በ2000 ዓ.ም የጀት ዓመት 93.5 ሚሊዮን ብር ለመንግሥት ቀረጥ ከፍሏል

Ethiopia Zare (እሁድ ጥቅምት 23 ቀን 2001 ዓ.ም. November 2, 2008)፦ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ የግል ባንኮች አንዱ የሆነው ዳሽን ባንክ፣ ባለፈው በጀት ዓመት (2000 ዓ.ም.) 239 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ አገኘ።

 

ባንኩ ኀሙስ ዕለት በሼራተን ሆቴል ባካሄደው በ14ኛ መደበኛ ዓመታዊ አጠቃላይ የባለአክሲዮኖች ጉባዔው እንደገለፀው፣ እየሰጠ ካለው የዌስተርን ዩኒየን ሐዋላ አገልግሎት በተጨማሪ፣ በኢትዮጵያ የመኒ ግራም ወኪል በመሆን የሐዋላ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልፆ፤ ከዚህም በተጨማሪ ከቪዛ ካርድ በተጨማሪ የኢንተርናሽናል ማስተር ካርድ ማስተናገድም እንደሚጀምር ተገልጿል።

 

የዳሸን ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ ሉልሰገድ ተፈሪ፣ በጉባዔው ላይ የባንኩን አጠቃላይ ሁኔታ በአኀዝ በተደገፈ ሪፖርታቸው ሲያቀርቡ፣ የባንኩ የተጣራ ትርፍ ከአምናው ጋር ሲነፃፀር በ28.3 በመቶ መጨመሩን ገልፀው፤ ዕድገቱ በዳሸን ባንክ ታሪክም ሆነ ከሌሎች አቻ ባንኮች ጋር ሲነፃፀር ከፍ ያለ ውጤት እንደሆነ አስረድተዋል።

 

በ2000 ዓ.ም. በጀት ዓመት ዳሽን ባንክ ካተረፈው፣ 239 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር በተጨማሪ 93.5 ሚሊዮን ብር የዓመቱን ግብር መክፈሉ ታውቋል። እ.ኤ.አ. 1997 ጀምሮ በጠቅላላው 326.2 ሚሊዮን ብር ለመንግሥት የቀረጥ ግብር ገቢ ማድረጉም በሪፖርቱ ላይ ተሠምቷል።

 

የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ተክሉ ኃይሌ፣ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ከ454 ሚሊዮን ብር በ61 ከመቶ ጭማሪ በማድረግ፣ የተከፈለ ካፒታሉ ወደ 650 ሚሊዮን ብር እንደሚያድግ ገልፀው፣ የባንኩ ሀብት ደግሞ ከአምናው በ1.8 ቢሊዮን ዕድገት በማሣየት 7.8 ቢሊዮን ብር ሊደርስ እንደቻለ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገ የመጣው ባንኮች በብሔራዊ ባንክ የሚያስቀምጡት፣ በዳሸን መጠባበቂያ ባንክ ላይ የፈጠረውን ጫና በተመለከተ ፕሬዝዳንቱ እንደተናገሩት፤ ዳሸን ባንክ ሥራ ሲጀምር በብሔራዊ ባንክ ያስቀምጥ የነበረው 5 ከመቶ፣ በአሁኑ ወቅት 15 ከመቶ በመድረሱ ከባንክ 6 ቢሊዮን ብር፣ ጠቅላላ ሥራ ማስኬጃ 900 ሚሊዮን ብር በብሔራዊ ባንክ ሊቀመጥ በመቻሉ የባንኩ የሥራ ማስኬጂያ 4.4 ቢሊየን ብር ሆኖ የበጀት ዓመቱን መዝጋቱን ገልፀዋል።

 

በብሔራዊ ባንክ ተቀማጭ የሚደረገው 15 ከመቶ መጠባበቂያ ወለድ የሌለው እንደሆነ ይታወቃል።

 

የባንኩ የቦርድ ዳይሬክተሮች ሊቀመንበር አቶ ተክሉ ኃይሌ በበኩላቸው፣ ካለፈው በጀት ዓመት የተጣራ ትርፍ ውስጥ 172 ሚሊዮን ብር ወደ ባንኩ ካፒታል መዞሩንና 70.5 ቢሊዮን ብር ለባለ አክሲዮኖች እንደሚከፈል ተናግረዋል።

 

በቪዛ ካርድ አገልግሎት ከ34 ሺ በላይ ደንበኞቹ አርባ በሆኑ የአውቶማቲክ ገንዘብ መክፈያ ማሽኖች ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ 471 በሚሆኑ የክፍያ ጣቢያ ማሽኖች እየተገለገሉ የሚገኙ ደንበኞች ከ510 ሺህ በላይ መሆኑ ታውቋል። በበጀት ዓመቱ ዳሸን ባንክ በውጪ ምንዛሬ የቪዛ ካርድ አገልግሎት፣ 31.7 ሚሊዮን ዶላር ገቢም ሊያገኝ እንደቻለ ተገልጿል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ