PM Dr. Abiy Ahmed

ጠቅላይ ሚኒስትር (ዶ/ር) አብይ አህመድ

ኢዛ (ረቡዕ መስከረም ፳፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. October 2, 2019):- ጠቅላይ ሚኒስትር (ዶ/ር) አብይ አህመድ የኢትዮጵያን ብልጽግና እና ሕልውናን ሊያስቆም የሚችል አንዳች ነገር የለም ሲሉ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ንግግር ያደረጉት አዲስ አበባን ለማስዋብ ከተያዙ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ አረንጓዴ ልማት የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ባስጀመሩበት ወቅት ነው።

በዕለቱ (መስከረም 20 ቀን 2012 ዓ.ም.) እንደተጀመረው ዐይነት ትልቅ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ ብልጽግና አንድ አካል መሆኑን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እንዲህ ዐይነት ሥራዎች ሲሠሩ አዋራ ከግራና ከቀኝ ሊነሳ ቢችልም፤ አሻራ የማስቀመጡን ተግባር እንገፋበታለን ብለዋል።

ይህንንም አባባላቸውን ለማጠናከር፤ “አዋራ ከግራና ከቀኝ ከፍ ብሎ ሊታይ ይችላል። አሻራችንን እስካስቀመጥን ድረስ ግን፤ የኢትዮጵያን ብልጽግናና ሕልውናን ሊያስቆም የሚችል አንዳች ነገር የለም” ብለዋል።

አያይዘውም፤ “በኢትዮጵያ ብልጽግና ተቃርነው የሚቆሙ ኃይሎች ካሉ ለምን ቆሙ ከሚለው ሐሳብ በፊት፤ ኢትዮጵያውያን እንዲገነዘቧት የምፈልገው እኔና እናንተ እንቁላል ፍርፍር ጠብሰን ለመብላት ከተስማማን፤ የግድ እንቁላሉ መሰበር አለበት። የእንቁላሉ ባለቤት ዶሮዋ ግን በቀላሉ የምትስማማበት ጉዳይ አይሆንም።

“ዶሮዋ እንቁላሏ ከሚሰበር አቅፋ ጫጩት መፈልፈል ትፈልጋለች፣ እኛ ደግሞ እንቁላሉን ሰብረን ጠብሰን ልንበላ እንፈልጋለን። ይህንን ለውጥ ተቃርኖ መገንዘብ ያስፈልጋል። ዶሮዋ እንቁላሏን ከመሰበር አታድነውም። እኛም እንቁላላችንን ፈርፍረን ከመብላት አንመለስም፤ ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች።” በማለት ተናግረዋል።

ይህንን የአዲስ አበባን የማስዋብ ሥራ በአንዳንድ ወገኖች ትችት የሚሰነዘርበት የነበረ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ቃል በተገባው መሠረት ሥራውን እንገፋበታለን ብለዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ