የአዲስ አበባ መስተዳድር ለማይጠቀምበት የሰንዳፋ ቆሻሻ መጣያ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ አውጥቷል

የአስከሬን ፍለጋው ባለመጠናቀቁ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል

Suspected to be missing
በቆሻሻ ክምሩ መደርመስ ሳቢያ ጠፍተዋል የተባሉና በመፈለግ ላይ የነበሩ ሕጻናት (ፎቶ፣ REUTERS/Tiksa Negeri)

ኢዛ (ሐሙስ መጋቢት ፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. Mar. 16, 2017)፦ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ መጋቢት 2 ቀን ከምሽቱ 1፡30 ላይ በተለምዶ ”ቆሼ” ወይም ”ቄስ” ሠፈር እየተባለ በሚጠራው እና በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ውስጥ በሚገኘው የቆሻሻ ክምር በመደርመሱ ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈው ሰዎች ቁጥር እስከ ትናንት ማምሻ ድረስ 113 መድረሱ ታወቀ። በዛሬው ዕለትም የአስከሬን ፍለጋው ሥራ የቀጠለ ሲሆን፣ የሟቾች መጠን ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል።

እስከትናንት ማምሻውን አስከሬናቸው ከተገኘው 113 ሟቾች መካከል 75ቱ ሴቶች ሲሆኑ፣ 38ቱ ወንዶች መሆናቸው ታውቋል። አስከሬናቸው የተገኙት ወገኖቹ አብዛኞቹ የቀብር ሥነሥርዓታቸው እስከ ትናንት ድረስ የተፈፀመ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለትም ቀብራቸው የሚፈፀም እንደሚኖር ታውቋል።

በብዛት በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡት እናቶች፣ ሕፃናት እና ወጣቶች ሲሆኑ፣ ለዚህም ምክንያቱ አደጋው የደረሰው በምሽት በመሆኑ አብዛኞቹ ደግሞ ከቀን ሥራቸው የሚያርፉበትና ወደ ቤታቸው የሚሰበሰቡበት ሰዓት ስለነበር ነው። ከአደጋው የተረፉት ወገኖች ለሌላ አደጋ ሳይጋለጡ በፊት መንግሥት ኃላፊነቱን መወጣት እንደሚገባው ጉዳዩ ያሳሰባቸው ወገኖች ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

ይህ ለደረቅ ቆሻሻ መጣያ ተብሎ ከ50 ዓመት በፊት የተሠራው ይኸው ሥፍራ 37 ሔክታር ስፋት እና 40 ሜትር ከመሬት በታች ጥልቀት ያለው ሲሆን፣ የቆሻሻው ክምር ሞልቶት ከምድር ወለል በላይ ከ13 ሜትር በላይ ደርሶ እንደነበር ታውቋል። በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች የቆሻሻ ክምሩ መናዱ አይቀሬ መሆኑን በመረዳት ለረዥም ዓመታት ለሚመለከታቸው አካላት አቤቱታ ሲያሰሙ የነበሩ ቢሆንም፣ ሰሚ ማጣታቸውን ተናግረዋል።

አደጋው በደረሰ ማግስት እሁድ መጋቢት ፫ ቀን የተነሳ ፎቶግራፍ። (ፎቶ፣ ZACHARIAS ABUBEKER/AFP/Getty Images)

በአካባቢው ከነበሩትና የአደጋው ሰለባ ከሆኑት ውስጥ ሕጋዊ የመሬትና የቤት ሰነድ ያላቸው ከ20 ያላነሱ ቤቶች የሚገኙበት ሲሆን፤ ለጊዜው ቁጥራቸው በኦፊሴል ያልታወቁ በርካታ የጨረቃ ቤቶችም እንደነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጠዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ አደጋው ሊደረስ እንደሚችል የወረዳው ኃላፊዎችም ሆኑ የመንግሥት ባለሥልጣናት ቀደም ብለው ያውቁ ነበር፤ ነገር ግን ቅድመ ጥንቃቄ አለማድረጋቸው ኃላፊነት የጎደለውና ቸልተኝነት የበዛበት ነው በማለት ለኢትዮጵያ ዛሬ ሪፖርተር ገልጠዋል።

እነዚሁ ነዋሪዎች ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ እንዳስረዱት ከሆነ፤ አደጋው ከመድረሱ አንድ ቀን በፊት አንዲት ላም እቆሻሻው ክምር ላይ ወጥታ ሳር ስትግጥ ክምሩ ተንዶ ወደታች ይዟት እንደውረደ፣ በዚያኑ ዕለትም የወረዳው ኃላፊዎች በአካባቢው ተገኝተው የጨረቃ ቤቶችን ሲለኩና ሲመዘግቡ ነበር። ነዋሪዎቹ ይህንን እና ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ለሚመለከተው አካል አቅርበውት የነበረውን ”አንድ ቀን ሊናድ ይችላል” የሚለውን አቤቱታቸውን መሰረት በማድረግ ነው የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላትን ኃላፊነት የጎደላቸውና ቸልተኞች በማለት የሚከሱት። ከዚህም ሌላ ባለፈው ዓመት ከሐምሌ ወር በፊት ለሰባት ወራት ወደ ሰንዳፋ ተዛውሮ የነበረው የደረቅ ቆሻሻ መጣያ ከተከለከለ ወዲህ፣ ተመልሶ ወደ ቆሼ ሰፈር ቆሻሻ መጣል መጀመሩ፣ በቆሻሻው ክምር ምክንያት አንድ ቀን አደጋ ሊደርስ እንደሚችል የሁሉም ስጋት እንደነበር የአደባባይ ምስጢር ነበር በማለት የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጠዋል።

ለደረቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ በሚል የአዲስ አበባ መስተዳድር በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚገኘው ሰንዳፍ ውስጥ ከአንድ ቢልዮን ብር በላይ ውጪ በማድረግ ያስገነባው፤ ”ሰንዳፋ ሳኒተሪ ላንድ ፊል” ባለፈው ዓመት 2008 ዓ.ም. ከታህሳሳ እስከ ሐምሌ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ ለሰባት ወራት አገልግሎት ከሰጠ በኋላ፤ በሰንዳፋ የሚገኙት የአካባቢው አርሶ አደሮች ባሰሙት ተቃውሞ ምክንያት የሰንዳፋ ሳኒተሪ ላንድ ፊል ሥራውን ማቆሙ ይታወቃል።

በወቅቱም ሆነ ከዚያ በኋላ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የኦሮሚያ ክልል ውይይት ቢያካሂዱም ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ቀርተዋል። የአዲስ አበባ መስተዳድር ይህንን ችግር በሰዓቱ መቅረፍ ያልቻለ ከመሆኑም በላይ አማራጭ የቆሻሻ መጣያ ሳያዘጋጅ ዘጠኝ ወራት አልፈዋል።

በአዲስ አበባና በኦሮሚያ መስተዳድሮች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ንትርክ ሲከታተሉ የነበሩ ወገኖች፣ የአደጋው ተጠቂና ሰለባ የሆኑና ቤተሰቦቻቸው፣ እንዲሁም ይህንን ንትርክ በቅርቡ የሰሙ ወገኖች በአብዛኛው በጉዳዩ ላይ ተመሳሳይ ጥያቄዎችን እየሰነዘሩ እንደሆነ የኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ ዝግጅት ክፍል ለመረዳት ችሏል። ከጥያቄዎቹ ውስጥ፣ ”የአዲስ አበባ መስተዳድር ለማይጠቀምበት የደረቅ ቆሻሻ መጣያ ቦታ ከአንድ ቢልዮን ብር በላይ ለምን አወጣ?”፣ ”በክልሎቹ መሃል የነበረውን አለመግባባት እንዴት የፌደራሉ መንግሥት ዝም ብሎ ተመለከተው?” የሚሉት ዋንኞቹ ናቸው።

በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖች ሥነሥርዓተ ቀብር በገብረክርስቶስ ቤተክርስቲያን፣ አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4 ቀን 2009 ዓ.ም. (ፎቶ፣ AP)

ከአደጋው ለተረፉ የአካባቢው ነዋሪዎች የኢትዮጵያ ቀይ መስቀልን ጨምሮ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጊዜያዊ ዕርዳታ እያደረጉላቸው መሆኑ ታውቋል። የከተማው መስተዳድር ደግሞ ሕይወታቸው ላለፉ ሰዎች የቀብር ማስፈፀሚያ ብሎ በሰው 10 ሺህ ብር መስጠቱን ከንቲባ ድሪባ ኩማ ገልጠዋል።

አደጋው በደረሰ አራተኛው ቀን ባለፈው ማክሰኞ፣ የተወካዮች ምክር ቤት ከትናንት ረቡዕ መጋቢት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ የኀዘን ቀን ማወጁ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ ዝግጅት ክፍል ሕይወታቸውን በአደጋው ላጡ ወገኖች ቤተሰቦች፣ ዘመዶች፣ ወገኖች እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን ይመኛል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!