ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ጃዋር መሐመድ፣ ኢሳት እና ኦኤምኤን ክስ ተመሰረተባቸው

Dr. Merera, Dr. Berhanu & Jawar
ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ጃዋር መሐመድ፣

ኢዛ (ዓርብ የካቲት ፲፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. Feb. 24, 2017)፦ ፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በዶ/ር መረራ ጉዲና፣ በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ በጃዋር መሐመድ፣ በኢሳት እና በኦኤምኤን ላይ፤ ”ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማስወገድ ሙከራ አድርገዋል” በሚል ትናንት ክስ መመስረቱ ታወቀ።

ዶ/ር መረራ ጉዲና ከሦስት ወር በፊት (ኅዳር ፳፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም.) ከአውሮፓ ሲመለሱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ መታሰራቸው አይዘነጋም። በወቅቱ ጥቅምት ፴ ቀን በአውሮፓ ሕብረት ጋባዥነት ብራስልስ (ቤልጅየም) ላይ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ንግግር ለማድረግ ተጋብዘው ከግንቦት ሰባት አመራር እና ሊቀመንበር ከሆኑት ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር ታይተዋል በሚል ለእስር መዳረጋቸውን መዘገባችን የታወሳል።

ዓቃቤ ሕግ የከፈተው ክስ በዶ/ር መረራ ስም ሲሆን፣ እሳቸው የመጀመሪያው ተከሳሽ ሲሆኑ፣ ሁለተኛ ተከሳሽ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ሦስተኛው ተከሳሽ አቶ ጃዋር መሐመድ ናቸው። ሦስቱ ተከሳሾች በ፲፱፻፺፮ ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ የተለያዩ ድንጋጌዎችን በመጣስ፣ በዋና አድራጊነት የሽብር እና የኹከት ተግባር መፈጸማቸውን፣ በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ለተነሱት አመጾች ተጠያቂ መሆናቸውን፣ በሚሊዮኖች ብር የሚቆጠር የመንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቁማት ንብረት መጥፋት የተከሳሾቹ አመጽ ማነሳሳት መሆኑን ክሱ ያመለክታል።

ከዚህም በተጨማሪ የዓቃቤ ሕግ ዶ/ር መረራን ”ከአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁ እርምጃዎች ጋራ የተያያዙ ግዴታዎችን በመተላለፍ ወንጀል” የሚል ተጨማሪ ክስ እንደመሰረተባቸው ለኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል የደረሰው ዘገባ ያስረዳል።

ይኸው የዓቃቤ ሕግ በዶ/ር መረራ ላይ በመሰረተው ክስ ላይ በተለያዩ አካባቢዎች ንብረቶች እንዲወድሙ አድርገዋል በማለት ከሷቸዋል። በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ አምቦ አካባቢ ለወደመ የብር 2,957,661.00 ንብረት፣ በቡራዩ የብር 42,598,204.98 ንብረት፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ የብር 17,352,482.00፣ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ለወደሙ የብር 215,468,309.99 የመንግሥት ንብረቶች እንዲሁም መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ንብረት ላይ ከብር 1,168,293,498.68 በላይ ግምቱ የሆነ ንብረት እንዲወድም አድርገዋል ይላል ክሱ። በዚህ ስሌት መሰረት ዓቃቤ ሕግ ዶ/ር መረራን እንዲውድም አስደርገዋል ብሎ የከሰሳቸው፤ ከብር 1,446,670,156.65 (አንድ ቢሊዮን አራት መቶ አርባ ስድስት ሚሊዮን፣ ስድስት መቶ ሰባ ሺህ፣ አንድ መቶ ሃምሳ ስድስት ከስድሳ አምስት ሳንቲም) በላይ ለሚገመት ንብረት መሆኑ ታውቋል።

በዚህ የክስ መዝገብ ላይ አራተኛው ተከሳሽ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን (ኢሳት) ሲሆን፣ አምስተኛው ተከሳሽ ደግሞ የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦ.ኤም.ኤን.) ናቸው። ሁለቱ የሚዲያ ተቋማት የተከሰሱት በሽብር ወንጀል መሆኑን ለመረዳት ችለናል።

ፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በሦስቱ ድርጅቶች እና በሁለቱ ተቋማት ላይ የመሰረተው ክስ ባለሃያ አራት ገጽ ሲሆን፣ ሙሉውን ክስ በፒዲኤፍ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!