የረሃብ አደጋው ጨምሯል፣ ራያ እና እንደርታ ክፉኛ ተጠቅተዋል 

Ethiopia Zare (ዓርብ መስከረም ፪ (2) ቀን ፳፻፩ (2001) ዓ.ም. September 12, 2008)፦በመላው በኢትዮጵያ በቅርቡ በተለያዩ የዕርዳታ ድርጅቶች በተደረገ የዳሰሳ ጥናት በትግራይ በጣም በድርቅ አደጋው የተጠቁት ራያ እና እንደርታ ሲሆኑ፣ በእነዚህ አካባቢዎች 127 ሺህ ህዝብ በድርቁ ተጎድቷል። በአምስት የትግራይ ዞኖች 601 ሺህ ህዝብ አጣዳፊ ዕርዳታ፣ 162 ሺ ህዝብ ደግሞ የቅርብ ክትትል ያስፈልገዋል። በኢትዮጵያ ለተከሰተው ረሃብ ከሚያስፈልገው ዕርዳታ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተገኘው ከግማሽ የማይበልጥ መሆኑ ታውቋል።

 

በኢትዮጵያ በረሃብ ለተጠቁ ወገኖች የሚያስፈልገውን የምግብና ተዛማጅ ዕርዳታዎች ለማቅረብ ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የተገኘው ገንዘብ ከሚፈለገው ከግማሽ የማይበልጥ መሆኑ ታወቀ።

 

በመላው ሀገሪቱ የተከሰተው የረሃብ አደጋ በትግራይ ክልል አምስት ዞኖች ውስጥ ከሚገኙ፣ 31 የገጠር ወረዳዎች የተገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በአምስት የትግራይ ዞኖች ከሚገኘው 3 ነጥብ 49 ሚሊዮን ህዝብ 601 ሺህ የሚሆነው በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኝ እና አጣዳፊ ዕርዳታ የሚፈልግ ነው። ከዚህ በተጨማሪ 162 ሺ ህዝብ የቅርብ ክትትል የሚያስፈልገው መሆኑ ታውቋል።

 

በዓለም አቀፍ የምግብ ፕሮግራም፣ በአደጋ መከላከል ዝግጁነት ኮሚሽን እና በሌሎች ዕርዳታ ድርጅቶች አማካኝነት በመላው ሀገሪቱ የዳሰሳ ጥናት ተካሂዷል። በጥናቱ መሰረት በትግራይ በጣም በድርቅ አደጋ የተጠቃው በደቡብ ዞን “ራያ” የተባለ አካባቢና በምሥራቅ ትግራይ ደግሞ “እንደርታ” አካባቢ መሆኑ ታውቋል። በአካባቢው 127 ሺህ ህዝብ በድርቅ ተጎድቷል። በትግራይ የዳሰሳ ጥናቱ የተካሄደባቸው ደቡባዊ ዞን፣ ደቡባዊ ምሥራቅ ዞን፣ ማዕከላዊ ዞን፣ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞንና ምሥራቅ ዞን ናቸው።

 

በዚህ መሠረት በነኀሴ ወር የተደረገው ሪፖርት እንደሚጠቁመው፣ ጥናቱ የተደረገው በትግራይ በገጠር ወረዳዎች ብቻ በመሆኑ ከተሞችን አያካትትም። በዚህ ጥናት መሰረት 25 በመቶ የሚሆነው ህዝብ የምግብ ዕርዳታ ይፈልጋል።

 

ባለፈው ሣምንት ኢትዮጵያን የጎበኙት ጆን ሆልምስ ከጉብኝታቸው በኋላ በሰጡት መግለጫ በኢትዮጵያ ያለው የረሃብ ቀውስ አሁንም አደገኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና፣ በረሃብ የተጠቁ ሰዎች ቁጥርም በየጊዜው እየጨመረ እንደሚሄድ ገልፀው ነበር።

 

የተባበሩት መንግሥታት በኢትዮጵያ በረሃብ የተጎዱ ሰዎችን በምግብ እና ተዛማጅ ዕርዳታዎች ለመርዳት ከሚፈልገው ከ3 ነጥብ 52 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ውስጥ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያገኘው ግማሽ የሚሆነውን ያህል ነው። በኢትዮጵያ እስከ 8 ሚሊዮን የሚደርስ ህዝብ በረሃብ የተጠቃ ሲሆን፣ በዚሁ ምክንያት ሰዎች እየሞቱ መሆናቸውን ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኀን እየዘገቡ ይገኛሉ።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ