተማ በፓሪስ ሲሆን፣ አሁን ባሉበት ቦታ ከኢትዮጵያ ስነጽሑፍ ጋር ያልተለዩና በተለይ ቋንቋና የሀገራችንን ታሪክ በተመለከተ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ተሳትፎቸውን በማበርከት ላይ የሚገኙ ናቸው።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!