Ethiopia Zare (ዓርብ ኅዳር 12 ቀን 2001 ዓ.ም. November 21, 2008)፦ በዓለም አቀፍ የሮዴ ደሴት ኢንስቲትዩት አማካይነት፣ የኤርትራ-ኩናማውያን ስደተኞች ሕይወት የሚያሳይ ዶክመንተሪ ፊልም ተሠራ።

 

የኢንስቲትዩቱ ሠራተኞች በሰሜን ኢትዮጵያ በሚገኘው ”ሽመልባ” የስደተኞች ጣቢያ በመገኘት፣ የስደተኞቹን አኗኗር ከደሳሳ የሳር ጐጆአቸው አንስቶ አዲስ ሕይወት እስከሚጀምሩበት የአሜሪካ ኑሯቸው የሚያሳይ ዶክመንተሪ (ዘጋቢ) ፊልም ሠርተዋል።

 

ፊልሙ የሸመልባን አቧራማ መንገዶች፣ ስደተኞች ሕይወትን ለማሸነፍ የሚያደርጉትን ጥረትና እናቶችና ሕፃናት ውሃ ለማግኘት የሚያደርጉትን ጉዞ የሚያሳይ ሲሆን፣ ሕፃናቱም በቆሻሻ ቦታ ሲጫወቱ ያሳያል። ስደተኞቹ በመጠለያ ጣቢያው ለዓመታት የቆዩ ሲሆን፣ በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር (UNHCR) በኩል በስደተኝነት ተመዝግበው፣ በአሜሪካ እንዲኖሩ የተፈቀደላቸው ይገኙበታል።

 

ከስደተኞች መካከል አንዷ በሰጠችው አስተያየት፣ በጦርነት ውስጥ ተወልዳ በጦርነት ውስጥ ማደጓን፤ አሁን ግን የጥይት ድምፅ የማይሰማበት አካባቢ መኖር የምትፈልግ መሆኗን ገልፃለች።

 

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪም በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ሕይወትን መምራት አስቸጋሪ መሆኑንና፣ ሕይወታቸው በሚሰጣቸው ዕርዳታ ላይ ብቻ የተመሠረተ መሆኑን ተናግራለች። የልብስ፣ የውሃ ብሎም የመተዳደሪያ ችግር አለ ያለችው ይህችው ስደተኛ በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ያለው ኑሮ ከእስር ቤት አይሻልም ብላለች።

 

ሌሎች ስደተኞች ግን ተስፋ እንዳላቸው በዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር. በኩል ወደ ሮዴ ደሴት ለመጓዝ እየተጠባበቁ መሆናቸው በፊልሙ ተጠቅሷል።

 

የሮዴ ደሴት ዓለም አቀፍ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተርና የቀረፃው ቡድን አባል ዊሊያም ሹዌ ዶክመንተሪ ፊልሙ፣ ለስደተኞቹ አዲስ ኑሮ ሲኖሩ የሚያጋጥማቸው ፈተናና እንዴት መለማመድ እንዳለባቸው ለማሳየት ያለመ መሆኑን ገልፀዋል። ለዚህም ሮዴ ደሴት የደረሱትን ስደተኞች የአፓርትመንት ኑሮ፣ የባስ አጠቃቀም፣ የጤና ተቋማት ጉብኝት፣ የእንግሊዝኛ መማሪያ ተቋማትና የገበያ ሥፍራዎች መጐብኘታቸው በፊልሙ ተካቷል።

 

በየዓመቱ ከ150 - 200 የሚደርሱ ኩናማውያን ስደተኞች፣ በሮዴ ደሴት ለትርፍ ባልተቋቋሙ ድርጅቶች አማካይነት እንደገና እየተቋቋሙ ናቸው።

 

የሮዴ ደሴት ዓለም አቀፍ ኢንስቲትዩት በ1921 ዓ.ም. የተመሠረተ ሲሆን፣ ስደተኞችንና የሀገሬውን ችግሮች በመርዳት ይታወቃል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!