Ethiopian Citizens for Social Justice Party (E-Zema)

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ - ፍትሕ (ኢዜማ)

ከተቋቋመ ጀምሮ የመጀመሪያ መግለጫው ነው

ኢዛ (ረቡዕ መስከረም ፳፰ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. October 9, 2019):- የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ - ፍትሕ (ኢዜማ) በመባል የሚታወቀው ፓርቲ ለመጀመሪያ ጊዜ የአገሪቱን ጉዳይ በተመለከተ “የኢትዮጵያ ሕዝብ የፍትሕና የነፃነት ጥያቄ በግዴለሽነት በሚንቀሳቀሱ ሰዎችና ተግባራቸው እንዳይታጠፍ ሁሉም ዘብ ሊቆም ይገባል” በማለት መግለጫ አውጥቷል።

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመትከል በትግላችን ያገኘነው አራት እድሎች መክነውብናል በማለት መግለጫውን የጀመረው ኢዜማ፤ በ2007 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ የፓርማውን ወንበር ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር የቻለው በዜጎች ቆራጥ ትግል መሆኑን እንደማሳያ ጠቅሶ አሁንም የተገኘውን ድልና የለውጥ ሂደትን ወደቀድሞው ለመመለስ የጠለፋ ምልክቶች እየታዩ እንደሆነ አስታውቋል።

ኢዜማ በመግለጫው፣ “አሁንም ለገጠመን ሁኔታ በአንድነት መቆም አለብን” በማለት አሳስቧል። የአንድ ወገንን አሸናፊነት ታሪክ መፍጠር ኃላፊነት የጎደለው ተግባር እንደሆነና ኢዜማ እውነተኛና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መደላድል ለመፍጠር የበኩሉን አስተዋጽኦ እየተወጣ እንዳለ ገልጾ፤ ለውጡ የጋራ ትግል ውጤት መሆኑን የዘነጉ ቡድኖችን እንቃወማለን በማለት 7 ነጥብ ያለው የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

በመግለጫውም የአማራና የቅማንት ሕዝብ አንድ ሕዝብ እንደሆነ፣ የፀቡ መነሻ በክፋት የተዋቀረ ፊዴራላዊ አሠራር መሆኑንና ይህም የተንኮል አካሄድ እንዲቆም፣ የሃይማኖትና ባህላዊ ክንውኖች ከፖለቲካ ነፃ መሆን እንደሚገባቸው፣ በእሬቻ በዓል ላይ የሰባሪና/ተሰባሪ ትርክት መቅረቡ አግባብ እንዳልሆነ፣ የአዲስ አበባን ሕዝብ ትዕግሥት የሚፈታተኑ ነገሮች እንዲቆሙ፣ ለከተማ ፖሊሶች እንዲሆን የተመረጠው የደንብ ልብስ ለፖሊስ አገልግሎት የሚመች እንዳልሆነ፣ በአማራ የሚከሰቱ ግጭቶችን ወሬ እየፈበረኩ ግጭቶችን በሚያዋልዱ ሚዲያዎች ላይ የብሮድካስት ባለሥልጣን አስተማሪ ርምጃ እንዲወስድ፣ ዘረኛነት ከፋፋይ በመሆኑ ለመጨረሻ ጊዜ መቆም እንዳለበት የጠቀሰው መግለጫ በሁሉም ነጥቦች ላይ ማብራሪያና ትንታኔ ሰጥቷል።

መግለጫው በውጪ አገርም ሆነ በአገር ውስጥ ያለው ሕዝብ ኢዜማ አደረጃጀት ውስጥ በመግባት ፓርቲውን እንዲቀላቀል በመጋበዝ፤ የተጀመረው የዴሞክራሲ ጉዞ ዳር እንዲደርስ እንዲያግዝ ጥሪ አቅርቧል። የማሕበረሰቡም መሪዎች ለአገር ሰላምና ለሕዝብ መረጋጋት ዘብ መቆም የሚገባቸው ዛሬ እንደሆነ ገልጾ፤ ኢዜማ የአገር አንድነትን ለማስቀጠል ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከሁሉም ቅድሚያ እሰጣለሁ ብሏል። ለዚህም አስፈላጊ መሥዋዕትነት ለመክፈል ወደኋላ እንደማይል በማስታወቅ መግለጫውን ደምድሟል።

ኢዜማም ኾነ ጥምረቱን የፈጠሩት (ግንቦት ሰባትና ሌሎቹም) ፓርቲዎች በሕዝብ መፈናቀል በደረሰበት ጊዜ፣ ግድያና ዘረፋ በየቦታው ሲፈጸም እንዲሁም በአዲስ አበባ ጉዳይና በአገሪቱ በተፈጸሙ ማንኛውም ሁኔታዎች ላይ አንድም መግለጫ ሳይሰጥ ቆይቶ ይህ የመጀመሪያው መግለጫ አድርጎ ማውጣቱ ለብዙዎች የመነጋገሪያ ርዕስ ለመኾን በቅቷል። የመግለጫው ሙሉ ቃል እዚህ ይገኛል! (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ