Sylvia's grave and Richard Pankhurst
የሲልቪያ መካነ መቃብር እና ፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት (ዲዛይን @ ኢዛ)

ኢዛ (ማክሰኞ የካቲት ፲፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. Feb. 21, 2017)፦ በኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪነታቸው ታዋቂና አንጋፋ የሆኑት የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስ ሥርዓተ ቀብር አዲስ አበባ በሚገኘው መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በብሔራዊ ክብር ዛሬ ተፈጸመ። በሥርዓቱ ላይ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ሊቃነ ጳጳሳት፣ የተለያዩ የኃይማኖት አባቶች፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው እና አድናቂዎቻቸው ተገኝተዋል።

ባለፈው ሳምንት ሐሙስ፣ የካቲት 9 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰማንያ ዘጠኝ ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት ሥርዓተ ቀብር ትናንት ሊፈጸም ታስቦ የነበረ ቢሆንም፤ በቤተሰቦቻቸው ጥያቄ ሥርዓተ ቀብሩ ለዛሬ መተላለፉን ለኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል የደረሰው ዘገባ ያመለክታል።

ቀብራቸውን አስመልክቶ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንዳይቀበሩ ተከልክሎ ነበር የሚል መረጃ ተሰራጭቶ የነበረ ሲሆን፣ መረጃውን አሰራጭተው የነበሩ ወገኖች ለዚህ ሰጥተውት የነበረው ምክንያት፤ ፕሮፌሰሩ የኦርቶዶክስ ኃይማኖት ተከታይ ባለመሆናቸው የሚል እንደነበር ታውቋል። ይኽንን ተከተሎ ሰሞኑን የተገኙ ማስረጃዎች እንደሚያመላክቱት ከሆነ፤ ፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት ኅዳር 22 ቀን 2007 ዓ.ም. በመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ አባልነት የተመዘገቡ ሲሆን፣ በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመን አባል ኾነው ተገኝተዋል። በዚሁ ማስረጃ ላይ የክርስትና ስማቸው ”ገብረ ሐና” መሆኑ ታውቋል። ጸሎተ ፍትሐቱ የተካሄደውም በሰባካ ጉባኤ አባልነት በተመዘገቡበት በመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን መሆኑን ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ ዝግጅት ክፍል የደረሰው ዘገባ ያስረዳል።

በአምስቱ ዓመት የፋሽስት ኢጣልያ ወረራ ወቅት ለኢትዮጵያ ታላቅ ውለታ የሠሩት የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት እናት ሲልቪያ ፓንክረስት ሥርዓተ ቀብር የተፈጸመው ብሔራዊ ክብር ተሰጥቶት በዚሁ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መፈጸሙ ይታወሳል። የፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት አስክሬንም በዛሬው ዕለት ያረፈው ከእናታቸው ጎን ለመሆን በቅቷል።

ሲልቪያ ወደ ኢትዮጵያ ጠቅልለው የገቡት እ.ኤ.አ. በ1956 ሲሆን፣ በኢጣልያ ወረራ ወቅት ከኢትዮጵያ ጎን ከኢትዮጵያ ጎን የቆሙ እንግሊዛዊ ነበሩ። በወቅቱ ወረራውን ተቃውመው በውጭ አገር በሚታተሙ የተለያዩ ጋዜጦች ላይ የኢትዮጵያን ጉዳይ በማስተጋባት የማይናቅ የነጻነት ተጋድሎ በማድረጋቸው፤ በብዙዎች ዘንድ “የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ” ይባላሉ።

በጣሊያኖች ተወስዶ የነበረውን የአክሱምን ሐውልት በማስመለሱ ሂደት ላይ ከፍተኛ ካደረጉት ሰዎች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት እንደሆኑ ይታወቃል።

ፕሮፌሰሩ ሕይወታቸውን በሙሉ ያሳላፉት በኢትዮጵያ ታሪክ ጥናትና ምርምር ላይ ነበር። በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህል እና ትውፊት ላይ ከተመረኮዙ ሥራዎቻቸው ውስጥ ለብቻቸው 17 መጻሕፍት ጽፈው ያሳተሙ ሲሆን፣ 22 መጻሕፍት ደግሞ በትብብር አሳትመዋል። ከ400 በላይ ጽሑፎችን ለዓለም አቀፍ መጽሔቶች ከማቅረባቸውም ባሻገር በበርካታ መጻሕፍት ላይ አርትኦት ሠርተዋል።

እናታቸው ሲልቪያ ፓንክረስት ወደ ኢትዮጵያ ጠቅለለው ከመግባታቸው በፊት፣ የሶሻሊዝም ፖለቲካን ያራምዱ የነበሩ ሲሆን፤ በኋላም በተለይም ዘመናዊው የሴቶች እንቅስቃሴና ትግል ሳይጀመር በፊት ለሴቶች መብት አደባባይ ድረስ በመውጣ ከፍተኛ ትግል ካካሄዱት ሦስት ሴቶች ውስጥ አንዷ ነበሩ። እ.ኤ.አ. 1912 የሴቶች እኩልነትና መብት እንዲከበር ተቃውሞ ሰልፍ በወጡ ጊዜ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ሲልቪያ ለሴቶች መብትና እኩልነት ሲቃወሙ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሲውሉ፣ እ.ኤ.አ. 1912፣ በትራፋልጋር አደባባይ
ሲልቪያ ለሴቶች መብትና እኩልነት ሲቃወሙ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሲውሉ፣ እ.ኤ.አ. 1912፣ በትራፋልጋር አደባባይ (ፎቶ፣ The LIFE Picture Collection/Getty Images)

የፊታችን የካቲት 25 ቀን 2009 ዓ.ም. (ማርች 4 ቀን 2017 እ.ኤ.አ.) የፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት እናት የትውልድ ከተማ በሆነው ማንቸስተር፤ የፕሮፌሰሩን ከከተማዋ መገናኘት ጋር አስመልክቶ የእግር ጉዞ እንደሚደረግ የከተማዋ ጋዜጣ (ማንቸስተር ኢቭኒንግ ኒውስ) ዘግቧል። ጉዞው ከሰዓት በኋላ 7:30 ሰዓት (13:30) ከቅድስት አኔ ቤተክርስቲያን (St Ann’s Church) እንደሚጀመር ታውቋል።

ፕ/ር ሪቻርድ ኅዳር 24, 1922 ዓ.ም. (December 3, 1927 እ.ኤ.አ) በእንግሊዝ ዋና ከተማ ሎንዶን ውስጥ በሚገኘው ዉድፎርድ ግሪን ነበር ከእንግሊዛዊቷ እናታቸው ሲልቪያ ፓንክረስት እና ከጣሊያናዊው አባታቸው ሲልቪዮ ኮሪዮ የተወለዱት።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!