Ethiopia Zare (ኀሙስ ነኀሴ 1 ቀን 2000 ዓ.ም. August 07, 2008)፦ ወጣት ሔኖክ ገብሬ ከኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ በጋራ በመተባበር ”ምንድንነው ምስጢሩ?” በሚል ርዕስ በሀገራችን በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለውን ድርቅና ረሃብ በሚመለከት ነጠላ ዜማ በዛሬው ዕለት ለህዝብ አቅርቧል።

 

ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ በ1966 ዓ.ም. ሀገራችን ኢትዮጵያን ያጠቃትን ድርቅና ረሃብ ተንተርሶ ”ዋይ! ዋይ! ሲሉ” በማለት ከዘፈነ ከ34 ዓመታት በኋላ አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ ወጣት ሔኖክ በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ላይ በቪዲዮ የተደገፈ ዘፈን ከኢትዮጵያ ዛሬ ጋር በመተባበር ህዝባዊ ጥሪ አቅርበዋል።

 

የዚሁ ”ምንድነው ምስጢሩ?” የሚለው ዘፈን ገጣሚ የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ቋሚ አምደኛና ተባባሪ ሪፖርተር ”ወለላዬ” በሚለው የብዕር ስሙ የሚታወቀው ገጣሚ ማትያስ ከተማ ሲሆን፣ የዜማ ደራሲው ደግሞ ራሱ ወጣት ሔኖክ ገብሬ ነው።

 

የ32 ዓመቱ ወጣት ሔኖክ ገብሬ አዲስ አበባ ውስጥ ፒያሣ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ታህሳስ 29 ቀን 1968 ዓ.ም. ነው የተወለደው። ሙዚቃ የጀመረው በስደት ስድስት ዓመት በኖረባት ሱዳን ሲሆን፣ ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ ተመልሶ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው ”ሴሌክት ፐብ” ውስጥ በድምፃዊነት ለአስራ ሁለተኛ ዓመት እየተጫወተ ይገኛል።

 

ወጣት ሔኖክ በተለያዩ የሀገራችንን ቋንቋዎች የሚጫወት ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ አፋርኛ እና አደርኛ ይገኙበታል። ከውጭ ሀገር ቋንቋዎች ደግሞ ሱዳንኛ፣ ዐረብኛ፣ ፈረንሣይኛ፣ ስዋህሊኛ እና ላቲኖ ዘፈኖችን እንደሚጫወት ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልጿል። ከእነዚህም ሌላ የተለያዩ የአፍሪካ ዘፈኖችን ይጫወታል።

 

የዚህ ዘፈን ዓላማ በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን እያጠቃት ያለውን ድርቅና ረሃብ በተለይም በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ውስጥ በረሃብ የተጎዱትን ወገኖቻችንን በኢትዮጵያና በመላው ዓለም ያሉ በትውልድም ሆነ በዜግነት ኢትዮጵያዊ የሆኑ ወገኖች በመተባበር ፈጥነን በመድረስ እንታደጋቸውና ኢትዮጵያዊ ኃላፊነታችንን በያለንበት እንድንወጣ ጥሪ ማስተላለፍ ነው።

 

ወጣት ሔኖክ ገብሬ ይህንን ነጠላ ዜማ ምንም ዓይነት ጥቅም ሳያገኝበት ለህዝብ ለማቅረብ የተነሳሳበትን ምክንያት በሚመለከት ላቀረብንለት ጥያቄ ”ለበጎ ነገር የግድ ሁላችንም ካለጥቅም መሥራት ይጠበቅብናል። ዓላማው በተለይ በአሁኑ ሰዓት ሁላችንም ተባብረን ሀገራችንንና ህዝባችንን እያጠቃቸው ካለው ረሃብ የየበኩላችንን አስተዋጽዖ በማድረግ እንድናድናቸው ህዝባዊ ጥሪ ማስተላለፍ ነው። ከተባበርን ችግሩን በጋራ ለመፍታት ጥንካሬ ይኖረናልና።” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

 

እስከዛሬ አልበም አለማውጣቱን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ዛሬ ለቀረበለት ጥያቄ ወጣት ሔኖክ አንድ አልበም አዘጋጅቶ መጨረሱንና በኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት አማካኝነት በቅርቡ ሥራዎቹን ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ገልጾልናል።

 

አቶ ማትያስ በበኩሉ ስለግጥሙ ሲገለጽ ”ሀገራችን በተለያየ ጊዜ በደረቅ ብተመታም እንደአሁኑ ጊዜ ከተማ ደረስ ዘለቆ የገባ አስከፊ ረሃብ ባለመታየቱ፤ ይህንንም የውጪ ዜና ማሰራጫዎች በሰፊው እየዘገቡት እያለ የኛ ምላሽ በመደብዘዙ የእርዳታ አሰጣጡ በምን መልክ ይሁን የሚለውን ተወያይተን አመቺ ሁኔታ በመፍጠር ወገናዊ ድርሻችንን እንድንወጣ ለማሳስብ ነው የገጠምኩት” ብሏል።

 

ለዚህ ነጠላ ዘፈን መሳካት አስፈላጊ ወጭዎችን በማረግ የተባበረው አቶ ፍቃዱ (አስረስ) መኮንን ሲሆን፣ ነዋሪነቱ ስዊድን ነው።

 

ግጥሙ

 

ምንድነው ምስጢሩ?

(ችግሩን ፊት ለፊት እያየን በዓይናችን

ረሃቡን ይፋ ሰምተን በጆሯችን

ኧረ! ምነው ጨከንን በወገኖቻችን

መሃረብ እንፍታ እንግባ ኪሳችን) (አዝማች)

 

እኛ ቁርስ ምሳ ስናማርጥ እራት

እወገን ቤት ገብቷል ችጋር በእንግድነት

ምንም እንደሌለ ልባችን ደንድኖ

ጆሯችን መዓቱን ሰምቶ አልሰሜ ሆኖ

እንዴት ተቀመጥን አቃተን መደንገጥ

አገር በመከራ በረሃብ ሲጨበጥ

 

(አዝማች)

 

እንደዚህ አጥቅቶን የረሃብ አደጋ

እጃችን ምን ነካው አለ አልዘረጋ

እሩህሩህ ነበርን ለሰው አዛኝ ድሮ

ግዜው ለወጠን ወይ ምን ነካን ዘንድሮ

እንኳን ለተራበ መስጠት ልንሳሳ

እናዘን ነበረ አካሉ ለከሳ

 

(አዝማች)

 

በዕድሜ የገፉ ወላጅ እናት አባት

ምንም የማያውቁ ቡቃያ ሕፃናት

በየቀኑ ሲያልቁ እንደዚህ ሲረግፉ

ዝምታው ምንድነው በማነው ማኩረፉ

የቻልነውን ያሀል እንሰጥ እናዋጣ

አንጠብቅ እርዳታከውጪ ሲመጣ

 

(አዝማች)

 

የለውም ጨርሶ ረሃብ ቀጠሮ

ችጋር የጎዳው ሰው አይገኝም አድሮ

ነገ ዛሬ አንበል በሉ እንረባረብ

ካለንበት ሆነን እንርዳ በገንዘብ

 

(አዝማች)

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!