እገዳው ከፕ/ት ትራምፕ ጋር የንግድ ግንኙነት ያላቸውን አገራት አላካተተም

Dubai Trump Golf Club

ኢዛ (ሰኞ ጥር ፳፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. Jan. 30, 2017)፦ ፕ/ት ዶናልድ ትራምፕ ባወጡት አስቸኳይ እገዳ ውስጥ በተካተቱት ሰባት አገራት ዜጎች እ.ኤ.አ. ከ1975 እስከ 2015 ድረስ አንድም አሜሪካዊ አለመገደሉን ሲኤንኤን ዘገበ። በተቃራኒው በእነዚሁ ዓመታት ውስጥ የሳውዲ ዐረቢያ ዜጎች 2,369፣ የተባበሩት ዐረብ ኢምሬትስ ዜጎች ደግሞ 314፣ እንዲሁም ግብጻውያን 162 አሜሪካውያንን መግደላቸውን ዘገባው አክሎ ገልጧል።

እገዳውን ባለፈው ዓርብ ጃንዋሪ 27 ቀን 2017 (እ.ኤ.አ.) ፕ/ት ትራምፕ በፊርማቸው ያጸደቁት ሲሆን፣ እገዳ የተጣለባቸው የሊቢያ፣ የሱዳን፣ የሶማሊያ፣ የሶሪያ፣ የኢራቅ፣ የኢራን እና የየመን ዜጎች ናቸው። የእነዚህ አገራት ዜጎች በስደትም ሆነ በጉብኝት ወደ አሜሪካ ለሦስት ወራት እንዳይገቡ የሚያግድ ሲሆን፣ የሶሪያ ዜጎችን ግን እስከመጨረሻው አሜሪካንን እንዳይረግጡ የሚያደርግ መሆኑ ታውቋል።

ይኸው የፕ/ት ትራምፕ እገዳ ሙስሊሞች የሚበዙባቸው አገሮች ላይ የተጣለ በመሆኑ፣ በእስልምና ላይ ያነጣጠረ ነው በሚል እየተተቸ ይገኛል።

ፕ/ት ትራምፕ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ በመሆናቸውና በተለይም ከእሳቸው የንግድ ሥራ ጋር ግንኙነት ያላቸውን በመካከለኛ ምስራቅ ያሉ የዐረብ አገራት በዚህ እገዳ ውስጥ ያላስገቡ በመሆናቸው ከፍተኛ ትችት እየደረሰባቸው ይገኛል።

ፕ/ት ትራምፕ በመካከለኛ ምስራቅ ባሉ የዐረብ አገራት ሆቴሎች ያላቸው ሲሆን፣ ባልታገዱት አገራት ውስጥ የሚገኙ ታዋቂ ድርጅቶችም ከፕ/ት ትራምፕ ድርጅቶች ጋር በንግድ ሥራ እንደሚገናኙ ዘገባዎች ይጠቁማሉ።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ