እነወ/ት ብርቱካንን የተቀበሉ በሳውላ ታሰሩ

Ethiopia Zare (ማክሰኞ ጥር 13 ቀን 2000 ዓ.ም. January,22,2008):- በደቡብ ኢትዮጵያ ሳውላ ከተማ በወ/ት ብርቱካን የተመራውን ልዑካን የተቀበሉ የቅንጅት ደጋፊዎች ለእስርና ለእንግልት መዳረጋቸውን ከስፍራው የደረሰ ዘገባ ጠቆመ።

 

እስከአሁን በደረሰን ዘገባ መሰረት ንጉሴ ደሳለኝ እና ታደለ ደጌ የተባሉ ሁለት አስተባባሪዎች "ሕጋዊ ያልሆኑ ሰዎችን አነጋግራችኋል" እንዲሁም "ሕህገወጥ ስብሰባ አድርጋችኋል" በሚል ክስ እስር ቤት እንደሚገኙ ለማወቅ ችለናል። በተጨማሪም ከ300 በላይ የሚሆኑ በስብሰባው ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ የቅንጅት ደጋፊዎች በተመሳሳይ ክስ በኢህአዴግ ካድሬዎች እየተንገላቱ መሆኑን ታማኝ ምንጮቻችን አስረድተዋል።

 

ጉዳዩን በሚመለከት የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ የሆኑት አቶ ሙሉነህ ኢዩኤል ስለእስረኞቹ ሁናቴና እንዲህ አይነት ሁኔታዎች እንዳይደገሙ ቅንጅቱ ምን አይነት እርምጃ መውሰድ ይገባዋል? ተብሎ ከኢትዮጵያ ዛሬ ድረ-ገጽ ለቀረበላቸው ጥያቄ የእስረኞቹን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተሉት መሆኑን ከገለጹ በኋላ፤ "ሰበብ አስባብ እየተፈለገ የፖለቲካ ሕይወታቸውን እንዳይለማመዱ (ኤክስፒሪአንስ) እንዳያደርጉ የሚደረግበት ሁኔታ ነው ያለው። እንደዛ ብሎ ሰዎችን ማሰር ራሱ ሕገ-ወጥ ነው። እንደዚህ አይነቱን ነገር እንደምክንያት የሚያነሱት በተለይ አሁን ካለፈው ሣምንት መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ 'ቅንጅት የሚለው ነገር ሕጋዊነት ያለው በአቶ አየለ ጫሚሶ የሚመራው ነው' በሚል ብዙ የቅንጅት አባላትንና ደጋፊዎችን የመወከል መብት ለማደናቀፍ የተሞከረ ሙከራ ነው። ይህም አግባብነት የሌለው ነው። የምንቀበለውም አይደለም። ..." ብለዋል።

 

አቶ ሙሉነህ አያይዘውም "... ያም ሆኖ በእንደዚህ ያለ ነገር ውስጥ አተካራ መግባት ያለብን አይመስለኝም። የምናገረው የራሴን አቋም ነው፤ ምክንያቱም ሥራ አስፈጻሚው ተሰብስቦ ውሳኔ ያላሳለፈበት ጉዳይ በመሆኑ። እንደኔ እንደኔ የምለው ምናልባት የስም ለውጥ አድርጎ እንደዚህ አይነት ነገሮችንና እንደዚህ አይነት እክሎችን ማለፍ የሚቻል ነው የሚመስለኝ። እና ወደፊት የስም ለውጥ መደረግ አለበት ብየ በግሌ አምናለሁ። በእንደዚህ አይነት ነገሮች ከመንግሥት ጋራ አተካራ ውስጥ ገብቶ አባላትንም ሆነ ደጋፊዎችን የማያስፈልግ ዋጋ እንዲከፍሉ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብዬ ስለማላምን፤ እኔ በግሌ ምናልባት የስም ለውጥ መደረግ አለበት ብዬ አምናለሁ" ሲሉ የግል አስተያታቸውን ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረ-ገጽ ሰጥተዋል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!