የእኔ ሽበት

"የእኔ ሽበት" አዲስ የግጥም መድብል መጽሐፍ በማትያስ ከተማ (ወለላዬ)

(ኢዛ) በገጣሚ በማትያስ ከተማ (ወለላዬ) ተደርሶ ለንባብ የበቃው “የእኔ ሽበት” የግጥም መድብል መጽሐፍ ቅዳሜ ኦክቶበር 6 ቀን 2018 ዓ.ም. በስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም በርካታ ታዳሚዎች በተገኙበት ተመረቀ። ምርቃቱ የተደረገው ስቶክሆልም፣ ቮርበሪ ሴንትሩም አካባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ የስብሰባ አዳራሽ ሲሆን፤ በዝግጅቱ ላይ የደራሲው ቤተሰቦች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የከተማው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

ዝግጅቱ የተጀመረው በፊርማ ሥነሥርዓት ሲሆን፣ ገጣሚ ማትያስ ከተማ በአዳራሹ እንግዶችን እየተቀበለ፣ በመጽሐፉ ላይ ፊርማውን ሲያኖር ነበር።

የእኔ ሽበት ምረቃ
ገጣሚ ማትያስ ከተማ እንግዶችን እየተቀበለ፣ ፊርማውን በመጽሐፍ ላይ ሲያኖር

መላዕከ ፀሐይ አበበ ገላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን የመድኃኒዓለም አስተዳዳሪ ተገኝተው ዝግጅቱን በጸሎትና በቡራኬ የከፈቱ ሲሆን፤ ከምርቃቱ ጋር ተያያዥነት ባለው ጉዳይ ላይ ትምህርት ሰጥተዋል። በተጨማሪም የደራሲው ወዳጆች የሆኑ ጋዜጠኞችና ደራሲያን መጽሐፉን ቀድመው በመውሰድ ስለደራሲው አጻጻፍ ስልት፣ ስለግጥሙምና መጽሐፉ ይዘት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“የእኔ ሽበት” የተሰኘው ግጥምና የመጽሐፉ ርዕስ ኾኖ የተመረጠው ግጥም፤ ደራሲው ከጃንሆይ መንግሥት ጀምሮ ለሽበት እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ያለውን ሁኔታ ለማሳየት ራሱን ወክሎ የጻፈው ግጥም ሲሆን፤ ሌሎችም በልዩ ልዩ ሁኔታዎች ላይ ያተኮሩ ሀምሳ አንድ ግጥሞች በመጽሐፉ ተካተዋል። ገጣሚ ማትያስ ከተማ በስደት ሕይወት በሚኖርበት በስዊድን፤ አያሌ ግጥሞች በመጻፍና በልዩ ልዩ መድረኮች በማቅረብ የሚታወቅ ሲሆን፤ በተለያዩ የአማርኛ ድረገጾችም ላይ በሚጽፋቸው ግጥሞች በአንባብያን ዘንድ ይታወቃል። በተለይም በኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ ላይ ከሚጽፋቸው ሌሎች ግጥሞች ውጪ፤ “የረቡዕ ግጥም” በማለት በየሳምንቱ ረቡዕ በሚጽፋቸው ግጥሞች ይበልጥ ታዋቂነትን አግኝቷል።

የእኔ ሽበት ምረቃ
በየእኔ ሽበት የግጥም መድብል ምረቃ ላይ የተገኙ ታዳሚዎች በከፊል

በየእኔ ሽበት ምርቃት፤ በርካታ ምሁራን፣ ደራሲዎችና ጋዜጠኖች፣ በዕድሜ የገፉ አዛውንቶችና ወጣቶች በአንድ መድረክ የታደሙበት ከመሆኑም በላይ፤ የተለያዩ የሕብረተሰቡን አባላት ያሰባሰበ ነበር። በስዊድን እንዲህ ያለ የመጽሐፍ ምረቃ ዝግጅት በኢትዮጵያውያን ዘንድ እንብዛም የተለመደ ባይሆንም፤ የእኔ ሽበት ምርቃት እጅግ የደመቀ ነበር።

በመጽሐፉ ላይ ከቀረቡት ግጥሞች መካከል በአስተያየት ሰጭዎቹ ተወስደው ለተሰብሳቢው የተነበቡና አስተያየት የተሰጠባቸው ግጥሞች ታዳሚውን ያሳቁ፣ አሳዛኝ ሆነው እንባ ያስፈሰሱ፣ ያመራመሩና ትዝብት የጫሩ ነበሩ።

ግጥሞቹ ቀለል ያሉና በማንኛውም የዕድሜ ክልልና የግንዛቤ ደረጃ መረዳት የማያዳግቱ እንደሆኑ ከአስተያየት ሰጭዎቹ የተሰነዘረው ሐሳብ ያስረዳል። ብዙዎችን ያሳቀው “ጎሽ እኔ አይደለሁም” የሚለው ግጥም ሲሆን፣ እንደሚከተለው ይነበባል።

ጎሽ እኔ አይደለሁም

አንዱ ከባላገር ብዙ ዶሮ አምጥቶ

በሸጠበት ገንዘብ ጠጥቶ ጠጥቶ

መጠጥ አሸንፎት ሰክሮ ሲወላገድ

ማጅራት መችዎች አግኝተውት መንገድ

እጅግ እጅግ በጣም ሰክሮ ስለነበር

ራሱን ላጭተውት ወስደው ያለውን ብር

ወዳንዱ ስርቻ ወርውረውት አድሮ

በጠዋት ሲነሳ ገንዘብ የለው ዶሮ

ወይኔ እያለ ሲጮህ ቆየና ሲያለቅስ

እጆቹን አንስቶ ራሱን ሲዳብስ

ጭራሽ በራሱ ላይ ሲያጣ ምንም ጠጉር

”ጎሽ እኔ አይደለሁም! አትርፎኛል እግዜር”

በማለት አቅርቦ ለአምላኩ ምስጋና

ራሱን ሊፈልግ ሄደ ተነሳና።

ወለላዬን ከዝግጅቱ በኋላ አነጋግረነው፣ ቀጣይ ሥራው ምን እንደሚሆን ላቀረብንለት ጥያቄ፤ የረቡዕ ግጥሞቹን ማሳተም ተከታይ ሥራው እንደሚሆን ገልጾልናል።

መጽሐፉ በአሁኑ ጊዜ ምርቃቱ በተደረገበት ቮርበሪ በሚገኘው የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ማዕከል የሚገኝ ሲሆን፤ ለወደፊት በቋሚነት የሚገኝባቸው ቦታዎችና ኦንላይን አዝዞ ማግኘት የሚቻልበት መንገድ በቅርቡ ይገለጻል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!