”መብቶች ይከበሩ፣ ለሕዝብ ቅሬታዎች መልስ ይሰጥ” ሂዩማን ራይትስ ዎች

Irrecha massacre in Ethiopia, 2016

ኢዛ (ዓርብ ጥር ፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. Jan. 13, 2017)፦ ሂዩማን ራይትስ ዎች ትናንት ባወጣው ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት እ.ኤ.አ. 2016 የሰብዓዊ መብቶች ቀውስ ውስጥ ወድቃለች ማለቱ ተደመጠ። ኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ መሰረታዊ መብቶችን ገድባ ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ደም አፍሳሽ አፈናዋን ቀጥላለች፣ በዘፈቀደ ታስራለች፣ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀንን ገድባለች በማለት ሪፖርቱ ያትታል።

ይኸው የትናንቱ የሂዩማን ራይትስ ዎች ሪፖርት እንዲህ ይነበባል፦

በዚህ የ2017 (እ.ኤ.አ.) የዓለም አቀፍ ሪፖርት ኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባወጀችበት በዚህ ወቅት መሰረታዊ መብቶችን በመገደብና ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የከፈተችውን ደም አፍሳሽ አፈናን ቀጥላበታለች ብሏል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በዘፈቀደ ማሰርን ይፈቅዳል፣ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀንን ይገድባል፣ እንዲሁም ከውጭ አካላት ጋር መገናኘትን ይከለክላል።

በዚህ ዓመት የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በኦሮሚያና አማራ ክልሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰልፈኞችን ገድሏል፣ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩትን እስር ቤት አጉሯል። ታስረው ከተፈቱት ብዙዎቹ በእስር ቤት ውስጥ ስቃይ እንደደረሰባቸው ታናግረዋል። ይህ እስረኞችን የማሰቃየት ችግር ኢትዮጵያ ውስጥ ለረጅም ግዜ ሳይፈታ የዘለቀ ችግር ነው። መንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ያደረሱትን በደሎች በተገቢው መልኩ ለመመርመርም ሆና ለአለማቀፍ ምርመራ ጥሪውች መልስ መስጠት አልቻለም።

"የኢትዮጵያ መንግሥት እ.ኤ.አ. በ2016 ዓ.ም. የቀረቡለትን ብዙ የማሸሻያ ጥሪዎችን በአግባቡ ማየትና ማስተካከል ሲገባው፤ ሰላማዊ ሰልፈኞችን ለማፈን ያልተመጣጠነና አላስፈላጊ ኃይል ተጠቅሟል" ብሏል ፌሊክስ ሆርኔ በሂዩማን ራይትስ ዎች ከፍተኛ የአፍሪካ ተመራማሪ። "የማይጨበጡ የተኀድሶ ተስፋዎች በቂ አይደሉም። መንግሥት ሁሉንም ትችቶች በኃይል ለማፈን ከመሞከር ይልቅ፤ መሰረታዊ መብቶችን መመለስና ትርጉም ያለው ውይይት ውስጥ መግባት አለበት" ብሏል ፌሊክስ ሆርን።

በባለ 687 ገጹ የዓለም ሪፖርት 27ተኛ እትም፤ ሂዩማን ራይትስ ዎች ከዘጠና በላይ በሆኑ አገራት ያለውን የሰብዓዊ መብት ትግበራ ገምግሟል። በዚህ የማስተዋወቂያ ጽሁፍ ዋና ዳይሬክተር ኬንዝ ሮዝ አዲስ የሕዝባዊ አገዛዝ ትውልዶች የሰብዓዊ መብቶችን ጽንሰ ሃሳብ ለመቀልበስ መሻታቸውን ጽፈዋል፤ መብትን የሚያስተናግዱበት መንገድ የብዙሃንን ፍላጎት ለመገደብ ባመቸ መልኩ መሆኑን ጽሁፋቸው ይገልጻል። ከዓለም ዓቀፉ የምጣኔ ሃብታዊ እድገት ትርፍ ተቋዳሽ እንዳልሆኑ የሚሰማቸው ሰዎች እና እየጨመረ ባለው የብጥብጥ ስጋት የሲቪክ ማኅበረሰብ ቡድኖች፣ መገናኛ ብዙኀን እና ሕዝቡ መብቶችን የሚያከብር ዴሞክራሲ እንዲገነባ አወንታዊ ሚና መጫወት አለባቸው።

የፀጥታ ኃይሎች በጥቅምት ወር የእሬቻ በዓልን ለማክበር የወጣውን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ለመቆጣጠር የተጠቀሙት ያልተገባ አያያዝ ምክንያት ሰዎች እርስ በእርስ በመረጋገጣቸው ምክንያት በርካቶች በመሞታቸው የተቃውሞ ሰልፈኞቹ ብስጭት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። በምላሹም የተናደዱት ወጣቶች፣ በተለይም በኦሮሚያ ክልል የግልና የመንግሥት ንብረቶችን አውድመዋል። ከዚህ በኋለ ነበር መንግሥት የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን በማዋጅ በሰልፉ ግዜ የጸጥታ ኃይሎች ሰልፈኞች ላይ ላደረሷቸው በደሎች ሕጋዊ ሽፋን በማላበስ ሰላማዊ ሰልፈኞቹ ላቀረቡት ጥያቄዎች የበለጠ ወታደራዊ መልስ እንደሚሰጥ ያመላክታል።

ሂዩማን ራይትስ ዎች እንዳለው ሀሳብን በነጻነት የመግለጽና መረጃ የማግኘት መብት ላይ መንግሥት የጣለው ገደብ፤ እንኳንስ ችግሩን ሊፈታ የተቃዋሚዎቹን ቅሬታዎች ለመረዳት የሚያስፈልገውን ሁሉን አቀፍ ፖለቲካዊ ውይይት አቅም ያዳክማል።

እ.ኤ.አ. በ2016 ዓ.ም. ከታሰሩት በአስር ሽዎች ከሚቆጠሩት አስረኞች መካከል፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪዎች፣ ሙዚቀኞች፣ መምህራንና የጤና ባለሙያዎች ይገኙበታል። እንደነ በቀላ ገርባ ያሉ ለዘብተኛ የሚባሉ የፖሊቲካ ፓርቲ መሪዎች በሽብር ተከሰው እስር ቤት ተወርውረዋል። የመማር ማስተማሩ ሂደት ተስተጓጉሏል፣ በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ አገር ጥለው ተሰድደዋል።

ልዩ ፖሊስ የሚባሉት የመከለከያ ሠራዊት ተወርዋሪ ኃይሎች እ.ኤ.አ. በ2016 ዓ.ም. በሶማሌ ክልል ነዋሪዎች ላይ ብዙ ግፎችን ፈጽመዋል። በኢትዮጵያ ልማት ፕሮጀቶች ምክንያት ዜጎችን ከቄዬአቸው ማፈናቀሉ ኦሞ ሸለቆን ጨምሮ በብዙ ቦታዎች ቀጥሏል።

እ.ኤ.አ. የ2016ቱ አፈና ለዓመታት በተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማኅበራትና ገለልተኛ የሚዲያ ተቋማት ላይ ሲደረግ የነበረው ስልታዊ ጥቃት ቅጥያ ሲሆን የፖለቲካ ምህዳሩን በደንብ በመዝጋት ተቀዋሚ ድምጾችን መተንፈሻ አሳጥቷል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!