ፖሊስ በሕገወጥ መንገድ ሰዎችን የሚያሸጋግሩ አሉ ብሎ ይጠረጥራል

Ethiopian Airlines 787 dreamliner የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን (Foto: STEFAN MATTSSON)

Ethiopia Zare (ሰኞ የካቲት 28 ቀን 2008 ዓ.ም. Mar. 01, 2016)፡- ከአዲስ አበባ ሌሊት ተነስቶ ዛሬ ጠዋት በስዊድን መናገሻ ስቶክሆልም በሚገኘው የአርላንዳ አየር ማረፊያ ባረፈው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን የዕቃ ኮንቴይነር ውስጥ የተደበቀ የ27 ዓመት ዕድሜ ያለው አንድ ሰው መገኘቱን ፖሊስ ገለጸ። ይኸው ግለሰብ በስዊድን ጥገኝነት መጠየቁ ታውቋል። ፖሊስ በሕገወጥ መንገድ ሰዎች የሚያሸጋግሩ ወገኖች እንዳሉ ጥርጣሬ አለኝ፣ ጉዳዩን እያጣራኹ ነው አለ።

አውሮፕላኑ ካረፈ ከሁለት ሰዓት በኋላ ወደ አምስት ሰዓት ተኩል (11፡30) አካባቢ የአርላንዳ አየር ማረፊያ ሠራተኞች ግለሰቡን በኮንቴይነሩ ውስጥ ተደብቆ እንዳገኙት የገለጸችው የስቶክሆልም ፖሊስ የፕሬስ ኃላፊ የሆነችው ካሪና ስካገርሊንድ ስትሆን፣ ግለሰቡ በተገኘበት ሰዓት ተዳክሞ የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ሰዓት ግን በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አክላ ገልጻለች።

10 ሰዓት ከ25 ደቂቃ በላይ በሚፈጀው ከአዲስ አበባ ስቶክሆልም በረራ ግለሰቡ ተደብቆበት የነበረው ኮንቴይነር የአየር ግፊት መቆጣጠሪያ የተገጠመለት በመሆኑ የሚተነፍሰው አየር ስላገኘ በሕይወት ለመገኘት መቻሉን የገለጸችው ካሪና፣ እንዲህ ያለ ነገር ያልተለመደ መሆኑን ተናግራለች። በእርግጥ እንዲህ ያለውን ነገር ሊያደርግ የሚችለው ይሄ የአየር ግፊት መቆጣጠሪያ እንዴት እንደሚሠራ በትክክል የሚያውቅ ወገን መሆን አለበት ስትል አክላ ተናግራለች። ጉዳዩንም ፖሊስ እንደሚያጣራ አልሸሸገችም።

ከአዲስ አበባ ስቶክሆልም በረራ

አውሮፕላኑ ከአዲስ አበባ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከሌሊቱ 7 ሰዓት ከ10 (01፡10 ሰዓት) ተነስቶ ስቶክሆልም ከመድረሱ በፊት በኦስትሪያ መናገሻ ቪየና በመሃሉ ማረፉ ታውቋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ይኸው አውሮፕላን ስቶክሆልም አርላንዳ አየር ማረፊያ ጠዋት ለአራት ሩብ ጉዳይ (09፡35 ሰዓት) ላይ አርፏል።

ፖሊስ በሕገወጥ መንገድ ሰዎችን የሚያሸጋግሩ አሉ ብሎ ይጠረጥራል

ፖሊስ የግለሰቡን ለስዊድን ኢሚግሬሽን ባለሥልጣን መስሪያ ቤት አሳልፎ የሰጠ ቢሆንም፣ በዚህ ጉዳይ ላይ በሕገወጥ መንገድ ሰዎችን የሚያሸጋግሩ ወገኖች እጅ ሊኖርበት ይችላል የሚል ጥርጣሬ እንዳለው ታውቋል።

ፖሊስ በጉዳዩ ላይ መረጃ እና ማስረጃ እንደሚሰበስብ፣ እንዲሁም ግለሰቡን እንደሚያነጋግር ካሪና ገልጻለች። ግለሰቡ እንዴትና ለምን በኮንቴይነሩ ውስጥ ተደብቆ እንደመጣ ለጊዜው ፖሊስ ባያውቅም፤ በትክክል ስለጉዳዩ ማጣራት እንደሚደረግ ገልጻለች። በመጨረሻም ኮንቴይነሩ ለምን አየር ማረፊያ ውስጥ እንደተከፈተ የታወቀ ነገር እንደሌለ ሳትጠቁም አላለፈችም።

በስቶክሆልም ይኽ ሁለተኛው መሆኑ

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ነሐሴ 8 ቀን 2007 ዓ.ም. (ኦገስት 14 ቀን 2015 እ.ኤ.አ.) አንድ የ25 ዓመት ኢትዮጵያዊ በሻንጣ መጫኛ ውስጥ ተደብቆ ከአዲስ አበባ ስቶክሆልም መግባቱ ይታወቃል። ግለሰቡ ከአዲስ አበባ ወደ ስቶክሆልም የበረረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ቦይንግ 787 ድሪምላይነር የሻንጣ ማስቀመጫ ውስጥ የተገኘው የኦርላንዳ አየር ማረፊያ ሠራተኛ የሆነው አልድሪን ዘካይ ሲሆን፣ እሱም በስዊድን ጥገኝነት ጠይቆ ነበር። ግለሰቡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኛ እንደነበር ታውቋል።

በወቅቱ የአርላንዳ ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ ስቴፋን ፋርዲግስ፣ በአርላንዳ እንዲህ ያለው ድርጊት አጋጥሞኝ አያውቅም ብለው ነበር።

የግለሰቡ ማንነት

የግለሰቡ ስም እና ዜግነት እስካሁን ያልተገለጸ ቢሆንም፣ ግለሰቡ በዜግነት ኢትዮጵያዊ እንደሆነ ይገመታል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!