Ethiopian Prime Minister Abiy Ahmed shakes hands with Egyptian President Abdel-Fattah el-Sissi, June 10, 2018

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድና የግብጹ ፕሬዝዳንት ኤልሲሲ ሰኔ 3 ቀን 2010 ዓ.ም. በግብጽ ዋና ከተማ ካይሮ በተገናኙበት ወቅት

“ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ አለባት” የግብጽ መገናኛ ብዙኃን

ጠ/ሚ ዐቢይ እርምጃ ይወሠዳል በሚል ለሚሰማው ነገር፤ ውጊያ መፍትሔ አለመኾኑን ተናገሩ

ኢዛ (ማክሰኞ ጥቅምት ፲፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. October 22, 2019)፦ በዛሬው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከአባላቱ ካቀረቡዋቸው ጥያቄዎች ውስጥ ግብጽ በህዳሴው ግድብ ላይ እያሳየች ያለችው አቋምን የሚያመለከት ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። ግብጽ እያደረገች ያለችው እንቅስቃሴ ስጋት አይኾንም ወይ? የሚል ይዘት ነበረው።

ለዚህ ጥያቄ ጠቅላይ ሚንስትሩ በሠጡት ምላሽ ያስቀደሙት፤ “ማንም ኃይል ኢትዮጵያን ከህዳሴው ግድብ ግንባታ ሊያስቆም አይችልም” የሚል ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ከህዳሴ ግድብ ግንባታ በተያያዘ ግብጽንም ኾነ ሱዳንን የመጉዳት ፍላጎት የለውም ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ኢትዮጵያ ግድቡን የምትሠራው የማንንም ጥቅም ለመንካት ሳይኾን፤ የሚገባትን ጥቅም ለማግኘት መኾኑን አስረድተዋል።

ከዚህ ውጭ ግን፤ እርምጃ ይወሠዳል በሚል ለሚሰማው ነገር፤ ውጊያ መፍትሔ አለመኾኑን አስገንዝበዋል።

አስፈላጊ ከኾነ ግን ሁሉም ባለው አቅም ሊሠራ ይችላል በማለት፤ ሕዝቡ መገንዘብ የሚኖርበት ብለው የጠቀሱት፤ ምንም ኃይል ከህዳሴው ግድብ ግንባታ ኢትዮጵያን ሊያስቆማት የማይችል መኾኑን ነው።

መንግሥት ከዚህ በፊት የተጀመሩ ፕሮጀክቶቻችን ያስቀጥላል በማለት፤ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የኢትዮጵያ ክብርና ጥቅም በሚያስከብር፣ ምኞትና ፕሮፓጋንዳን ለይቶ በሳይንሳዊ መንገድ በእውቀት ላይ በተመሠረት ፕሮጀክት ማኔጅመንት፤ እንዲሁም የታችኛውን የተፋሰስ አገሮችን በማይጎዳ ሁኔታ የሚሠራ መኾኑንም አስገንዝበዋል።

ግብጽ በግድቡ ዙሪያ አዲስ ጥያቄ ካነሳች ወዲህ ከግብጹ ፕሬዝዳንት ኤልሲሲ ጋር በስልክ ጭምር ማውራታቸውን ገልፀው፤ ነገ ወይም ከነገወዲያ በግንባር ፕሬዝዳንቱን እንደሚያገኙና እንደሚወያዩበት አመልክተዋል።

ይህንን ምላሽ ከሠጡ ከሰዓታት በኋላ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከኤልሲስ ጋር በግንባር ይመክሩበታል ተብሎ ወደ ተጠቀሰው ሞሥኮ አምርተዋል።

በተያያዘ ዜና በግብጽ የሚገኙ የመገናኛ ብዙኃን፤ ኢትዮጵያ ግብጽ ያቀረበችላትን ስምምነት ባለመቀበልዋ፤ ግብጽ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ ይገባታል በማለት ጫናና ግፊት እየፈጠሩ መኾናቸውን ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እየዘገቡ ይገኛሉ። በዛሬውም ዕለት የዘገቡ አሉ። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ