ሦስት ጋዜጠኞች ግን እንደተከለከሉ ነው

Ethiopia Zare (ኀሙስ ጥር 29 ቀን 2000 ዓ.ም. February 7,2008)፦ የጋዜጣ አሣታሚነት ፈቃድ ተከልክለው ከነበሩት አምስት ጋዜጠኞች ውስጥ ለሁለቱ በትናንትናው እና በዛሬው ዕለት ከረዥም ጊዜ መጉላላት በኋላ እንደተሰጣቸው ለማወቅ ችለናል።

 

ምርጫ 97ን ተከትሎ ከቅንጅት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ወደ እስር ተግዘው ከነበሩትና በኋላም ከተፈቱት የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞች ውስጥ ጋዜጠኛ ሠርካለም ፋሲል፣ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ እና ጋዜጠኛ ወሰንሰገድ ገ/ኪዳን የጋዜጣ ፈቃድ ተከልክለው እንደነበር ይታወቃል።

ጋዜጠኞቹ ከእስር ከተፈቱ በኋላ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ለማስታወቂያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አመልክተው የነበረ ቢሆንም በወቅቱ ተገቢውና አፋጣኝ ምላሽ ሳይሰጣቸው ቆይቶ በስተመጨረሻ እንደተከለከሉ ተነግሯቸው እንደነበር በተለያዩ ሚዲያዎች መዘገቡ አይዘነጋም።

ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ የቀድሞው የሃዳር ጋዜጣ ባለቤትና ዋና አዘጋጅ፣ እና ጋዜጠኛ ወሰንሰገድ ገ/ኪዳን የቀድሞው የአዲስ ዜና ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ለሦስት ጊዜ ፈቃድ አይሰጣችሁም ከተባሉ በኋላ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተደውሎላቸው የይቅርታ ቦርዱ የሠጣችሁን የምስክር ወረቀት (ሠርቲፊኬት) ይዛችሁ ኑ ተብለዋል።

ሁለቱ ጋዜጠኞች ይቅርታ ጠይቀው ከተፈቱት ውስጥ ያሉበት ሲሆን፣ ሠርቲፊኬቱን ይዘው ከቀረቡ በኋላ ጋዜጠኛ ዳዊት "አውራአምባ ታይምስ" በሚል ስያሜ ትናንት፣ ጋዜጠኛ ወሰንሰገድ ደግሞ በዛሬው ዕለት "ሐራምቤ" በሚል ስያሜ የጋዜጣ ፈቃድ እንደተሰጣቸው ለማወቅ ችለናል።

ጋዜጠኛ ሠርካለም፣ ጋዜጠኛ ሲሳይ እና ጋዜጠኛ እስክንድር ግን እስከዛሬው ዕለት ድረስ ፈቃድ አልተሰጣቸውም። ሦስቱ ጋዜጠኞች ፍርድ ቤቱ ሚያዝያ 1 ቀን 1999 ዓ.ም. ከእስር በነፃ ካሰናበታቸው በኋላ አሣታሚ ድርጅቶቻቸውን ጥፋተኛ ብሎ ድርጅቶቹ እንዲዘጉና የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ መወሰኑ አይዘነጋም። ከዚህም ሌላ ሦስቱ ጋዜጠኞች የይቅርታ ደብዳቤውን ያልፈረሙ መሆኑ ይታወቃል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!