ቦርዱ የላከው ደብዳቤ ”ለአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲ” በሚል ነው

Ethiopia Zare (ሰኞ ነኀሴ 5 ቀን 2000 ዓ.ም. August 11, 2008)፦ ”አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ”ን በምርጫ ቦርድ ለማስመዝገብና ሕጋዊ ፈቃድ ለማግኘት ለቦርዱ ማመልከቻ ያስገቡት የቀድሞው የቅንጅት አመራሮች ጥቂት ማስተካከያዎችን እንዲያሟሉ በድጋሚ ከምርጫ ቦርድ በደብዳቤ ተገለጸላቸው። ደብዳቤው የተፃፈው ”ለአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲ” በሚል መሆኑን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጹ።

 

የፓርቲው መሥራቾች ረቡዕ ሐምሌ 2 ቀን 2000 ዓ.ም. የፈቃድ መጠየቂያ ማመልከቻ ካስገቡ በኋላ ኀሙስ ሐምሌ 10 ቀን የፓርቲውን መጠሪያ ስም ጨምሮ በ10 ነጥቦች ላይ ማሻሻያ አድርገው ቦርዱ ከማየቱ በፊት እንዲያቀርቡ የምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ጠይቆ እንደነበር መዘገባች አይዘነጋም። በዚሁ መሠረት ኀሙስ ሐምሌ 17 ቀን 2000 ዓ.ም. ማስተካከያዎቹን አሟልተው ማቅረባቸው አይዘነጋም።

 

ቦርዱ ዓርብ ነኀሴ 2 ቀን 2000 ዓ.ም. ተሰብስቦ ተሻሽሎ የገባውን ማመልከቻ አይቶ ምላሽ ሰጥቶበታል። ይህንኑ ምላሽ በማግስቱ ቅዳሜ ”ለአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲ” በሚል በተፃፈ ደብዳቤ ላይ ጥቂት ማስተካከያዎችን እንዲያደርጉ ጠይቋቸዋል።

 

ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ከተጠቀሱት ውስጥ ”ፓርቲው የራሱ ባንዲራ እንዲኖረው” የሚል ይገኝበታል። ጽ/ቤቱ ሐምሌ 10 ቀን እንዲያሟሉ ከጠየቃቸው 10 ነጥቦች ውስጥ የባንዲራው ጉዳይ ይገኝበት ነበር። የአንድነት ፓርቲ መሥራቾች ሐምሌ 17 ቀን ባስገቡት ማስተካከያ ላይ ስለባንዲራው ምላሽ ሲሰጡ ”አዋጁ አያስገድድም” ብለው ነበር። ቦርዱ ግን ባንዲራችሁን ግዴታ አምጡ የሚል ምላሽ ሰጥቷቸዋል።

 

ስሙን በተመለከተ ምንም አይነት ተቃውሞ ከቦርዱ ያልቀረበባቸው ሲሆን፣ ቦርዱም ደብዳቤውን ሲጽፍ ”ለአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲ” በማለቱ ስሙ ተቀባይነት እንዳገኘ ታምኗል።

 

ቦርዱ ተሟልተው እንዲያቀርቡለት ያዘዛቸውን ጥቃቅን ጉዳዮች ፓርቲው አሟልቶ እስከ ተነገ ወዲያ ረቡዕ ነኀሴ 7 ቀን 2000 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤት በኩል ማስገባት የሚጠበቅበት ሲሆን፣ ዓርብ ነኀሴ 9 ቀን ቦርዱ በድጋሚ ተሰብስቦ ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሎ ይጠበቃል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!