የመጀመሪያው ቡድን ዛሬ ወደ ደሴ ይጓዛል

Ethiopia Zare (ሰኞ ጥቅምት 10 ቀን 2001 ዓ.ም. October 20, 2008)፦ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ሕጋዊ ፈቃዱን ካገኘ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በየክልሉ ከተሞች ጽ/ቤቶችን ለመክፈትና ከህዝብ ጋር ውይይት ለማድረግ በወ/ት ብርቱካን የሚመራው የልዑካን ቡድን ዛሬ እንቅስቃሴ መጀመሩን የድርጅቱ ቃል አቀባይ ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ በተለይ ለኢትዮጵያ ዛሬ አረጋገጡ።

 

አንድነት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚጓዙ ልዑካኖችን ያዘጋጀ ሲሆን፣ የመጀመሪያውን ልዑክ በመምራት የድርጅቱ ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እና አቶ ተመስገን ዘውዴ ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 10 ቀን 2001 ዓ.ም. የደቡብ ወሎ ዋና ከተማ ወደሆነችው ደሴ ከተማ መጓዛቸው ታውቋል።

 

ልዑካኑ አደራጅ አባላትን ያካተተ ሲሆን፣ በደሴ ከተማና አካባቢው የሚገኙ የቀድሞ ቅንጅት አባላትና ከከተማው ነዋሪዎች ጋር ውይይት እንደሚደረግና የመጀመሪያውን ጽ/ቤት እንደሚከፈት ለማወቅ ችለናል። በተመሳሳይ ልዑካን ቡድኑ ጉዞውን በሰሜን ወሎ በመቀጠል በአምስት ቀናት ቆይታ በአጠቃላይ ሦስት ጽሕፈት ቤቶችን እንደሚከፍት ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ገልፀዋል።

 

ሁለተኛው የልዑካን ቡድን በመጭው ቅዳሜ በጎጃምና ጎንደር አካባቢ በመጓዝ ተመሳሳይ ውይይቶችን በማድረግ ጽ/ቤቶችን የሚከፋት ሲሆን፣ ሦስተኛው የልዑካን ቡድን ደግሞ በኦሮሚያ ክልል በተለይ በአርሲ፣ አሰላና በሌሎች ዋና ዋና ከተሞች ከህዝብ ጋር በመወያየት ጽ/ቤቶችን ይከፈታሉ።

 

አንድነት በተመሳሳይ አራተኛውን የመልዕክተኞች ቡድን በጅማና አካባቢው የሚልክ ሲሆን፣ በመቀጠልም በየክልሉ ብዙ ህዝብ በሚኖርባቸው አካባቢዎች ልዑካንን በመላክ ጽ/ቤቶችን እንደሚከፍት ለማወቅ ችለናል።

 

አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ለድርጅቱ ሥራ ማስፈጸሚያና ቢሮዎችን ለመክፈቻ በያዝነው ዓመት (2001 ዓ.ም.) ብቻ 7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው መግለጹን መዘገባችን አይዘነጋም።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!