Artist Getachew Mekuria. አርቲስት ጌታቸው መኩሪያ

Ethiopia Zare (ማክሰኞ መጋቢት 26 ቀን 2008 ዓ.ም. April 4, 2016):- በ1927 ዓ.ም. የተወለደው አርቲስት ጌታቸው መኩሪያ ጥበብን የተቀላቀላት በመንገድ ላይ ታንቡር መቺ በመሆን ነው። ይህ የሆነው በ1940 ዓ.ም. ነበር ። በኋላም ጥበብን እየተከተላት እሷም ወዳለችበት እየጠራችው በ1948 ዓ.ም. በመዘጋጃ ቤት ተቀጥሮ በፊት ከሚያደንቃቸው በኋላም ለረጅም ዓመታት አብረውት ከሠሩት ከአርቲስት ተፈራ አቡነወልድና ከአርቲስት ወዳጄነህ ፍልፍሉ ጋር ተቀላቀለ።

አርቲስት ጌታቸው ጥበበ እልቡ ወስጥ ያሳደጋት በመሆኑ በሙያነት ሲረከባትም አዲስ አልሆነችበትም። እንደውም በታዋቂው የሙዚቃ መምህር በነርሲስ ላቫልዲያን የተሰጠውን የሙዚቃ ትምህርት ከተከታተለ በኋላ ይበልጥ ነገሠባት። በሳክስፎን የሙዚቃ መሣሪያ ጨዋታው ተወዳዳሪ የለሽ በመሆን የመጨረሻው ደረጃ ላይ ወጣ። አርቲስቱ ከነርሲስ ላቫልዲያን የቀሰመው የሳክስፎን ትምህርት ብቻ አልነበረም፤ አልቶ ክላሬትንም እንደሰው ያናግረው ጀመር። በዚህ ሙያውም ተደናቂና ተወዳጅ እየሆነ በመምጣቱም ከነበረበት ክፍል ውጪ በፖሊስ ሠራዊትና በብሔራዊ ትያትር ቤት በመዘዋወር ሲሠራ ቆይቷል።

በሳክስፎን መሣሪያ በቀረርቶና በሽለላ ጨዋታ ይበልጥ ውጤታማ የሆነው አርቲስት ጌታቸው መኩሪያ፤ ከሙያው ሳያሰልስ ለስድስት አስርት ዓመታት ዘልቋል። በ1986 ዓ.ም. በጡረታ ቢገለልም ካደገበት ሙያ ሳይነጠል በኢትዮጵያ ሼራተን ሆቴል ለ8 ዓመታት ተጫውቷል። ጡረታ ከመውጣቱ በፊትና በኋላ በ104 የዓለም ሀገሮች በመዘዋወር የሙዚቃ ሥራውን ለማቅረብ ችሏል።

አርቲስቱ በነዚህ ዘመናት ውስጥ ሃምሳ አምስት ዓመት በትዳር አብረው ከቆዩት ባለቤቱ አስራ አንድ ልጅ ያፈራ ሲሆን፤ በሙያው የተመሰገነ የሰው አክብሮትና ፍቅር የነበረው ደስተኛና ተግባቢ ሰው እንደነበር ብዙዎች ይመሰክራሉ። አርቲስት ጌታቸው ከሦስት ዓመት በፊት የልብና የእግር ሕመም ስለደረሰበት ለክፉ ቀን በቋጠራት ቅሪቱ በልዩ ልዩ ቦታ ከፍተኛ ገንዘብ አውጥቶ ለመታከም ቢበቃም፤ ሕመሙ እየባሰበት ሄዶ ትናንት ሰኞ መጋቢት 26 ቀን 2008 ዓ.ም. በ82 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

አርቲስት ጌታቸው መኩሪያ ምንም እንኳን በሞት ቢለየንም ሥራው ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ ይኖራል። እግዚአብሔር ነፍሱን ይማርልን! ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጅ ዘመዶቹና ለአክባሪዎቹ መጽናናትን እንመኛለን!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!