መርካቶ
መርካቶ ገበያ፣ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

ኢዛ (ሰኞ ሐምሌ ፲፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. July 24, 2017)፦ መንግሥት ቀደም ሲል ያውጣውን በቀን ገቢ ግምት ላይ የተመሰረተ የግብር ክፍያን በመቃወም በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ተቃውሞ መነሳቱ ይታውቃል። ይኼው ተመን በነጋዴዎችና በሕዝቡ ጉሮሮ ላይ የተሰነቀረ አጥንት በመሆኑ በመላው አገሪቱ ነጋዴዎች ተቃውሞ አስነስቷል። በዚሁም መሰረት በአዲስ አበባ በሚገኘው በመርካቶ ገበያ ማዕከል ተቃውሞ በመነሳቱ፤ በርከት ያሉ የንግድ ቤቶች ዝግ ኾነው ውለዋል። የጣና ገበያ አዳራሽም በመዘጋቱ ምክንያት መርካቶ ጭርና ቅዝቅዝ ብላ አርፍዳለች።

መንግሥትን የሚወክሉ ካድሬዎችና ፖሊሶች በአካባቢው በመዘዋወር ንግድ ቤቶቹን አስገድደው ለማስከፈት ሙከራ ቢያደርጉም፤ እስካሁን የተሳካ ውጤት እንዳልተገኘ ታውቋል። አንዳንድ ተችዎች፤ ይኼ ሁኔታ መንግሥት ሕዝብ ላይ ባለው ጥላቻ በፈጠረው ድርጊት፤ እራሱንም ሊያናውጠው እንደሚችል ይናገራሉ። ምክንያቱንም ሲያስረዱ፤ “ነጋዴው በመንግሥት የተጣለበትን የዕለት ገቢ ግብር ለመቋቋም፤ በበኩሉ በሕዝብ ላይ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉ የማይቀር በመሆኑ፤ ሕዝብ የነጋዴውን ተቃውሞ በመቀላቀል ሊነሳ ስለሚችል፤ በመንግሥት ላይ ያልታሰበ ውጥረትና ሊቋቋመው የሚያዳግት አደጋ ሊገጥመው ይችላል” ይላሉ። ተቃውሞው ዘርና ኃይማኖትን ያማከለ ሳይሆን፤ በአንድነት ሕዝብን የሚያስነሳ በመሆኑ የታመቀ በደል የሚገለጽበት እንደሚሆንም ይገመታል።

አዲስ አበባ፣ መንግሥት እንደሚለው ሳይሆን፤ የኢትዮጵያ መገለጫ የሆነች የብዙ ብሔር ብሔረሰብ መኖርያና መናኸሪያ እንደሆነችም፤ የከተማዋ ነዋሪ ተቃውሞውን በግልጽ የምያሳይበት ኹኔታ ሊፈጠርም ስለሚችል፤ ከወራት በፊትም መንግሥት ያወጣው የኦሮሚያን ልዩ ጥቅም የሚያስጠብቅ ረቂቅ አዋጅን ዋጋ እንደሚያሳጣው ይታሰባል።

በዚኽ ሰሞን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ ለሚወስኑት ነገሮች ወቅታዊ መረጃ እንደሌላቸውንና አለ ዕቅድና ፕላን ሰዎች ከሚናገሩት ተነስተው እንደሚሰሩ፤ ይህም አሰራር በጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት ብቻ የሚሰራበት ሳይሆን፤ እታችም ባሉት መስሪያ ቤቶችም ጭምር እንደሚፈጸም የገለጹበት ንግግር ከዚህ አሁን በነጋዴው ላይ የደረሰው ከአቅም በላይ የተጫነ ግብር የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር እውነተኛነት የሚመሰክር ሆኖ ተገኝቷል።

ተቃውሞው እስካሁን ካንዱ ከተማ ወደ አንዱ ከተማ እየተዛመተ ሄዶ፤ አዲስ አበባ ቢደርስም ተቃውሞውን ለማብረድ መንግሥት የኃይል እርምጃ ከመውሰድ በቀር የወሰደው መፍትሄ ስለሌለ፤ ኹኔታው ሊባባስ እንደሚችልና ከፍተኛ የሕዝብ አመጽም ሊቀሰቅስ እንደሚችል ብዙዎች ይናገራሉ።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!