"ውሳኔው ለሕዝብ ማስተማሪያ ነው" ካሚላት መህዲ

"ውሳኔው ፍትሃዊ አይደለም" ወላጅ እናቱ

Kemilat MehadiEthiopia Zare (ቅዳሜ ጥር 24 ቀን 2000 ዓ.ም. February, 2,2008)፦ ልደታ የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ረቡዕ ጥር 21 ቀን 2000 ዓ.ም. በካሚላት መህዲ ላይ አሲድ በደፋው ደምሰው ዘሪሁን ላይ የሞት ቅጣት ሲወስንበት፤ በዚሁ መዝገብ ላይ በተባባሪነት በተከሰሰው ያዕቆብ ኃይለማርያም ደግሞ በ20 ዓመት ጽኑ እንዲቀጣ ውሳኔ አስተላልፏል። ወ/ት ካሚላት በችሎቱ አዳራሽ ተገኝታ ነበር።

በዕለቱ ከፍተኛ ቁጥር የነበረው ህዝብ ችሎቱን የተከታተለ ሲሆን፣ ከእነሱም ውስጥ የካሚላት ቤተሰቦችና ወዳጆች፣ የሁለቱም ተከሳሾች ቤተሰቦችን ወዳጆች፣ ጋዜጠኞች፣ ጉዳዩን የፍርድ ሂደቱን ሲከታተሉ የነበሩ ወገኖች ይገኙበታል። የሰው መጨናነቅ ከታየባቸው ችሎቶች ይኸኛው የመጀመሪያውን ደረጃ እንደሚይዝ በርካታ ችሎቶችን የተከታተሉ ወገኖች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። አዳራሹ ሞልቶ ከውጭም በርካታ ህዝብ የነበረ ሲሆን፣ በግምት በአዳራሹ ውስጥ ከ350 የማያንስ ህዝብ ነበር።

የፍርድ ቤቱ ሙሉ የችሎት ውሎ የሚከተለውን ይመስላል። ከጠዋቱ አራት ሰዓት ከ30 ደቂቃ ሲሆን ዳኞች ተከስተ ብርሃን ታዬ፣ ብርሃነ መስቀል ዋግሬ፣ ፍእዲ ሑሴን በማርፈዳቸው ይቅርታ ጠይቀው ነበር የተሰየሙት።

መዝገቡ የተቀጠረው ተከሳሾች በጋራ አባሪ ተባባሪ በመሆኑ በወ/ት ካሚላት መህዲ ላይ ሰልፈሪክ አሲድ በመድፋት ጉዳት ማድረሳቸው በመረጋገጡ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ገለጸ።

የቅጣት ውሳኔውንም በጽሑፍ ማንበብ ጀመረ። ተከሳሹ ደምሰው ዘሪሁን ሆን ብሎ አስቦና ፈቅዶ በካሚላት ላይ አሲድ በመድፋት የመግደል ሙከራ ማድረጉ በዐቃቤ ሕግ ክስ ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ በክርክር ሂደት ውስጥ የነበረ ጉዳይ ነው።

ፍርድ ቤቱም ክርክሩን ሲያዳምጥ ከቆየ በኋላ የጥፋተኝነት ውሳኔ በተጠቀሰው ቀን ሲሰጥ የዐቃቤ ሕግንና የሁለቱን ተከሳሾችም የቅጣት አስተያየት ተቀብሏል።

Demsew Zerihunዐቃቤ ሕግ ባቀረበው የቅጣት አስተያየትም አንደኛ ተከሳሽ ደምሰው ሆን ብሎ አስቦና አቅዶ እጅግ ከባድ በሆነው አደገኛ ሰልፈሪክ አሲድ የሰው መግደል ሙከራ በመፈጸማቸው በአንቀጹ ላይ በተደነገገው በመጨረሻው ፍርድ “በሞት” እንዲቀጣ ጠይቋል። ለቅጣት ማክበጃውም ደምሰው በተለያዩ አራት መዝገቦች ክስ ያለበት መሆኑ ጠቅሷል።

ሁለተኛ ተከሳሽም ጥፋተኛ ከተባለው ከደምሰው ጋር ወንጀሉን ለመፈጸም ተስማምተው ያደረጉት በመሆኑ በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲቀጥሉት ጠይቋል።

ደምሰው ባቀረበው አስተያየትም በካሚላት ላይ እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት አለመፈጸሙን እሷም ሆነ ቤተሰቦቿ እንደሚያውቁ ጠቅሶ፤ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ነው ካለው የተሰጠውን ፍርድ እንደሚቀበል ተናግሯል።

በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ ፍርዱን ሲሰጥ የ87 ዓመት ዕድሜ ያላቸው አያቱን፣ የ58 ዓመት ዕድሜ ያላቸው እናቱን በአጠቃላይ ስድስት ቤተሰብ የሚያስተዳድር መሆኑን በመግለጽ ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን እንዲያቀልለት ጠይቋል።

በሁለተኛ ተከሳሽነት ጥፋተኛ የተባለው ተከሳሽ ያዕቆብ በበኩሉ ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት እንደሆነ እና በተጨማሪም ሌሎች ቤተሰቦችን እንደሚያስተዳድር እሱ በመታሠሩ ቤተሰቦቹ ችግር ላይ መሆናቸውን ገልጾ ቅጣቱ እንዲቃለልለት ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት መመርመሩን በንባብ በማሰማት የቅጣት ውሳኔውን ሰጥቷል።

የቅጣት ውሳኔውን ያነበቡት የቀኝ ዳኛው ብርሃነ መስቀል ዋገሬ ሲሆኑ፣ ጋብቻ እንኳን የሚፈጸመው በሁለቱ ተጋቢዎች መልካም ፈቃድ እንጂ በማስገደድ አለመሆኑ በሕግ መደንገጉን፤ ነገር ግን ወ/ት ካሚላት አብራ ላለመሆን እንቢታዋን በምታሳይበት ጊዜ አንደኛ ተከሳሽ አቶ ደምሰው ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በክፉ ልቦና ተነሳስቶ 94 በመቶ አስደሳች ያለው የሆነ ያልተለመደ ሰልፈሪክ አሲድ በመድፋቱ ጨካኝነቱን፣ ነውረኛነቱንና አረሜነነቱን አሳይቷል ሲሉ በንባብ አሰሙ።

“ፍርድ ቤቱም የሚከተለውን ትዕዛዝ ሰጥቷል” ሲሉ ቆሙ።

በፍርድ ቤት የቅጣት ውሳኔ ሲነበብ ዳኞች የሚቆሙት ለአንዲት ውሳኔ ብቻ እንደሆነ የሚያውቁ ፊታቸውን እንዳቀጨሙ አብረው ቆሙ አዳራሹ ውስጥ ውሳኔውን ለመስማት በተሰበሰበው ሰው ላይ ድንጋጤ ተፈጠረ። ይህ ድንጋጤ በተለይ በቤተሰቦቹ ላይ ከፍተኛ እንደሚሆን የማያጠራጥር ነው። ዳኛው የጀመሩትን የቅጣት ውሳኔ ንባብ ቀጥለው “አቶ ደምሰው ዘሪሁን በሞት እንዲቀጣ ወስነናል” ሲሉ ውሳኔያቸውን አስተላልፈው ተቀመጡ።

ከቤተሰቦቹና ወዳጅ ዘመዶቹ እንደሆነ የሚገመት ጩኸት በችሎቱ አዳራሽ አስተጋባ “ጸጥታ፣ ጸጥታ” ሲሉ የችሎት ሥነ-ሥርዓት አስተባባሪዎች አስጠነቀቁ።

ዳኛው የቅጣት ውሳኔያቸውን በሁለተኛ ተከሳሽ ላይ ማሰማት ቀጠሉ - ሁለተኛው ተከሳሽ ያዕቆብ ኃይለማርያም በ20 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወሰኑና ትዕዛዝ አስተላለፉ።

የፍርዱ ፍፃሜ የሚሆነው የአገሪቱ ርዕስ ብሔር (ፕሬዝዳንት) ሲያጸድቀው መሆኑን በመግለጽ ማረሚያ ቤት ተከታተሎ እንዲያስፈጽም አዘዘ። ተከሳሾች ይግባኝ መብት አላቸው ሲሉም ጠቆሙ። በመጨረሻም “መዝገቡን ዘግተን ወደ መዝገብ ቤት መልሰናል” በማለት ትዕዛዛቸውን አጠናቀቁ።

የችሎቱ መተራመስ ጨመረ። በካሚላት ቤተሰቦች ፊት ላይ ደስታ ነው ሊባል የሚችል የተለየ ነገር ባይነበብም እንዳልተከፉ ለመረዳት ይቻላል። የደምሰው ቤተሰቦች ግን ኀዘናቸውን ከአዳራሹ ጀምሮ በለቅሶ መግለጽ ጀመሩ።

አንድ ዘገባ በዕለቱ አመሻሽ ላይ በጋዜጠኞች “የተሰጠው የፍርድ ውሳኔ ትክክልና ተመጣጣኝ ነው ወይ? አንዳንድ ሰዎች ፍርዱ ተጋኗል ይላሉ። ጉዳትሽን አንቺ ነሽ የምታውቂውና አንቺ ስለፍርዱ ያለሽ አመለካከት ምንድን ነው? የደረሰብሽን አደጋ የተሰጠው ፍርድ ይመልሰዋል ትያለሽ?” የሚሉ ጥያቄዎች ለካሚላ ቀርበውላት እንደነበር ገልጿል። ካሚላም በውስጧ የሚሰማትን ስሜትና ጉዳቷን የተፈረደው ፍርድ እንደማይመልሰው ገልጻ፤ ነገር ግን በእሷ ምክንያት የተሰጠው ፍርድ ለህዝብ ትምህርት ይሆነዋል ስትል ለጋዜጠኞቹ ገልፃለች።

እሷ አንድ ግለሰብ መሆኗን የተፈረደው ደግሞ የመንግሥት ፍርድ መሆኑን፣ በደረሰው ነገር ፍርድ ቤቱ ገምግሞ የራሱን ውሳኔ መስጠቱን በመጠቆም፤ በዚህ ደግሞ ጣልቃ ገብቼ የምናገረው ነገር የለኝም ስትል ሃሳቧን ገልጻለች።

“ቅጣቱ በዝቷል የሚሉ ወገኖች አሉ” የሚለውን ጥያቄ ስትመልስም ውስጧ የሚሰማትን ስሜት ለመግለጽ መቸገሯን በመጠቆም ሁሉም ሰው ሲደርስበት ወይም የጉዳቱ ተጠቂ ብቻ ሲሆን ስሜቱን እንደሚያውቅ ተናግራ፣ ውስጧ ያለውን ስሜት በቃላት ለመግለጽ እንደምትቸገር ገልጻለች።

ካሚላት በአሁኑ ሰዓት በፈረንሳይ አገር በሼኽ ሙኸመድ ሁሴን አሊ ዓል አሙዲ ለተደረገላት የገንዘብ ድጋፍ ደግማችሁ ደጋግማችሁ፣ አመስግኑልኝ ብላለች።

በሞት እንዲቀጣ የተወሰነበት የደምሰው ዘሪሁን እናት ወ/ሮ ሐረገወይን ላቀው የሚኖሩት ቀጨኔ መድኃኔዓለም ሲሆን፣ እሳቸውንም ከፍርድ ውሳኔው በኋላ ጋዜጠኞች እመኖሪያ ቤታቸው ድረስ በመሄድ አነጋግረዋቸው ነበር።

ወ/ሮ ሐረገወይን በተሰጠው ፍርድ ላይ ቅሬታ እንዳላቸው ተጠይቀው “ፍርድ ቤቱ ሚዛናዊ ፍትህ አልሰጠም ወደ አንድ ወገን አመዝኗል” ብለዋል። “ፍትህና የሕግ የበላይነት ሲባል እኔን እንደሚገባኝ ከሆነ እኩል በሆነና ለማንም ወገን ባላጋደለ ሁኔታ ዳኝነት የሚሰጥ እንደሆነ አውቃለሁ። ነገር ግን በልጄ ላይ የተፈረደው ፍርድ ሕጋዊ አይደለም” ይላሉ።

የመከላከያ ማስረጃውን በሚገባ አቅርቧል። ከፎቶ ግራፍ ጀምሮ በሰው ምስክር አስመስክሯል። የከሳሽ ወገን ምስክሮችም ቢሆኑ እሱ ሲደፋ አየን ያለ የለም። በአጠቃላይ ፍርዱ ፍትሐዊ እንዳልሆነ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

Kemilat & Demsew“በእርግጥ የካሚላት ጉዳት እንደ እናትነት ሆኜ ሳስበው አዝናለሁ። ድርጊቱን የፈጸሙባት ተገኝተው ቢቀጡ ደስ ይለኛል። ነገር ግን ልጄ ይህን ድርጊት አልፈጸመም። ይህን ያልኩበት ምክንያት ደግሞ፤ እንደ ዓይን ብሌን የሚሳሳላት፣ ለእሷ ብሎ የኔን የእናቱን ቤት ጥሎ የወጣ ኃይማኖቱን እስከመቀየር የደረሰ፤ እንኳን እንቢ ልትለው ቀርቶ ድርጊቱ ተፈጸመባት እስከተባለው እስከመጨረሻዋ ሣምንት ድረስ አብረው በፍቅር የነበሩ ... የሚያስተዳድረን እሱ ቢሆንም ሁለቱ አንድ ላይ በፍቅር ከመሆናቸው የተነሳ የሚሰፍርልን ቀለብ የሚደርሰን በእሷ በኩል ሲሆን፣ እኛም የምንጠይቀው እሷን መሆኑን ለመጋባት የወሰኑ መሆናቸው፣ ለዚህም ዝግጅት እያደረጉ እንደነበር ነው። ለዚህም በየጊዜው የተገናኙበትን ዓመት እዚሁ ቤት ሲያከብሩ የተነሱት እና ለሚዲያ የማይወጡ የተለያዩ ፎቶግራፎች ምስክሮቼ ናቸው” ብለዋል።

“በተጨማሪም የእሱ ፍቅረኛ ስለመሆኗ አንድም የማያውቃት የዚህ አካባቢ ነዋሪ የለም። ፍቅረኛ ብቻ ሳይሆን እስከ መጨረሻዋ ሰዓት ጸብ እንዳልነበራቸው መንደርተኛው ይመሰክርልኛል። አብዛኛውን ጊዜዋን እዚህ ነው የምታጠፋው። በአጠቃላይ ምኑን ዘርዝሬ ምኑን እንደምተወው አላውቅም። ግን በአጠቃላይ ፍርዱ ሚዛናዊ ያልሆነ ነው” ብለዋል።

በፍርዱ ፍትህ እናገኛለን ብለው እንደጠበቁም ገልጸው፤ ግን ሚዲያው ሁሉ ለእርሷ አድልቶ፣ ሴቶች ጉዳይ ለእሷ አድልቶ ስለነበር ይህ ጫና በፍርድ ቤቱም ላይ ተንጸባርቋል ብለዋል። እውነቱን ለማውጣት ግን እስከመጨረሻው የፍትህ አካል ድረስ በመቅረብ አቤት እንደሚሉ አረጋግጠዋል።

“ደምሰው ካሚላትን አስገድዷት ያለፍላጎቷ እንዳልሆነና ሁለቱም በፍቅር አብረው እንደነበሩ ለእኔም ሕዝብ ይፍረደኝ። እውነቱን ግን አሁንም እግዚአብሔር ቀጣዩን የፍርድ ሂደት ይፍታልኝ” ብለዋል።

የደምሰው ታናሽ እህት ይሉሻል ዘሪሁን በበኩሏ ደምሰው በሷ ላይ ይህን ድርጊት እንደማይፈጽምባት እና “ሁለቱ እጅግ በጠነከረ ፍቅር ውስጥ እስከመጨረሻው ሣምንት ማለትም ቅዳሜ ድርጊቱ ሊፈፀም እስከ ኀሙስ ድረስ አብረው እንደነበሩ የማውቅ ምስክር ነኝ። እሱ ይህን ድርጊት በእሷ ላይ አይፈጽምም። ድርጊቱን እሱ እንዳልፈጸመባትና እንደፈጸመባት መናገር የምትችል ብቸኛዋ ምስክር ደግሞ እሷ ብቻ ናት” ብላለች።

ሁለቱም የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው ተከሳሾች ይግባኝ ማለት እንደሚችሉ ታውቋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ