አንሚ የኢትዮ- ኤርትራን ድንበር ለቆ እንዲወጣ ተወሰነ

Ethiopia Zare (ቅዳሜ ሐምሌ 26 ቀን 2000 ዓ.ም. August 02, 2008)፦ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት፣ በኢትዮ ኤርትራ ድንበር ላለፉት ስምንት ዓመታት አሰማርቶት የነበረውን የሰላም አስከባሪ ኃይል እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ማቆሙን አስታወቀ፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራ በማንኛውም ሰዓት ጦርነት ውስጥ ይገባሉ ተብሎ ተሰግቷል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል መንግስት በሚቆጣጠራቸው የመገናኛ ብዙሀን ልዩ ቅስቀሳ እየተካሄደ ሲሆን የተለያዩ ዘመናዊ ጦር መሳሪያዎች በቲቪ ለህዝብ እየቀረቡ መሆኑን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ይጠቁማል።

 

የፀጥታው ምከር ቤት የሠላም አስከባሪ ኃይል አንሚ፤ በኤርትራ የተለያዩ ጫናዎች ሲጣልበት የቆየ ሲሆን ከሰባት ወራት በፊት ጀምሮ አካባቢውን በማንኛውም ሰዓት ለቆ ሊወጣ ይችላል በሚል ድንበሩ በስጋት ተወጥሮ ሰንብቷል፡፡

 

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ም/ቤት የሠላም አስከባሪ ኃይል (UNMEE) በድንበር ውዝግብ ውስጥ በሚገኙት በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ላይ የሚኖረው የቆይታ ጊዜ ያራዝም ወይም ያቋርጥ በሚለው ሃሣብ ላይ 15 ለ ዐ በሆነ ሙሉ ድምፅ ተልዕኮው እንዲቆም አድርጓል፡፡

 

የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሰላም አስከባሪ ኃይሉ በድንበሩ አካባቢ ተንቀሳቅሶ ኃላፊነቱን እንዳይወጣ፤ ኤርትራ የነዳጅ ኃይል አቅርቦት እንዲቆረጥ ማድረጓን ኮንነዋል፤ በዚህም መሠረት በአካባቢው የሚገኙትና በመጨረሻ የቀሩት 328 የሠላም አስከባሪ ወታደሮች አካባቢውን ለቀው ይወጣሉ፡፡

 

የፀጥታው ም/ቤት ውሣኔን ተከትሎ በሁለቱ አገራት ድንበር አካባቢ ያለው ውጥረት እየጨመረ ሊመጣ እንደሚችል በሪፖርታቸው ያስታወቁት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ ባንኪ ሙን ናቸው፡፡

 

ባንኪ ሙን በሪፖርታቸው፣ «ኤርትራ በሠላም አስከባሪ ኃይል ላይ የወሠደችው የመንቀሣቀስ ነፃነት ገደብ፣ የነዳጅ አቅርቦት መቋረጥ፣ የሰላም አስከባሪ ኃይሉ በተሠጠው መብት መሠረት ተግባሩን እንዳይወጣ አድርጓል፡፡» ብለዋል፡፡

 

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግስታት ዲፕሎማቶች፣ ከፀጥታው ም/ቤት ውሣኔ በኋላ በፍጥነት በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሠጣቸው መጠየቃቸው ታውቋል፡፡

 

«የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የኢትዮ-ኤርትራ የሠላም አስከባሪ ሃይል እ.ኤ.አ ከ2000 ዓ.ም ከአልጀሪስ ስምምነት በኋላ በሁለቱ አገራት አዋሣኝ ድንበር ውስጥ 620 ማይል የሚሆን ቦታን ፀጥታ በቅኝት ይከታተል ነበር፡፡ በዚሁ መሠረት የአንሚ የስምንት ዓመት ቆይታ በዚሁ ሊደመደም ችሏል በማለት» አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

 

በፀጥታው ም/ቤት የቤልጂየም አምባሣደር ለአሶሺየትድ ፕሬስ እንደገለጹት፣ በሁለቱ አገሮች በተለይ በኤርትራ ምክንያት አንሚ ተግባሩን መወጣት አልቻለም ብለዋል፡፡

 

ከስምንት አመታት በፊት የሁለቱን አገራት ድንበሮች ለመጠበቅ 4 ሺህ አንሚ ወታደሮችን ይዞ ከገባ በኋላ ላለፉት ሶስት አመታት ኤርትራ ልትተባበር ስላልቻለች በተለያየ ጊዜ በሚያወጣው መግለጫ ወታደሮቹን ሲቀንስ 1ሺህ 460 ወታደሮት በቀሩት ግዜ ከኤርትራ ከባድ ጫና ደርሶበታል፡፡

 

ኤርትራ አንሚ አካባቢው ለቆ ካለመጣ በሚል ከስድስት ወራት በፊት የአንሚን ወታደሮች በማገዷ በባሬንቱ፣ በሰንአፌ እና በአሰካ አካባቢ ያሉ ወታደሮች ተሰባስበው አካባቢው እንዲለቁ ተደርጓል፡፡

 

ኤርትራ የነዳጅ እገዳዋን እንደቀጠለች የቆየች ሲሆን በመጨረሻ የቀሩት 320 ወታደሮት አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ተወስኗል፡፡

 

የሰላም አስከባሪ አካባቢው ለቆ ከወጣ በአካባቢው በግልፅ የሚታዩ የጦርነት ምልክቶች አዲስ ጦርነት ሊቀሰቅሱ ይችላለ በሚል የተባበሩት መንግስታት ቃል አቀባይ ስጋታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል::

 

አንሚ በስምንት ዓመት ቆይታው ዓመታዊ ወጪው 113 ሚሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን ከወታደራዊ አባላቶች በተጨማሪ በጥቂቱ 400 ሲቪል ሠራተኞችም ነበሩት፡፡

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!