አትሌት ገንዘቤ ዲባባ በሴቶች ፪ ሺህ ሜትር ሁለት የዓለም ክብረወሰኖች ሰበረች

Genzebe Dibaba breaks world 2000M record in Sabadell

ኢዛ (ረቡዕ የካቲት ፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. Feb. 08, 2017)፦ ትናንት ምሽት ላይ ስፔይን በምትገኘው ሳባዴል ከተማ በሁለት ሺህ ሜትር የቤት ውስጥ የሩጫ ውድድር የገባችበት ሰዓት አዲስ የዓለም ክበረወሰን ማስመዝገቧ ታወቀ። ክብረወሰኑ የተሰበረው ከአስራ ዘጠኝ ዓመት በኋላ ነው። 

አትሌት ገንዘቤ ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀባት 5 ደቂቃ ከ23 ሰከንድ ከ75 ማይክሮ ሰከንድ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም በሮማንያዊትዋ አትሌት ጋብሪዬላ ዛቦ እ.ኤ.አ. 1998 ተመዝግቦ የነበረውን 5:30.53 የዓለም ክብረውሰን፤ ገንዘቤ በሰባት ሰከንድ አሻሽላ በርቀቱ የክብረወሰኑ ባለቤት ለመሆን በቅታለች።

ይኸው የአትሌት ገንዘቤ የሁለት ሺህ ሜትር የቤት ውስጥ ሩጫ የዓለም ክብረወሰን ከመሆኑም ባሻገር፤ በዚሁ ርቀት በአየርላንዳዊትዋ ሶኒያ ኦሱሊቫን ተይዞ የነበረውን ከቤት ውጪ የዓለም ክብረወሰን (5:25.36 ደቂቃ) ጭምር አሻሽላለች። በዚህም ምክንያት አትሌት ገንዘቤ በሁለት ሺህ ሜትር የሴቶች ሩጫ በሁለቱም (በቤት ውስጥ እና ከቤት ውጭ) ውድድሮች የክብረወሰኑ ባለቤት ሆናለች።

የሃያ አምስት ዓመትዋ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ፣ ሦስት ጊዜ የዓለም የቤት ውስጥ አሸናፊ ስትሆን፤ በተጨማሪም የአንድ ሺህ 500 ሜትር ሩጫ የዓለም ክብረወሰን ባለቤት ናት። አትሌት ገንዘቤ፤ ከእነዚህም ሌላ በቤት ውስጥ ውድድሮችም በአንድ ሺህ 500፣ በአንድ ማይል፣ በሁለት ሺህ ሜትር፣ በሦስት ሺህ ሜትር፣ በሁለት ማይል እና በአምስት ሺህ ሜትር የምንግዜም የዓለም ፈጣን ሰዓት ባለቤት እንደሆነች ይታወቃል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!