The protest started in Addis AbabaEthiopia Zare (ማክሰኞ መስከረም ፳፬ ቀን ፪፲፻፱ ዓ.ም. October 4, 2016)፦ በጦር ኃይሎች፣ በዓለም ገና፣ በአየር ጤና፣ በጀሞ ሁለት፣ በቡሌ ሆራ፣ በፉሪ እና ቡራዩ አካባቢዎች ከፍተኛ ህዝባዊ አምጽ የተነሳ ሲሆን፣ በርካታ መኪኖች ከመቃጠላቸውም በላይ የሰው ሕይወት መጥፋቱን የኢትዮጵያ ዛሬ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የከተማው ነዋሪዎች ገለጡ። ህዝባዊ እምቢተኝነቱ የተጀመረው ዛሬ ከሰዓት በኋላ ወደ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ሲሆን፣ በተለያዩ ቦታዎች የተኩስ ድምፅ እየተሰማ መሆኑን ለመረዳት ችለናል።

አዲስ አበባ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የገባች ሲሆን፣ ወደከተማዋ መግቢያ ከሆኑት አካባቢዎች የደቡብ ምዕራቡ (በተለምዶ ጅማ በር) መግቢያ ተዘግቶ መኪኖች ተቃጥለዋል። በእነዚህ አካባቢዎች የተጀመረው ህዝባዊ እምቢተኝነት ወደከተማዋ እየተዛመተ ሲሆን፣ ህዝቡ በተፈጠረው አመጽ ግርግር በመፍጠሩ ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች የመኪና አደጋ እንደደረሰባቸውና ወደ ሆስፒታል እንደተወሰዱ ለመረዳት ችለናል። በእነዚህ አካባቢዎች ከፍተኛ የአምቡላንስ ጩኸት ሲደመጥ እንደነበረ የዓይን ምስክሮች ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልጠዋል።

በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተቃውሞው መበርታቱን ሲረዱ ሠራተኞቻቸውን ወደየቤታቸው እንዲሄዱ አድርገዋል። ትምህርት ቤቶችም ለወላጆች እየደወሉ ልጆቻቸውን እንዲወስዱ ማድረጋቸው ታውቋል። ሱቆች፣ መዝናኛ ቦታዎች እና የግል ተቋማት የተዘጉ ሲሆን፣ ከፍተኛ የህዝብ ትራንስፖርት (ታክሲና ባስ) እጥረት በአካባቢዎቹ ተስተውሏል።

ህዝባዊ እምቢተኝነቱ ወደ መሃል አዲስ አበባ እየተዛመተ የሚገኝ ሲሆን፣ መርካቶ ውስጥ ያሉ ሱቆችም እየተዘጉ መሆኑን የደረሰን መረጃ ያመለክታል። ይህ ህዝባዊ እምቢተኝነት በአዲስ አበባ እንዲጀመር ያደረገው፤ እሁድ መስከረም ፳፪ በደብረዘይት (ቢሾፍቱ) ሆራ ላይ ይከበር በነበረው የኢሬቻ በዓል ላይ ወደ 700 የሚጠጉ ዜጎች መገደላቸውን ተከትሎ እንደሆነ ይገመታል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ