Kibreab Dawit, Betel Belay and their childrenኢትዮጵያ ዛሬ (ማክሰኞ ኅዳር ፲፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. Nov. 22, 2016)፦ ባለፈው ሣምንት የአዋሳ የከተማ የእግር ኳስ ቡድን ግብ ጠባቂ የነበረው የወጣት ክብረአብ ዳዊት ከሁለት ልጆቹ ጋር በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ በቃጠሎ አደጋ ሕይወቱ ማልፉ ሲዘገብ ቆይቷል።

በወቅቱ ከአደጋዎ ሕይወቷ ተርፎ የነበረችው የሟች ክብረአብ ባለቤት ወ/ሮ ቤቴል በላይ በደረሰባት ቃጠሎ ምክንያት በሆስፒታል በሕክምና ስትረዳ ቆይታ ኅዳር ፲፩ ቀን ሕይወቷ አልፏል።

ወ/ሮ ቤቴል በቃጠሎው ጊዜ ልጆቻቸውን ለማዳን ባደረገችው ሙከራ በእጆችዋና በእግሮቿ ላይ ደርሶባት በነበረው ቃጠሎ ምክንያት በሕይወት መቆየት ሳትችል መቅረቷ ታውቋል።

በክብረአብ ዳዊት እና በባለቤቱ መካከል በፍርድ ቤት የደረሰ ግጭት በመኖሩ ለተወሰነ ጊዜ ተለያይተው እንደነበር፤ በኋላም አደጋው እስከደረሰበት ዕለት ኅዳር ፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. ድረስ አብረው ይኖሩ እንደነበር የደረሰን መረጃ ያረጋግጣል።

ሆኖም ባልና ሚስት ፀብ እንደነበራቸው በመታወቁ፣ የባለቤቱ ከአደጋው መትረፍን፣ የክብረአብ ያለምንም ራስን የማትረፍ እንቅስቃሴ መሞትን፤ ብሎም በቤት ውስጥ ቤንዚን እንደነበረ መረጋገጡ፤ በባለቤቱ ወ/ሮ ቤቴል ላይ ጥርጣሬ አሳድሮ ቆይቷል።

በዚህም ምክንያት ባለቤቱ በሆስፒታል ውስጥ በፖሊስ ጥበቃ ስር ኾና ሕክምና እንድትከታተል ተደርጓል። የሕክምና እርዳታ እየተደረገላት ባለበት ወቅት ሕይወቷ ማለፉ ሁኔታውን ይበልጥ ጥልፍልፍ እንዲሆን አስችሎታል።

አንዳንድ ታዛቢዎች፤ ጥርጣሬው ኃላፊነት የጎደለው በፍፁም ይሆናል ተብሎ ሊገመት የማይችል ነው ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ ሕዝቡ ለክብረአብ ካለው ፍቅርና ተቆርቋሪነት የመነጨ ጥርጣሬ እንደሆነ ይገልጻሉ።

ጉዳዩን በመከታተል ላይ ያሉ የፖሊስ አባላት በበኩላቸው፤ ባልና ሚስት ካላቸው የቆየ ፀብ ከሕዝቡ ጥርጣሬ ቤቱ ውስጥ በተገኘው ቤንዚንና መሰል ምክንያቶች ጥርጣሬ አሳድረው እንደነበር ይናገራሉ። ሆኖም ባለቤቱ በሕይወት እስካለች ጊዜ ድረስ ተጨባጭ ማስረጃ ሊያገኙ እንዳልቻሉ ገልጸው፤ በተጨማሪ አሁንም ጉዳዩ ስላልተዘጋ ቴክኒካዊ ምርመራ በማድረግ የቃጠሎው ሁኔታ እንዴት እንደተከሰተ ከበስተጀርባም አደጋውን ያደረሱ እንዳሉ በማጣራት ላይ የምንገኝ ስለሆነ ምርመራውን ስናጠናቅቅ ለሕዝብ ይፋ እናደርጋለን ብለዋል።

ክብረአብ ዳዊት የአዋሳ እግር ኳስ ቡድን ግብ ጠባቂ ብቻ በመሆን ሳይወሰን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ወጣት ቡድን ተሰልፎ መጫወቱ ይታወቃል።

ክብረአብ ለወደፊትም ለዋናው የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡደን ግብ ጠባቂ ለመሆን ዓላማና ግብ እንደነበረው ጓደኞቹ ይናገራሉ።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!