Ethiopia Zare (ዓርብ ሐምሌ 25 ቀን 2000 ዓ.ም. August 01, 2008)፦ በሙስና ወንጀል ተከሰው ፍርድ ቤት ለሰባት ዓመታት ታስረው ከነበሩት ሦስቱ ወንድማማቾች ብቻውን ቀርቶ የነበረው አቶ አሰፋ አብርሃ በትናንትናው ዕለት ከእስር የተለቀቀ መሆኑን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች አረጋገጡ።

 

የአቶ ስዬ አብርሃ ወንድም አቶ አሰፋ አብርሃ የቀድሞው የመንግሥት ልማት ድርጅት ሥራ አስኪጅ የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱ በነበረው ሥልጣን ተጠቅሞ የዱቄት ፋብሪካዎችንና ጣይቱ ሆቴልን ተደራድሮ አሽጡዋል በሚል እና ከወንድሙ ከአቶ ስዬ ጋር ሆኖ ከአሚቼ ኩባንያ ለወንድማቸው ለአቶ ምህረትአብ አብርሃ መኪናዎችን በቅናሽ ገዝተዋል፣ መኪናው የተገዛበትን ገንዘብ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከመመሪያ ውጪ ብድር እንዲገኝ አድርገዋል የሚል ነበር።

 

ወንድማማቾቹ ከሰባት ዓመት በፊት በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በመጀመሪያ የቀረበውን ክስ አሻሽለን እናቀርባለን በሚል ክርክሩ ሳይጀመር ከቆዩ ከሰባት ወራት ቆይታ በኋላ ክሱ ተመስርቶ ክርክር የቀጠለ ሲሆን፣ የክርክሩ ሂደት ስድስት ዓመት ፈጅቷል።

 

በመጨረሻ በ1999 ዓ.ም. ክሱ የፍርድ ውሳኔ ያገኘ ሲሆን፣ አቶ ስዬ አብርሃ አቶ ምህረትአብ አብርሃና ጣይቱ ሆቴልን የገዛው የእህታቸው ባል አቶ ፍጹምዘአብ አስግዶም ቢፈረድባቸውም የፍርድ ጊዜያቸውን በእስር ስለጨረሱት ከአንድ ዓመት ከሃያ ቀን በፊት ተለቀዋል።

 

አቶ አሰፋ አብርሃ 9 ዓመት ተፈርዶበት የነበረ ሲሆን፣ ለሰባት ዓመታት በእስር ቤት ከመቆየቱም በላይ ከተፈረደበት ጊዜ ጀምሮ አመክሮ እንዲሰጠው ሲጠይቅ የነበረ ቢሆንም፤ እስካሁን ሊሰጠው ሳይችል ቀርቷል። ምንጮች እንደገለጹት በትናንትናው ዕለት በሚገኝበት አዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ያሉ ፖሊሶች በድንገት መጥተው ዕቃህን ጠቅልለህ ውጣ ሲሉ ከእስር ቤት ማሰናበታቸው ታውቋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ