Blue taxis at meskel sq

በአዲስ አበባ ከሚተራመሱት ተሽከርካሪዎች አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ሚኒባሶች መስለው ይታያሉ። ሚኒ ባስ ተሽከርካሪዎቹ ሰሌዳቸውን ብንመለከት አብላጫዎቹ ሦስት ቁጥር ሰሌዳ ሆነው እናገ ኛቸዋለን። በከተማው በሰማያዊና ነጭ በኮድ አንድ የሚሰሩ ታክሲዎች ብዛት ቀንሶ በተለያየ ቀለም በኮድ ሦስት የሚሰሩ ሚኒ ባስ ታክሲዎች በልጠው ለመገኘታቸው ዋናው ምክንያትም ከአዲስ አበባ ከተማ ወጥቶ ለመስራት የሚያስችል ዕድል ስለሚፈጥር መሆኑን መገንዘብ አያዳግተንም።

የጸሐይ ታክሲ ባለንብረቶች ማህበር ሰብሳቢው አቶ አበባው ካሳ እንደሚገልጹት፤ ነጭና ሰማያዊ ቀለም አስቀብቶ የአዲስ አበባ ከተማ ታክሲ አገልግሎት ፍቃድ አውጥቶ ወደ ዘርፉ የሚገቡ ባለንብረቶች በአሁኑ ወቅት የሉም። ምክንያቱ ዘርፉ በበርካታ ችግሮች የተተበተበ መሆኑ ነው። ቀለሙ በህብረተሰቡ ተፈላጊ አይደለም። ተሽከርካሪዎቹ ታክሲ በመሆናቸው ብቻ ለመግባት የሚከለከሉባቸው ስፍራዎች አሉ።

«ሰማያዊ ቀለም ከመቀባት ይልቅ ሦስት ቁጥር ሰሌዳ አውጥቶ በትራንስፖርት ሥራ መሰማራት አዋጭ ነው። ከተማውን ያጥለቀለቁትም አብዛኞቹ ኮድ ሦስት ታክሲዎች ናቸው። እነርሱ ዞናዊ ስምሪት የለባቸውም። የሚሰሩት በማይታይ ታፔላ ነው። ይህ ደግሞ ረጅም ርቀት በመጓዝ የተሻለ ሂሳብ ለመሰብሰብ ያስችላቸዋል» ይላሉ አቶ አበባው።

በትራንስፖርት ዘርፉ ጭማሪ ቢደረግ ህብረተሰቡ ይጎዳል በሚል እሳቤ ታሪፍ ለመጨመር አለመቻሉን በመግለጽ፤ በአንጻሩ ለግብአት የሚጠቀሙባቸው እንደ ተሽከርካሪ ጎማ፣ ባትሪና ሌሎች መለዋወጫ እቃዎችና ለጥገና የሚከፍሉት ዋጋ እንደ ትራንስፖርት አገልግሎት ታሪፍ ተተምኖ እንዳይጨመር መደረግ እንዳለበት ያመለክታሉ።

ዘርፉ ከፍተኛ ስጋት ለሆነው የትራፊክ አደጋ የተጋለጠ፣ ህገ ወጥ ተራ አስከባሪዎችና ሌሎች የተለያዩ ተግዳሮቶች የተጋረጡበት መሆኑን በመጠቆም፤ ድምር ምክንያቶቹ የታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት ወጪና ገቢ እንዳይ መጣጠን ከማድረጉ ባሻገር አትራፊ ባለመሆኑ ኃላፊነት ወስዶ ወደ ዘርፉ የሚገባ ሰው እንደሌለም አቶ አበባው ያስረዳሉ።

በመንግሥት በኩል ዝቅተኛ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡትን ለማበረታታት ፍላጎት እንደሌለ የሚገልጹት አቶ አበባው፤ «በርካታ ህዝብ የሚጭኑ አውቶብሶችን ከቀረጥ ነጻ ለማስገባት 70 በመቶ ከባንክ ብድር፣ ቀሪውን 30 በመቶ አዋጥተን ለመግዛት ቢፈቀድልንም በአባሎቻችን ዘንድ በአክሲዩን ተደራጅቶ የመስራት ልምዱ የለም። ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልገናል ይላሉ።

በሚኒባስ ታክሲዎቻችን እያገለገልን አውቶብስ አስገብተን ለህብረተሰቡ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት እንፈልጋለን። መንግሥት የትራንስፖርት ዘርፉን ሊደግፍ፣ ማህበራቱን ሊከታተልና ሊያበቃ ይገባዋል ሲሉ አቶ አበባው ያስገነዝባሉ። መንግሥት ዘርፉ አትራፊ እንዲሆን የማስተባበሩን ሥራ በመሥራት ብዙዎች እንዲገቡበት ማድረግ እንደሚጠበቅበትም ነው ያመለከቱት።

የብሌን ታክሲ ባለንብረቶች ማህበር ሰብሳቢ አቶ ኑረዲን ዲታሞም፤ በሰማያዊና ነጭ በኮድ አንድ የነበሩት ታክሲዎች ብዛት ቀንሷል። ምክንያቱ ተቆጣጣሪ አካል መብዛት፣ የተሽከርካሪ ዕቃ መለዋወጫዎች ከጊዜ ጊዜ መጨመር መሆኑን ይገልጻሉ። በአንጻሩ የታሪፍ ማስተካከያ አለመደረጉ በዘርፉ ተሰማርቶ ራሱንና ቤተሰቡን ከመደጎም አልፎ የተሽከርካሪውን ህልውና አስጠብቆ ለመቀጠል እየቻለ አይደለም። በመሆኑም አብዛኛው ሰው ወደ ዘርፉ ለመግባት አይበረታታም ይላሉ።

እንደ አቶ ኑረዲን ማብራሪያ፤ ከፍ ያለ ገንዘብ አውጥተው ዘርፉ ላይ የተሰማሩትም ባለንብረቶች ተሽከርካሪያቸው ሲጎዳ ከገዙበት ዋጋ ቀንሰው በመሸጥ ከዘርፉ ለመውጣት ይገደዳሉ። ገሚሶቹም ያለውን ጫና መቋቋም ሲያቅታቸው ከአዲስ አበባ ክልል ቀይረው የኦሮሚያ ክልል ሰሌዳ አውጥተው ሲሰሩ ይታያሉ። ይህ ዘርፉ ምቹ ሁኔታ እንደሌለው ማሳያ ነው ይላሉ።

በአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ባለስልጣን የተቀናጀ የትራንስፖርት አደረጃጀትና ስምሪት ቁጥጥር የሥራ ሂደት መሪው አቶ ተስፋዬ ገብሬ እንደሚሉት፤ በከተማው ኮድ አንድ ታክሲዎች ነጭና ሰማያዊ ቀለም ቀብተው የሚንቀሳቀሱ አራት እና አሥራ ሁለት ሰዎችን የሚጭኑ ተሽከርካሪዎች መሆናቸውን ይጠቁማሉ።

ከዚህ ቀደም ቁጥራቸው ከሀያ ሺህ በላይ የሆነው አሥራ ሁለት ሰዎችን የሚጭኑ ታክሲዎች ብዛታቸው ስድስት ሺ፣ አራት ሰው የሚጭኑ አነስተኛ ታክሲዎች ቁጥርም ወደ አንድ ሺ መውረዱን ይናገራሉ።

ለመቀነሳቸው ምክንያቶቹ በርካታ ቢሆንም ዘርፉ በአደረጃጀት ችግር ያለበት በመሆኑና በዘርፉ የተሰማሩት ባለሃብቶች በሚፈልጉት መልኩ ተጠቃሚ ባለመሆናቸው መሆኑን ይጠቁማሉ። አዋጪነቱ ዝቅተኛ መሆኑ በርካታ ባለሀብቶች ከዘርፉ ወጥተው ወደ ሌሎች ዘርፎች እንዲገቡ ምክንያት መሆኑን ነው አቶ ተስፋዬ የሚናገሩት።

እየተሰራበት ያለው የትራንስፖርት ታሪፍ አዋጭ ባለመሆኑ ከወቅቱ ገበያ ጋር እንዲስተካከል፣ በየጊዜው ሥርዓት ተፈጥሮለት አለመሄዱ በዘርፉ ከተሰማሩት ባለሙያዎች ቅሬታ ይነሳል።

በብዙሃን ትራንስፖርት ላይ የተሰማሩ አካላት በቀላል መንገድ የመለዋወጫ ዕቃዎች የሚያገኙበት ዕድል አለመመቻቸት ከችግሮች መካከል ዋነናው ነው። ዘርፉን ለማሳደግ ማህበራቱ ተጠናክረው የራሳቸውን የተሽከርካሪ ጥገና የሚከፍቱበት፣ የመለዋወጫ ዕቃ የሚነግዱበት ስርዓት ለመዘርጋት አቅማቸውን የማጠናከር ሥራ ሳይሰራ ዘመን አልፎ ዘመን መጣ።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!