"ፓርቲው የተጠየቀውን አሟልቶ ለምርጫ ቦርድ አስገብቷል" ወ/ት ብርቱካን

Ethiopia Zare (ሰኞ ነኀሴ 12 ቀን 2000 ዓ.ም. August 18, 2008)፦ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ፣ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲን ለማስፈን ለሚያካሂደው ትግል ለማሳካት ዓመታዊ ወጪው ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅ ዋና ፀሐፊው አቶ አስራት ጣሴ ገለጹ።

 

አቶ አስራት ጣሴ፣ የፓርቲው ም/ቤት አባል ከሆኑት ከፕሮፌሠር መስፍን ወ/ማርያም ጋር በዩናይትድ ስቴትስ የተለያዩ ግዛቶች ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት ሲያካሂዱ እንደገለጹት፣ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ፣ ላሉት 11 ቋሚ ኮሚቴዎች የሥራ መርሐግብር በተሟላ ሁኔታ ለማካሄድ ከፍተኛ የገንዘብ አቅም ያስፈልጋል ብለዋል።

 

በአትላንታ ጆርጂያ የአንድነት ፓርቲ ድጋፍ ሰጪ ኮሜቴ በተዘጋጀው ውይይት ላይ፣ ፕሮፌሠር መስፍን እንደገለጹት፣ "ኢትዮጵያውያን በሙሉ፣ ገዥው ፓርቲን ጨምሮ በአገራችን የዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን በተሟላ ሁኔታ ለማስፈን ከውስጣችን መለወጥ ይኖርብናል" ያሉ ሲሆን፤ ፕሮፌሠር መስፍን አክለው እንደተናገሩት "አንድነት ፓርቲ በኢትዮጵያ የሠለጠነ የሲቪል ማኅበረሰብን ለመፍጠር ለሚያደርገው ጥረት፣ ፓርቲውን በገንዘብ መደገፍ ያስፈልጋል" ብለዋል።

 

ፕሮፌሠር መስፍን ከንግግራቸው በፊት ባደረጉት ፀሎት "ኢትዮጵያ ከባድ ችግር ላይ ነች፣ ህዝቦቿም በታላቅና ከባድ ችግር ላይ ናቸው፣ እኛ እርስ በእርስ ልንስማማ፣ ልንተባበርና ልንግባባ አልቻልንም። በዚህም የተነሳ አገራችንና ህዝባችንን ልንረዳ በምንችልበት ሁኔታ ላይ አንገኝም። ፈጣሪ ሆይ! እባክህ ኅሊናችንን ለእውነት፣ ልባችንን ለፍቅር፣ መንፈሣችንን ለመቻቻል ክፈተው። ኢትዮጵያን ከአደጋ እንድንታደጋት አድርገን" ሲሉ ፀልየዋል። ከፀሎት ሥነ-ሥርዓቱ በኋላ ፕሮፌሠሩ ባደረጉት ንግግርም አጽንዖት የሰጡት ዴሞክራሲ፣ ፍትህ፣ እኩልነትና ነፃነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን የመገንባቱን ታላቅ ዓላማ ለማሳካት፣ መለወጥና ለለውጥ መዘጋጀት እንደሚገባ አሳስበዋል።

 

"የኢትዮጵያ ህዝብ ለመለወጥና ለለውጥ ዝግጁ ነው። ለውጥንና መለወጥን አሻፈረኝ የሚለው ኢህአዴግ ነው" በሚል ከታዳሚዎች ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ፕ/ር መስፍን ምላሽ ሲሰጡ "የገዥው ፓርቲ አባላትም እንደሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ ራሳቸውን መለወጥ አለባቸው" ሲሉ አሳስበዋል።

 

በተጨማሪም ታዳሚዎቹና መላ ኢትዮጵያውያን፣ ጥላቻንና ተስፋ መቁረጥን እንዲያስወግዱ፤ ለዴሞክራሲ፣ ፍትህ፣ እኩልነትና ነፃነት ከሚደረገው የትግል መድረክ እንዳይርቁም አስገንዝበዋል።

 

አቶ አስራት ጣሴም በኢትዮጵያ የሠላማዊ ትግል በማያጠራጥር ሁኔታ ስኬታማ እንደሚሆን፣ በተጨማሪም አንድነት ፓርቲ ብቻውን በመንቀሳቀስ ለውጥ አመጣለሁ ብሎ እንደማያምንና ከሌሎች የፖለቲካ ፖርቲዎችና ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር በትብብርና በጋራ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀዋል። "ይህንንም እውን ለማድረግ አንድነት ፓርቲ የብሔራዊ የእርቅ ጉባዔ እንዲካሄድ ግፊት ያደርጋል" ብለዋል። አያይዘውም ለዲሞክራሲና ፍትህ መስፈን የሚደረገውን ትግል ለማገዝ፣ ፓርቲውን በገንዘብ መደገፍ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀው፤ የፓርቲውን 11 ቋሚ ኮሚቴዎች እና የፖርቲውን አስቸኳይ ሥራዎች ለማከናወን፣ በዓመት 912 ሺህ ዶላር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

 

የአትላንታው ስብሰባ አዘጋጆች ለፕ/ር መስፍን እና ለአቶ አሥራት ጣሴ፣ ለኢትዮጵያና ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፈን ያለመታከት ላደረጉት አስተዋጽኦ እና ለአትላንታ ቆይታቸው መታሠቢያ የሚሆን የማስታወሻ ስጦታ አበርክተውላቸዋል።

 

በተያያዘም ሕጋዊ ሠርተፍኬት ለማግኘት፣ የመመረቻ ሰነድ አዘጋጅቶ ለምርጫ ቦርድ ያስገባው አንድነት ፓርቲ፣ ካቀረበው ሰነድ ላይ የፓርቲውን ዓርማ፣ የገንዘብ ምንጩን በግልፅ እንዲያስቀምጥና መሥራች አባላት ከስምና ፊርማ ጋር በተያያዘ፣ በሰነዱ ላይ ያሉትን ችግሮች አስተካክሎ እንዲያቀርብ በታዘዘው መሠረት ከቦርዱ የሚሰጠውን ዝርዝር መግለጫ በመጠባበቅ ላይ እንደሆነ የፓርቲው ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ አስረድተዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!