የፊታችን ቅዳሜ በስዊድን ህዝባዊ ውይይት ያካሂዳሉ

UDJP deligates arrival, Stockholm

Ethiopia Zare (ኀሙስ ኅዳር 4 ቀን 2001 ዓ.ም. November 13, 2008)፦ አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲን በመወከል በአውሮፓ ሰባት ሀገሮች ለሥራ የመጡት ሊቀመንበሯ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እና አቶ አክሉ ግርግሬ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ከቀኑ በ8 ሰዓት ስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም ገቡ።

 

የልዑካን ቡድኑን በስዊድን የአንድነት ፓርቲ ድጋፍ ሰጪ ኮሚቴ እና የፓርቲው ደጋፊዎች በኦርላንዳ አየር ማረፊያ የተቀበሏቸው ሲሆን፣ የልዑካን ቡድኑ ተይዞለት በነበረው የሥራ ዕቅድ መሠረት የስዊድን የሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ከሆኑት ማሪታ ኡልቭስኩግን ጋር ተገናኝቷል።

 

ከዋና ፀሐፊዋ ጋር የተደረገው ውይይት ሰፋ ያለ ጊዜ የወሰደ ሲሆን፣ ወ/ት ብርቱካን እና አቶ አክሉ ስለፓርቲያቸውና ኢትዮጵያ ስላለችበት ሁኔታ በሰፊው አብራርተዋል። ዋና ፀሐፊዋ ማሪታ ኡልቭስኩግ እሳቸውም ሆነ ፓርቲያቸው የኢትዮጵያን ሁኔታ በቅርብ እንደሚከታተሉ ገልፀው፣ በግላቸውም ሆነ በፓርቲያቸው ስም የሚችሉትን ትብብር፣ አብሮ የመሥራትና ዕርዳታ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።

 

Anenet deligates with Social Demokraterna party

 ወ/ት ብርቱካንና አቶ አክሉ ከስዊድን ሶሺያል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ማሪታ ጋር ሲወያዩ

 

ማሪታ ኡልቭስኩግ ፓርቲያቸው ገዥ በነበረበት ወቅት የሲቪል ሚኒስትር እንዲሁም የባህል ሚኒስትር ሆነው ሠርተዋል። ማሪታ ኡልቭስኩግ ጋዜጠኛና በስዊድን ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው የ57 ዓመት እንስት ሲሆኑ፣ ከፓርቲው ሊቀመንበር ሞና ሳሊን ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው። ሞና ሳሊንም እንስት ናቸው።

 

W/t Birtukan, Marita, Ato Akilu
ከግራ ወደቀኝ - ወ/ት ብርቱካን፣ ማሪታ፣ አቶ አክሉ
ኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ውይይቱ ምን ይመስል እንደነበር በስዊድን የአንድነት ፓርቲ ድጋፍ ሰጪ ማኅበር ሰብሳቢ የሆኑትን አቶ ታምራት አዳሙን ጠይቋቸው የነበረ ሲሆን፣ አቶ ታምራት ”ውይይቱ ጠቃሚ ነበር” ሲሉ ገልፀውታል።

 

ነገ ዓርብ ኅዳር 5 ቀን 2001 ዓ.ም. (November 14, 2008) የልዑካን ቡድኑ ከስዊድን ፓርላማ አባላት ጋር ከቀኑ ሰባት ሰዓት (13፡00) ጀምሮ ለመወያየት ዕቅድ ተይዞለታል። ውይይቱን የጠራው የስዊድን ሊበራል ፓርቲ ሲሆን፣ የውይይቱ ሰብሳቢና አስተባባሪ የሆኑት ወ/ሮ ብሪጊታ ኡህልሶን ናቸው። ወ/ሮ ብሪጊታ ዕድሜያቸው 33 ሲሆን፣ የስዊድን ሊበራል ፓርቲ የፓርላማ ተመራጭ፣ የፓርቲው የውጭ ጉዳይ አፈ-ጉባዔ ናቸው።

 

ቅዳሜ ኅዳር 5 ቀን 2001 ዓ.ም. (November 15, 2008) ደግሞ ከቀኑ ሰባት ሰዓት (13፡00) ጀምሮ በስቶክሆልም ስካርፕኔክስ ከልቸርሁሰት የልዑካን ቡድኑ ከአንድነት ፓርቲ ደጋፊዎችና በስዊድንና አካባቢው ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት ያደርጋል። በዚህ ዝግጅት ላይ የልዑካን ቡድኑ ስለፓርቲያቸው ለኢትዮጵያውን ማብራሪያ እንደሚሰጡና ከተሳታፊዎች ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚሰጡ ለማወቅ ችለናል።

 

ከዚህም ሌላ ለፓርቲው የድጋፍ ገንዘብ ማሰባሰብ የሚደረግ ሲሆን፣ ዝግጅቱ እስከ ማምሻውን በመቀጠል የእራት ግብዣ እንደሚኖር የዝግጅቱ አስተባባሪዎች ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልጸዋል። የዝግጅቱ ሥፍራ ስካርፕኔክስ አሌ 25 (Skarpnäcks Allé 25) መሆኑንም አክለው ገልጸዋል። (ካርታውን አሳየኝ)

 

Andent party deligates, Arlanda airport, Stockholm
የአንድነት ፓርቲ ልዑካን በስቶክሆልም አቀባበል ሲደረገግላቸው
የልዑካን ቡድኑ በስዊድን የሚኖረውን የሥራ ጉብኝት የሚያጠናቅቀው ቅዳሜ ምሽት ሲሆን፣ እሁድ ወደ ሆላንድ ይበራል። ቡድኑ አውሮፓ የገባው ጥቅምት 28 ቀን (November 7) ሲሆን፣ በመጀመሪያ የተጓዘው ወደ እንግሊዝ እንደነበር መዘገባችን አይዘነጋም። በእንግሊዝ ከእንግሊዝ ባለሥልጣናት ጋር ከተወያየና ከፓርቲው ደጋፊዎችና ከኢትዮጵያውያን ከተወያየ በኋላ ወደ ቤልጅየም ብራስልስ አቅንቶ፣ እዚያም ከአውሮፓ የፓርላማ አባላት ጋር ተወያይቷል።

 

የብራስልስ ሥራውን ካጠናቀቀ በኋላ ወደ እንግሊዝ በድጋሚ በርሮ፣ ዛሬ ዓርብ ኅዳር 5 ቀን 2001 ዓ.ም. ወደ ስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም ገብቷል። ከስቶክሆልም ቀጥሎ ቡድኑ በያዘው ዕቅድ መሰረት ሆላንድን፣ ጀርመንን፣ ስዊዘርላንድን እና ኖርዌይን ይጎበኛል ተብሎ ይጠበቃል። በቀሪዎቹ ሀገሮችም ተመሳሳይ የሥራ ዕቅዶች እንዳሉት ታውቋል።

 

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!