ገዱ አንዳርጋቸው

የተከበሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአማራው ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት

ምሁራን/አክቲቪስቶች ኦሮሞኛ በአማራ ክልል በግዕዝ ፊደል እንደ ትምህርት እንዲሰጥ ጠየቁ

“በባዕዳን ፊደል የሚጽፉ አፍሪካውያን፣ በአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች ሲገዙ የነበሩና ራሳቸው የፈለሰፏቸው የፊደላት አማራጭ ያልነበራቸው ሕዝቦች ናቸው። እኛ በጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ደምና አጥንት ነፃነታችን ተከብሮልን የኖርንና አኩሪ ቅርስ የሆነ የራሳችን ፊደል ያለን ሕዝቦች፤ ቅኝ እንደተገዙትና እንደተዋረዱት ያልታደሉ ሰዎች ልንሆን አይገባም።” ሲሉ ታዋቂ ምሁራን እና አክቲቪስቶች፣ አሮምኛ በአማራ ክልል በግዕዝ ፊደል እንዲሰጥ የሚጠይቅ ጥናታዊ ሰነድ አዘጋጅተው ለአቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት አስገቡ። ደብዳቤውን ከአባሪ ሰነዶች ጋር በዚሀ ጽሑፍ አቅርበነዋል።

በባዕዳን ፊደል የሚጽፉ አፍሪካውያን፣ በአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች ሲገዙ የነበሩና ራሳቸው የፈለሰፏቸው የፊደላት አማራጭ ያልነበራቸው ሕዝቦች ናቸው። እኛ በጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ደምና አጥንት ነፃነታችን ተከብሮልን የኖርንና አኩሪ ቅርስ የሆነ የራሳችን ፊደል ያለን ሕዝቦች ቅኝ እንደተገዙትና እንደተዋረዱት ያልታደሉ ሰዎች ልንሆን አይገባም። ምሁራን/አክቲቪስቶች

ጉዳዩ፦ ኦሮምኛን በአማራው ክልል በግዕዝ ስለማስተማር

ጥር 30 ቀን 2010 ዓ.ም.

ለተከበሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአማራው ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት

ክቡር ፕሬዝደንት ሆይ፦

የአማራ ክልል ከኦሮሚያ ቀጥሎ ብዙ ሕዝብ የሚኖርበትና ስፋት ያለው ክልል ነው። ከአማራ ክልል ውጭ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ አማርኛ ተናጋሪዎች እንደሚኖሩት፣ የአማራ ክልልም የሌሎች ብሔረሰቦች አባላት በስፋት ይኖሩበታል። ከዚያም የተነሳ በአማራ ክልል ሆነ በተቀረው የአገራችን ግዛቶች የተለያዩ ቋንቋዎች ይነገራሉ።

አንዳንዶች ቋንቋን የማንነት ምልክት አድርገው የማየት ዝንባሌ አላቸው። ሆኖም ግን ቋንቋ በዋናነት የመግባቢያ መሳሪያ ነው። አንድ ሌላ ቋንቋ የምናውቅ ከሆነ፣ አስተማሪ ወይም ሐኪም ሆነን ወይም በተለያዩ ሌሎች ምክንያቶች፣ ቋንቋው የሚነገርበነት አካባቢ ከሕዝቡ ጋር በቀላሉ የመግባባት እድል ይኖረናል። ቋንቋ ማወቅ ጠቃሚ ብቻ ሳይሆን ሊበረታታ የሚገባው ነው።

አንደኛ፦ ከአማርኛና እንግሊዘኛ ቀጥሎ ሌላ ሦስተኛ ቋንቋ ስለማስተማር

በአዲስ አበባና በአማራ ክልል (ከሚሴ ከተማ የሚገኝበት በአማራ ክልል የኦሮሚያ ልዩ ዞንን ሳይጨመር) በትምህርት ቤቶች የአማርኛና የእንግሊዘኛ ትምህርቶች ይሰጣሉ። በሌሎች ክልሎች ግን ዜጎች ሌላ ሦስተኛ ቋንቋ ይማራሉ። ለምሳሌ በትግራይ ክልል እንግሊዘኛ፣ አማርኛና ትግሪኛ፣ በደቡብ ክልል ሐዲያ ዞን እንግሊዘኛ፣ አማርኛና ሐድይኛ፣ በሶማሌ ክልል እንግሊዘኛ፣ አማርኛና ሶማልኛ ... ይማራሉ። ብዙ ቋንቋ አለማወቃቸው የአዲስ አበባና የአማራው ክልል ተማሪዎችን ግን ብዙ ጥቅሞች እንዲጎድልባቸው ሊያደረግ ይችላል ብለን እናስባለን።

ከአሥራ ዘጠኝ ዓመታት በፊት፣ ሁሉም ክልሎች (ከአማራ ክልልና ከአዲስ አበባ በስተቀር) ከአማርኛ በተጨማሪ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸውን ስለሚማሩ፣ በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ ግን የአፍ መፍቻና የፌደራሉ የስራ ቋንቋ አንድ በመሆኑ፣ የክልሉ ተማሪዎች አንድ የሀገር ውስጥ ቋንቋ ብቻ በመማር በወደፊት የስራ ህይወታቸው ላይ የሚደርሰውን ተግዳሮት ለመቀነስ፣ የክልሉ የትምህርት ቢሮ አንድ ጥናት አስጠንቶ ነበር። በዚህ ጥናት ዙሪያ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶ/ር በድሉ ዋቅጃራ፣ በፌስ ቡክ ገጻቸው፤

“በ1990 - የክልሉ ትምህርት ቢሮ ለጨረታ ያቀረበውን፣ የተጠቀሰውን ጥናት ያጠናነው እኔና ሁለት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስነትምህር ባለሙያዎች ነበርን። በክልሉ በሳይንሳዊ መንገድ ናሙና በመውሰድ (ወላጆችን፣ የትምህርት አስተዳደር ሠራተኞችን፣ መምህራንንና ተማሪዎችን) በተደረገው በዚህ ጥናት የተገኘው ውጤት የኦሮምኛ ቋንቋ በክልሉ ትምህርት ቤቶች በሁለተኛ ቋንቋነት እንዲሰጥ በአንደኛነት መመረጡን ነው። ከዚህም ሌላ አጥኚዎቹ አዋሳኝ ቋንቋዎችን ከግምት ያስገባና ጥናቱን መሰረት ያደረገ ሐሳብ (recommendation) አቅርበን ነበር”

ሲሉ ጽፈዋል። ዶ/ር በድሉ፣ ከሰማኒያ ሺህ ብር በላይና ወደ አንድ ዓመት ገደማ የፈጀው ጥናት ውጤት፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ባዘጋጀው መድረክ ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበትን ገልጸዋል።

በመሆኑን ክብርነትዎ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የአማራ ክልል የትምህርት ፖሊሲ የሚሻሻልበትና ከአማርኛና ከእንግሊዘኛ ቀጥሎ በዜጎች ወይንም በወረዳው አስተዳደር ምርጫ ሦስተኛ የአገራችንን ቋንቋ የሚማሩበት ሁኔታ ቢመቻች ጥሩ ሊሆን ይችላል እንላለን። ያ ከሆነ አብዛኞቹ ወረዳዎች ምርጫቸው ኦሮምኛ ሊሆን ይችላል ብለን እናስባለን።

ይህ አሠራር በሠለጠኑት አገራት በተለይም በአውሮፓ የተመለደ አሠራር ነው። ለምሳሌ በፈረንሳይ የትምህርት ፖሊሲ እያንዳንዱ ዜጋ ከፈረንሳይኛና ከእንግሊዘኛ በተጨማሪ ሌላ ሦስተኛ ቋንቋ በምርጫ እንዲማር ይደረጋል። አንዳንዶቹ ጀርመንኛ አንዳንዶቹ ራሺያኛ፣ አንዳንዶቹ ጣሊያንኛ ... ይመርጣሉ።

ሁለተኛ፦ የግዕዝ ፊደላትን መጠቀም የአገር ቅርስ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን የተሻለም ነው

ምዕራባውያን ለጥቁር ሕዝብ መሸጥና መዋረድ እንደ ምክንያት የሚጠቀሙበት አንዱና ትልቁ መከራከሪያቸው “ጥቁሮች የራሳቸውን ስነፅሁፍና ፊደል መቅረፅ ያልቻሉት ዝቅተኞች ስለሆኑ ነው” የሚለው ነው። ይሄን ትርክት ውድቅ ለማድረግ፣ ግዕዝን ምናልባት የተሻለ ስምም ሰጥተን ኢትዮጲስ ወይም ሌላ ብለነው ወደቀረው አፍሪካ እንዲስፋፋ መታገል ነበረብን። ሆኖም በተለያዩ አገራዊ አጀንዳዎች በመወጠራችንና በሃገራችን የሰፈነው የማንነት ፖለቲካና ከኢትዮጵያ የተለየ ማንነት ይፈልጉ የነበሩ አክራሪ ብሔርተኞች አሉታዊ ጫና ምክንያት አላደረግነውም። እንኳን ወደ አፍሪካ አገሮች ግዕዝን ልንወስድ ቀርቶ በአገራችን የነጮችን ፊደል፣ ላቲን፣ ለአንዳንድ ኢትዮጵያ ቋንቋዎች እየተጠቀምን ነው። አንዳንድ ወገኖች የግዕዝ ፊደልን የአንድ ብሔረሰብ እርስት አድርገው የመቁጠር ዝንባሌ ሲኖራቸው አንዳንዶች ደግሞ የግዕዝ ፊደል ብቃት እንደሌለው አድርገው ያስባሉ። የላቲን ፊደላት ተናጋሪው እንደሚናገረው አይጻፉም። ስፔሊንጉን ለማወቅ ችግር ነው። በኢትዮጵያ ፊደላት ግን ሰው እንደሚናገረው ስለሚጻፉ፣ የስፔሊንግ ስህተት ሊሠራባቸው አይችልም። ስለዚህም ከላቲን ፊደል ይልቅ ግዕዝ የበለጠ ይመረጣል።

ኤርትራውያን መቼ የግዕዝን ፊደላት አንፈልግም አሉ? ከኢትዮጵያ ተገነጠሉ እንጂ መቼ ከፊደላችን ተገነጠሉ? እንደውም እነሱ ቀደም ሲል በጣልያን ቅኝ ግዛት ተገዝተው ስለነበር፣ በላቲን እንቸክችከው ቢሉ፣ ጥሩ ሰበብ በሆናቸው ነበር። ከላቲን ይልቅ ኢትዮጵያውያኑ ፊደላት ብዙ ጥቅሞች እንዳላቸው በመገንዘባቸው ግን ፊደሎቻችን ላይ ሙጭጭ ብለው ይዘዋቸው ሄዱ።

ግዕዝ የአማራው ማኅበረሰብ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያውያን ቅርስ ነው። ከዐረብኛ ውጭ ብቸኛው የጥቁር ሕዝብ ፊደል ነው። አማርኛ፣ ትግሪኛ፣ ጉራጌኛ፣ ሐድይኛ፣ ከንባትኛ፣ ንውርኛ፣ አኙዋክኛ፣ አገውኛ፣ አደሪኛ፣ ስልጥኛ ... በአሁኑ ጊዜ የግዕዝ ፊደላትን ነው የሚጠቀሙት። አደሪኛ ለአስር ዓመታት ላቲን ይጠቀሙ የነበረ ቢሆንም ግዕዝ ይሻላል ተብሎ ወደ ግዕዝ ዞሯል።

ኢትዮጵያ በአባቶቻችን መስዋትነት ነጻነቷን ጠብቃ የኖረች አገር ናት። የራሱ ባህል፣ የራሷ ቋንቋዎች፣ የራሷ ፊደል፣ የራሷ ቅርሶች ያላት። በአገራችን የሌለ፣ ለአገር የሚጠቅም፣ ከባእድ አጋር ይዘን ብንመጣ ችግር አይኖረውም። ሆኖም ግን የተሻለ ነገር እኛ ጋር እያለ የሌሎችን ማምጣት ተገቢ አይደለም። ፊደል እንደሌለን፣ ቅኝ የተገዛን ይመስል፣ የኛን የተከበረ ፊደል ጥለን ላቲንን ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች መጠቀም ሊበረታታ አይገባም። ሌሎች ክልሎች የተለየ መስመር ቢከተሉም የአማራ ክልል ግን የአገርን ቅርስ በማስጠበቅ አንጻር የመሪነት ሚናውን እንዲወጣም በአክብሮት እንጠይቃለን።

ሦስተኛ፦ የግዕዝ ፊደላትን ለኦሮሞኛ ስለመጠቀም

አፋን ኦሮሞ በላቲንም በግዕዝም ይጻፋል። በኦሮሚያ ክልል በተለይም ኢሕአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ የተወለዱ ወገኖች አፋን ኦሮሞን በላቲን ነው የሚጽፉትና የሚያነቡት። ሆኖም ላቲኑ በጣም ውስንነት አለው። በኦሮሚያ የሚኖሩ ሌሎች ማኅበረሰባትና ከአርባ ዓመት በላይ የሆኑ ኦሮሞዎች ግዕዝ ፊደልን ማንበብ ነው የሚቀናቸው። ቋንቋው በላቲኑ ምክንያት በኦሮሚያ ከተወሰኑ ወገኖች አጥር ውጭ ሊያድግ አልቻለም።

ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ፣ ለተከበሩ አቶ ለማ መገርሳ፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት በታህሳስ ወር 2010 ዓ.ም. በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ከጻፉት ግልጽ ደብዳቤ፣ ለኦሮምኛ ከላቲን ይልቅ ግዕዝን መጠቀም ምን ያህል በኢኮኖሚ፣ በትምህርት ቅልጥፍና፣ በሊንጉስቲክ (ቋንቋ ጥናት) እና በሳይንስ አንጻር የተሻለ መሆኑን አስነብበውናል። ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሶ የጻፉትን፣ ዶ/ር አበራ ሞላ ሌሎች በርካታ ምሁራን ያደረጉትን ጥናት በተወሰነ መልኩ ያካተተ ተያያዥ ሰነድ፣ በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በኦሮሞው ቄስ አባ ኦነሲሞስ ነሲቡ በግዕዝ ፊደላት መጫፈ ቁልቁሉ ተብሎ ከተተረጎመው የኦሮምኛ ቅዱስ መፅሃፍ ውስጥ የተወሰዱ ሁለት ገፆችን አብረን አያይዘናል።

ክቡርነትዎ ሆይ!

እርስዎ አንደሚገነዘቡት፣ በባዕዳን ፊደል የሚጽፉ አፍሪካውያን፣ በአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች ሲገዙ የነበሩና ራሳቸው የፈለሰፏቸው የፊደላት አማራጭ ያልነበራቸው ሕዝቦች ናቸው። እኛ በጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ደምና አጥንት ነፃነታችን ተከብሮልን የኖርንና አኩሪ ቅርስ የሆነ የራሳችን ፊደል ያለን ሕዝቦች ቅኝ እንደተገዙትና እንደተዋረዱት ያልታደሉ ሰዎች ልንሆን አይገባም።

በእዚህና እላይ በተዘረዘሩት የአመክንዮ ምክንያቶች፣ እንዲሁም ስለ ክብራችንና ማንነታችን ሲባል እርስዎና የአስተዳደር ባልደረቦችዎ፣ አፋን ኦሮሞ የኢትዮጵያ ቋንቋ እንደመሆኑ በኢትዮጵያዊ ፊደል በግዕዝ እንዲጻፍ ፈር ቀዳጅ ይሆኑ ዘንድ በአክብሮት እንጠይቅዎታለን። በአንድ ጊዜ ሁሉንም ማድረግ ባይቻልም፣ ቢያንስ በተወሰኑ ለኦሮሚያ ክልል ቅርበት ባላቸው ወረዳዎች በግዕዝ የአፋን ኦሮሞ ትምህርት የሚሰጥበትን ሁኔታ ማመቻቸት ቢቻል በጣም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል ብለን እናስባለን።

በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት፣ በኦሮሞው ቄስ አባ ኦነሲሞስ ነሲቡ፣ በግዕዝ ፊደላት “መጫፈ ቁልቁሉ” ተብሎ የኦሮምኛ ቅዱስ መጽሓፍ ተተርጉሟል። የዛሬ 120 ዓመት እንኳን፣ ቅዱስ መፅሐፍን የሚያህል በራሳችን ፊደላት መፃፍ ከቻልን፣ አሁንማ በዘመነ- ገጽ 4 የ4 ኮምፒዩተር፣ በቀላሉ ኦሮምኛን ግዕዝ በሚባለው ኢትዮጵያዊ ፊደል ያለ ችግር መክተብ የማንችልበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ዋናው ቀና ልቦና፣ በራስ ፊደል ኩራትና ፍላጎት ናቸው!!

ከታላቅ አክብሮት ጋር

 1. ዶ/ር አበራ ሞላ
 1. ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ
 1. ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ
 1. ዶ/ር ባዬ ይማም
 1. ፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ
 1. አትሌት ገዛኸን አበራ
 1. የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ
 1. አቶ ያሬድ ጥበቡ
 1. አቶ ሰይፉ ኣዳነች ብሻው
 1. አቶ ተፈራ ድንበሩ
 1. አቶ ሙሉጌታ ውዱ
 1. አቶ አበባየሁ ደሜ
 1. አቶ ብርሃኑ ገመቹ
 1. አቶ አብርሃም ቀጄላ
 1. አቶ ሃብታሙ ኪታባ
 1. አቶ ግርማ ካሳ

ግልባጭ፣

- ለአማራው ክልል የትምህርት ክፍል ቢሮ

- ለአማራው ክልል የኮሚኒኬሽን መስሪያ ቤት

- ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ክብር አቶ ለማ መገርሳ

- ለባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት

"ግዕዝ ከላቲን ለምን እንደሚሻል የሚያመላክቱ ነጥቦች" በሚል ርዕስ የቀረበውን አባሪ ሰነድ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!