Zamzam Bank

ዘምዘም ባንክ የመጀመሪያው ከወለድ ነፃ ባንክ

በሸሪዓ ሕግ የሚሠራ የመጀመሪያው ከወለድ ነፃ ባንክ ይኾናል

ኢዛ (ሐሙስ ጥቅምት ፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. October 17, 2019):- ራሱን የቻለ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመሥጠት የሚያስችል ባንክ ለማቋቋም ሲንቀሳቀስ የቆየው ዘምዘም ባንክ አክስዮን ማኅበር፤ ወደሥራ ለመግባት የሚያስችለውን ካፒታል ማሰባሰብ መቻሉን አስታወቀ።

ከባንኩ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕግ መሠረት አንድ ባንክ ለማቋቋም ከሚጠይቀው 500 ሚሊዮን ብር በላይ የተከፈል ካፒታል የሚያስፈልገው ሲሆን፤ ባንኩ ሲያካሒድ ከነበረው የአክስዮን ሽያጭ ሕጉ ከሚጠይቀው ገንዘብ በላይ አሰባስቧል።

ከ650 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል አሰባስቧል

እስከ መስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ባካሔደው የአክስዮን ሽያጭ 1.3 (አንድ ነጥብ ሦስት) ቢሊዮን ብር የሸጠ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከ650 ሚሊዮን ብር በላይ የሚኾነው የተከፈለ በመኾኑ፤ ባንኩን ሥራ ለማስጀመር እንደሚችልም ገልጿል።

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በመደበኛ ባንኮች ውስጥ በመስኮት ደረጃ እንዲጀመር ምክንያት የኾኑት የዘምዘም ባንክ አደራጆች፤ ራሱን የቻለ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሠጥ ባንክ ለማቋቋም ከ13 ዓመታት በላይ ቆይተዋል።

ባንኩ ከቀጥዩ ወር ጀምሮ ወደሥራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህም በሸሪዓ ሕግ የሚሠራ የመጀመሪያው ከወለድ ነፃ ባንክ ያደርገዋል።

ከጥቂት ወራት በፊት በወጣው ሕግ መሠረት፣ ከወለድ ነፃ ራሱን የቻለ ባንክ ለማቋቋም እንደሚቻል ከተደነገገ ወዲህ ከዘምዘም ባንክ ሌላ በተመሳሳይ ከወለድ ነፃ ባንክ ለማቋቋም ሦስት ባንኮች የአክስዮን ሽያጭ እያደረጉ መኾኑ ይታወቃል።

ራሱን ከቻለ ባንክ ሌላ በአሁኑ ወቅት 11 የአገሪቱ ባንኮች በመስኮት ደረጃ አገልግሎቱን እየሠጡ መኾናቸውን ለማወቅ ችለናል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ